Tuesday, 10 May 2016

“ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” (ሐዋ.2፥32)

   
   ደቀ መዛሙርት የተጠሩለት ዋና ዓላማ አንድና ግልጥ ነው፡፡ “መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥” (1ቆሮ.15፥3-4) የሚለውን ሕያው እውነት ለዓለሙ ሁሉ ማወጅና መመስከር ነው፡፡
   
          በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ገና ከጽንሰቱ ጀምሮ አብሮ ነበር (ሉቃ.1፥35) ፤ በአገልግሎቱ ጅማሬም መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አልተለየውም (ሉቃ.4፥17) ፤ ሲጠመቅም እንደርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ ታይቷል (ማቴ.3፥16) ፤ በትንሣኤውም እግዚአብሔር የሞትን ጣር አጥፍቶለት (ሐዋ.2፥24) እንደቅድስና መንፈስ (ሮሜ.1፥4) ከሙታን መካከል ተነስቷል ፡፡

     እንደቅድስና መንፈስም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መነሣቱ ብቃት ያለው አዳኝ ወይም እውነተኛ መሲሕና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ፍጹም ያስረግጣል፡፡ በእርግጥም “ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው ሕያው የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ወይም የኢየሱስ መንፈስ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ነው” (ሮሜ.8፥11)፡፡ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም ሲወለድ፥ ክርስቶስ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ከሙታን መካከል በመነሣት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ አዎን! ከክርስቶስ ኢየሱስ በቀር ማንም ከሙታን መካከል የተነሣ የለም፡፡
     “ስለዚህም ጌታ ሰው ሆነ ፤ ሰውንም አስነሣ ፤ እርሱም በመዋቲ ሥጋ ይነሣ ዘንድ በፈቃዱ ሞተ ከተነሣም በኋላ ዳግመኛ አይሞትም ፤ ከትንሣኤው በኋላ ግን ጌታ ይህን አልተናገረም ፤ ከሰውም ወገን ማነንም ተነሥ ፤ ከመቃብር ውጣ አላለም ፤ ዳግመኛ እስከሚመጣበት ቀን ድረስ ለሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው በሚነሡበት ቀን ሙታን ይነሣሉ አላቸው፡፡”
              (ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ምዕ.59 ቁ.49)

