Wednesday, 17 April 2019

በሮተር ዳሙ ካቴድራል - ጣዖት አምልኮ?

Please read in PDF

   ሕዝቅኤል እስራኤልን ሲመለከታት በኀጢአት የተጨማለቀች አመንዝራ ሴትን ትመስላለች፤ ታማኝነቷን ያጐደለች ፍቅረኛ ናት፣ ከሕፃንነት ጀምሮ ቢከታተላትም፣ ከተጣለችበት ቢያነሣትም፣ “በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም።” (ሕዝ. 16፥4-5) ከተጣለችበት አንሥቶ በብዙ ምሕረቱ ቢታደጋትም እርሷ ግን “ … አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ።” እንዲል ፈጽማ አመንዝራ መንገድን ተከተለች።

   ከዚህ የከፋው ነገር ደግሞ፣ “በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ። ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል።” (ሕዝ. 16፥15-16) እንዲል ዐመጻዋ እጅግ በአደባባይ ኹሉ ተገልጦ ነበር። እስራኤል እንዲህ በበዛ ነውር ብትያዝም ጌታ ቸርነቱን አላጓደለባትም ነበር።
   እንዲያውም ሽማግሌዎቹ የቅናት ጣዖትን፣ ሴቶቹ ተሙዝ ለተባለው የባቢሎናውያን የልምላሜ ጣዖት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያመልኩ ነበር፤ (ሕዝ. 8፥1-1-18)። ምንም እንኳ መቅደሱ የእግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መገኘት ምሳሌ ቢኾንም ነገር ግን ሕዝቡ ኹሉ ጣዖትን በማምለክ ተጠምደው ነበር። ለእግዚአብሔር ብቻ በኾነበት ስፍራ እግዚአብሔር አባወራውና ባለቤቱ ተሰዶና ተባሮ፣ ጣዖት አምልኮ ገንኖ፣ ባዕዳን አማልክት ይመለኩ ነበር።  እግዚአብሔር በቤቱ ባዳ፣ ክብር እንደማይገባው ተቈጥሮ ተሽቀንጥሮ ተጥሎ ነበር። ለዚህም እግዚአብሔር ክብሩን ፈጽሞ ከመቅደሱ ቀስ በቀስ እንዳሸሸና እንደ ተለየ እንመለከታለን።
   እግዚአብሔር እስራኤልና ሕዝቦችዋ የተመኩበትንም ቅዱስ መቅደስ ፈጽሞ እንዲፈርስ፣ እንዲቃጠል፣ እንዲወድምም አድርጎታል፤ እነርሱ መቅደሱ እስካለ ድረስ እግዚአብሔር የትም አይሄድም ብለው ተመክተው ነበር፤ መቅደሱ የመገኘቱ ምልክት ነበርና፣ እግዚአብሔር ግን ጻድቅና ቅዱስ ነውና መቅደሱን ጭምር እንዲፈርስ በማድረግ እስራኤልን ለባቢሎን ምርኮ አሳልፎ ሰጥቶአል።
   መሥዋዕቱ አልተጓደለም፣ ዕጣኑም ይጤሳል፣ ዜማውም ይቀርባል፣ ጾሙም አልቀረም፣ ሰውነት መዋረዱ፣ ልብስን መቅደዱ፣ ዐመድ መነስነሱ፣ ማቅ መልበሱ … የዘወትር ተግባር ነው፤ ነገር ግን ውጫዊው ክፍል እኒህ ኹሉ ነገሮች ያሉበት ቢኾንም፣ ውስጡ ግን እጅግ የረከሰና በጣዖት አምልኮ የጨቀየ ነበር፤ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያከብር ማናቸውም አገልግሎት መንፈሳዊ የሚመስል ብዙ መልክ ኖሮአቸው ጉባኤው በመላ በአጋንንት ሊወረስ ወይም የአጋንንት ማኅበር ሊኾን ይችላል።
 ከቃጠሎው በፊት
ከቃጠሎው በኋላ
የዛሬዎቹ አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ሃይማኖታዊ መልክ እንጂ እግዚአብሔርን ፈጽመው እንደማያከብሩ እጅግ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። ከእነዚህም መካከል ከሰሞኑ የተቃጠለውን የፓሪሱን ኖተር ዳም ካቴድራል ከቃጠሎ በኋላ ውስጣዊውን ገጽታውን መመልከት በቂ ነው፤
ከቃጠሎው በፊት
ከቃጠሎው በኋላ
  ይህ ከካቴድራሉ ቃጠሎ በኋላ የተገለጠ ገጽታ ነው፤ መንፈሳዊው ካቴድራል ውስጡ እግዚአብሔርን የማያከብር እጅግ አጸያፊ ምስሎችን በውስጡ የያዘ ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ አስመሳይነትንና ግብዝነትን ፈጽሞ ይጠየፋል፤ በእርሱ መዘበትም ነው። አምልኮን በማስመሰል ማምለክ እጅግ አጸያፊ ነው፤ ዛሬም በአገራችን የሚበዛው አምልኮ ከዚህ የተለየ አይመስልም፤ ብዙ ገዳማት ውስጥ በግብረ ሰዶም እንዳለ ይታወቃል፣ ስግብግብነትና ጉበኝነት የቤተ ክህነትና የአብያተ ክርስቲያናት መገለጫ እስኪመስል ተስተውሏል፤ ሃብት ማካበትና ድኾችን በፈውስና በማዳን ሰበብ መበዝበዝና መንጠቅ የተለመደና የተፈቀደ እስኪመስል ደርቷል፣ በሃይማኖት ካባ ምድሪቱን ማጭበርበር ናኝቶአል።
   እግዚአብሔር በስሙ የሚደረግን ማናቸውንም ክፋት ንስሐ እስካልገባን ድረስ በጠራራ ፀሐይ ያሰጣዋል፣ ያዋርደናልም። በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በትክክል የማያምኑትንና በልጁ የሚዘብቱትን እግዚአብሔር እስከ መጨረሻ ያዋርዳቸዋል። ጌታ በምድሪቱ ላይ የሚሠራውን ግፍና ዓመጻ ጣልቃ በመግባት እንዲቈጣጠረው እንማልዳለን፣ እኛም ኹላችን በእውነተኛ ንስሐ መመለስ ይኹንልን፤ አሜን።


2 comments:

  1. ጌታ ኢየሱስ ያግዘን!

    ReplyDelete
  2. GEta beneger hulu yirdan. betam asferi zemn nw.

    ReplyDelete