Tuesday, 2 September 2025

በሰማይ ኢየሱስ በምድር ጰራቅሊጦስ አለን!

 Please read in PDF

ቅዱስ ጳውሎስ ለሮም ቤተ ክርስቲያን በጻፈው መልእክቱ፣ በግልጥ ቃል፣ “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም።” (ሮሜ 8፥1) በማለት፣ በክርስቶስ ላሉት ከእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ኵነኔ እንደማይጠብቃቸው ተናግሮአል፤ ክርስቶስ ስለ ሞተልን፤ ደግሞም ከሙታን መካከል ስለ ተነሣልን የኀጢአት ኃይል፤ የገሃነም ጉልበት የተሰበረልን የዳንን ሕዝቦች ነን።



ምንም እንኳ የዳንን ሕዝብና ወገን ብንኾንም፣ ምልልሳችን በወደቀውና ሙሉ ለሙሉ ባልተዋጀው ዓለም እንደ ኾነ መዘንጋት የለብንም፤ “በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።” (ገላ. 5፥16) የሚለው ቅዱስ ቃልና “በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮሜ 7፥23) በሚሉት ንባባት ውስጥ፣ እግዚአብሔርን ለማክበር የሚፈልገው አዲሱ ሰውነታችን፣ባለማቋረጥ ከአሮጌው የኀጢአት ባሕርይ ጋር የሚዋጋ መኾኑን ሊስተባበል የማይችል ሐቅ ነው።

አሮጌው ተፈጥሮ ወይም ሥጋ ወይም የኀጢአት ኃይል ዘወትር ከመገዛት ይልቅ መግዛት የሚሻ፤ በእግዚአብሔርም ላይ የሚያምጽ የኀጢአት ባሕርይ ነው። ምንም እንኳ የዳንን ብንኾን፣ በዚህ ምድር እስካለን ድረስ ከዚህ ውጊያና መጋደል ከቶውንም ልናመልጥ አንችልም። በተለይም አማኝ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እያደገ ሲሄድ፣ የውጊያው ተከታታይነት የማያቋርጥና እየጠነከረ የሚሄድ ነው።

ስለዚህም ልክ ለመዳን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሊሞትና ሊሠዋልን እንዳስፈለገው እንዲኹ፣ በወደቀው ዓለም ላይ ስንመላለስ የምናደርገውም ተጋድሎ በእግዚአብሔር እንጂ በእኛ የሚቻል አይደለም፤ ለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ፣ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐ. 14፥15-17) በማለት የተናገረው።

ቅዱስ ጳውሎስም በምድር ለሚገጥመን ማናቸውም ፈተና፣ “መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤” (ሮሜ 8፥26) በማለት፣ መንፈስ ቅዱስ አብሮን የድካማችንና የመቃተታችን አካል እንደ ኾነ ተናግሮ፣ በሰማይ ደግሞ የሞተው ይልቁንም ደግሞ ከሙታን መካከል የተነሣው ክርስቶስ ኢየሱስ በአብ ዘንድ ያለ ብርቱ ተሟጋች ዋስትናችን መኾኑን የሚመሰክረው፤ (ሮሜ 8፥34)።

ስለዚህም በምድር ለሚገጥመን ማናቸውም ድካምና ችግር፣ መንፈስ ቅዱስ አብሮን አለ፤ በሰማይም ለሚነሳብን ማናቸውም ክስና ተቃውሞ ሞታችንን ያሸነፈውና ከሳሻችንን የጣለው ክርስቶስ አለልን፤ ከዚህ የተነሣ አማኝ ከቶውንም ሥጋትና ፍርሃት የለበትም! ይህ የጽድቅ እውቀት “ድኛለኹ” በሚል ሰው ኹሉ ዘንድ ለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም።

መርሳት የሌለብን እውነት ግን፣ “… የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።” (ዕብ. 12፥24) የተባልን እኛ ደግሞም፣ “… ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤” (ዕብ. 12፥2) ተብለናል፤ ደርሰናል ነገር ግን ለመድረስ እንሮጣለን! ለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ አማኝ ኾነው ዳተኝ የኾኑ ወገኖችን እንዲህ በማለት ያስጠነቀቀው፣

“ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ።” (ዕብ. 3፥12)።

ደግሜ እላለሁ፣ ይህ የተነገረው “ወንድሞች” ለተባሉ መኾኑን አንዘንጋ!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:

Post a Comment