Please read in PDF
የፍጥረትን
አፈጣጠር የሚነግረን ቅዱስ ሙሴ የኦሪቱን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፍ ሲጀምር፥ “…ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም
ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ …” (ዘፍ.1፥2) ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን እስኪል ድረስ፥ ጨለማው በምድር ሁሉ ላይ ሰልጥኗል
፤ ማለትም፥ ምድር ለሥራ የማትመችና የማትታይ ፣ ቅርጽ አልባና ባዶ ፣ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ የተወረሰች ነበረ ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔር
ብርሃን ይሁን” ባለ ጊዜ ግን፥ ለሥራ የማትመቸዋ ምድር ታየች ፣ ተገለጠች ፣ ሕልውናዋ ታወቀ ፤ ቅርጽ አልባና ባዶ የነበረችው
አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ልታበቅል ዝግጁ ሆነች ፤ አስደሳችና ውብ ውበትን ለበሰች ማለት ነው፡፡ ጨለማዋን የእግዚአብሔር
ብርሃን ገልጦላታልና፡፡
ለተፈጠረችው ምድር ጨለማ ቀድሞ ሰልጥኖባት እንደነበረው እንዲሁ፥ ዋናው
ብርሃን ዘእምብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሊሰለጥንና በሕይወታችን ብርሃንን ከማብራቱ በፊት የኃጢአት ጨለማ በልባችን ለዘመናት
ሰልጥኖ ነበር፡፡ ምድር ስትፈጠር ብርሃን ይሁን ያለው እግዚአብሔር ወልድ፥ አሁንም በአዲስ ኪዳን ልደት፥ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን
የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” (2ቆሮ.4፥6) በማለት፥
በዚህ ቃል ቀድሞ ምድር ሕልውናዋ እንደተገለጠ፥ አሁንም ለእኛ በጽድቅ መኖርና መገለጥ ክርስቶስ መሠረትና ዋናችን ሆኖልናል፡፡ እርሱ
በደሙ ቤዛነት ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን አውጥቶናልና፡፡