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስን ከሙታን መካከል መነሣት እርግጠኛ ሆኖ ይናገራል፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ፊት ለፊት አጊኝቶ ከእርሱ ሁሉን ተረድቷልና፡፡ “ … ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ” (1ቆሮ.15፥8) ከማለት አልፎ፥ ሐዋርያም በእርሱ በራሱ እንደሆነ ሲናገር “  በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ …” (ገላ.1፥1) በማለት በግልጥ ተናግሯል፡፡ አሥራ አንዱ ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርትም ጌታን ከሙታን መካከል መነሣቱን የዓይን ምስክሮች ሆነው ፊት ለፊት አይተውታል፡፡ (ማቴ.28፥9 ፤ 17 ፤ማር.16፥9 ፤ 12 ፤ 14 ፤ ሉቃ.24፥15-31 ፤ 36-51 ፤ ዮሐ.20፥13-18 ፤ 19-23 ፤ 26-31 ፤ 21፥1-22 ፤ ሐዋ.2፥32 ፤ ሮሜ.4፥24 ፤ 1ቆሮ.15፥4-9 ዕብ.13፥20 ፤ 1ጴጥ.1፥21)
     ለኃጢአታችን ክርስቶስ ኢየሱስ መሞት የሚገባውን ያህል ከሙታን መነሣቱ ደግሞ እጅግ አስፈላጊና ለሞተልን ሞቱ ትርጉም ሰጪ ዓቢይ ነገር ነው፡፡ ሐዋርያው “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት” (1ቆሮ.15፥14) እንዳለው ክርስቶስ ከሙታን መካከል ባይነሣ ሁሉም ነገር ባዶ ፤ የእኛም ምስክርነት የሐሰትና የማይጨበጥ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ ኢየሱስ ከሙታን መካከል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተነሥቷል፡፡
    እርሱ ከሙታን መካከል ሊነሣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዳስፈለገው፥ እኛም ዛሬ በማናቸውም መንፈሳዊ ሕይወታችን የበረታን እንድንሆንና እንዲከናወንልን በመንፈስ ቅዱስ ፍጹም ልንደገፍ ይገባናል፡፡ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መነሣት ለአንዳንዶች የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ዝቅ የሚያደርግ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ የባርያን መልክ ይዞ ለመስቀል ሞት የታዘዘ በሆነ ጊዜ ከአምላክነት ዝቅ እንደማለት ወይም አምላክነትን እንደመቀማት አልቆጠረውም፡፡ (ፊልጵ.2፥6-8)
    ጌታ ኢየሱስ የአማኞች ሁሉ የጽድቅ ሕይወት ዋና መሠረትና ዓቢይ ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ፥ “  የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።” (1ጴጥ.2፥21) በማለት እንደተናገረው፥ ወደጌታ ኢየሱስ ወደግንዱ ስለምናድግ እርሱን በመምሰል ልንመላለስ ይገባናል፡፡ ምንም የከበረና የተወደደ አገልግሎት ቢሆንም ወደሰባኪ ፣ ወደጳጳስ ፣ ወደዘማሪ ፣ ወደቄስ … አናድግም ፤  በመንፈስ ቅዱስ በመደገፍ ወደዋናው ግንድ ወደኢየሱስ ክርስቶስ ልናድግ ይገባናል፡፡ ፍጽምና ያለበት የማይሳሳተውና በዚህች ጠማማ ትውልድ በበዛባት ዓለም ላይ ሳይሳሳት የጽድቅ ሕይወት ምስክር ነውና ወደእርሱ ብቻ ልናድግ ይገባናል፡፡
      እርሱም ሲያስተምር እንዲህ አለ፦ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል” (ዮሐ.15፥5) አንድ ቅርንጫፍ ከግንዱ ጋር ካልተጣበቀ በቀር ፈጽሞ ሊያፈራና ሊያድግ እንደማይችል ሁሉ አንድ አማኝም ያለክርስቶስም ፈጽሞ ሊያፈራ ፤ ሊያድግ አይቻለውም፡፡ የማያስፈልገው ነገራችን ከእኛ በመወገድ ልንገረዝና ፍሬ ልናፈራ የሚቻለን እንኳ ከግንዱ ሳንለያይ ፍጹም ተጣብቀን የኖርን እንደሆን ብቻ ነው፡፡ ያለእርሱ ምንም ማድረግ አይቻለንም ፤ ያለ ክርስቶስ!!!
     ሕይወታችን የሕይወት መዓዛ የሆነውና ብዙዎችን ለክርስቶስ ሕይወት ማራኪ ያደረግነው፥ ክርስቶስ እርሱ አምላካችን ከሙታን መካከል ስለተነሣ ነው፡፡ እርሱ ከሙታን ለመነሣቱ እኛ ምስክሮች ነን በማለት ሐዋርያት መስክረዋል፡፡ ይህን እውነት ለመጀመርያ ጊዜ አፋቸውን ከፍተው የተናገሩት ደግሞ ጌታን ሰቅለው ለገደሉት አይሁድ ነው፡፡ በአንዲት ገረድ ፊት ክርስቶስን አላውቀውም ብሎ ብዙ ሲራገም የነበረው ጴጥሮስ፥ በገዳዮቹ ፊት ቆሞ፥ “በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።” በማለት ምንም ሳይፈራ መንፈስ ቅዱስን ተመልቶ ተናግሯል (ሐዋ.2፥23)፡፡ አዎን! እርሱ ከሙታን መካከል ተነሥቶ የሕይወት ራሱ ሆኗል፡፡
      ለዚህ ነገር ከሐዋርያቱ ጋር በሚስማማ ቃል እኔም ምስክር ነኝ ፤ በትንሣኤው ኃይል እኔንም ከኃጢአተኛ ሕይወቴ አስነሥቶ ዘላለማዊ ሕይወቱን ሰጥቶኛልና፡፡ “በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና” የሚለው ቅዱስ ቃል፥ እግዚአብሔር የኀጢአትን ባሕርይ ፍጹም ኃጢአት በሌለበት በክርስቶስ ሰብአዊ ተፈጥሮ ላይ ሆኖ የኰነነበትን ሁኔታ ያሳያል (ሮሜ.8፥3)፡፡ አዎን! ክርስቶስ ኃጢአትን በሞቱና በትንሣኤው ኰንኖታል ፤ ድል ነስቶታል ፤ እንዲሁም በሕይወት መንፈሱ ዘላለማዊ አርነትና ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ እንግዲህ አብርሐም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ ጌታ አምኖ እንደጸደቀ፥ እንዲሁ እኛም “ጌታ ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው” በማመናችን ያለጥርጥር እንጸድቃለን (ሮሜ.4፥24)፡፡ ደግሞም በትንሣኤው ኃይል መጽደቃችንን ያለአንዳች ፍርሃት እንመሰክራለን፡፡ አዎን! እርሱ ከሙታን መካከል ተነሥቷል ፤ መቃብሩም ባዶ ነው ፤ ለዚህም ምስክሮች ነን፡፡
    ጌታ ኢየሱስ ሆይ! የትንሣኤህን የታመኑ ምስክሮችን አብዛ፡፡ አሜን፡፡


1 comment:

  1. የባረከህ አምላክ ይባረክ ዘመንህ ከጌታ ጋር ይለቅ

    ReplyDelete