ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ከክርስቶስ ትምህርት፣ ሕይወትና ሥራ አንጻር ተሐድሶ እንደሚያሻት ለጥያቄ የማይቀርብ ሐቅ ነው። በተደጋጋሚ ቤተ ክርስቲያኒቱ ራስዋ፣
“ተሐድሶ እንደሚያሻት” ስትናገር ሰምተናታል። ከዚኹ ጋር በተያያዘ፣ “ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማደስ” ከሚንቀሳቀሱ አካላት ሦስት ዓይነት
ተግዳሮቶች በግልጥ ይታያሉ፤
1.
የጠመጠሙ ግን የተሐድሶ ጠረን እንኳ የማይታይባቸው “ሐዳስያን”፦ ሚዲያውን
የሞሉት፣ ጥምጣም ጠምጥመው፣ ካባ ደርበው፣ መስቀልም ጨብጠው… ስድብና ብሽሽቅ የሚቀናቸው፣ ርኅራኄ አልባ ቃላትን የሚጠቀሙ፣ “እናድሳቸዋለን”
የሚሉትን መምህራን፣ ዘማርያን፣ ጳጳሳትና መነኮሳት ስማቸውን ጠርተው ሊማልዱላቸው የሚያቅራቸው፣ ለጤናማና ለትክክለኛ የወንጌል አገልግሎት
ልባቸው የወረደ፣ ለየትኛውም ኅብረት ራሳቸውን የማያስገዙ፣ መጋቢ
የሌላቸው፣ “ሚኒስትሪ” ከፍተው የውሸት ሪፖርት እያቀረቡ ገንዘብ የሚያጋብሱ፣ … “ለኦርቶዶክስ ግን ሐዳሲ ነን” የሚሉ ቊጥራቸው ጥቂት አይደለም።
2.
“ተሐድሶ” መባል የማይፈልጉ ሐዳስያን፦ ከኦርቶዶክስ ተለይተው የራሳቸው ማኅበር
ቢኖራቸውም “ተሐድሶ” መባልን የሚጠየፉ፣ ከሌላው ጤናማ የተሐድሶ ኅብረት ጋር በአብሮነት መሥራት የማይፈልጉ፣ ራሳቸውን የተሐድሶ
መለኪያ ጥግ አድርገው የሚቈጥሩ፣ እንደ ለ“እውነት ቃል አገልግሎት”ና መሰል “cults” ደጆቻቸውን ጠርቅመው የማይዘጉ፣ ከወንድማማችነት
ይልቅ “አገልግሎት” የሚበልጥባቸው፣ ሌላውን አገልግሎት የበታችና ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ … አስቂም አሳዛኝም የ“ተሐድሶ ማኅበራት”
አሉ።
3.
ሸክሙና ፍላጎቱ ኖሯቸው ግን ዕውቀትና ቅንአት የሌላቸው፦ አንዳንዶች ኦርቶዶክስን
ለመድረስና በወንጌል እንድትረሰርስ ፍላጎትና ሸክም አላቸው፤ እንዲህ ያሉት በኦርቶዶክሳውያንና በወንጌላውያንም አብያተ ክርስቲያናት
መካከል አሉ፤ ጠንካራ ሸክም ቢኖራቸውም ግን እንዴት መድረስ እንደሚቻል ወይም በምን መልኩ ሊፈጸም እንደሚቻል አያውቁም።
በሦስተኛ ላይ የተጠቀሱትን፣ ማቅናትና ማስተካከል
አይከብድ ይኾናል፤ ኹለቱ ግን ለተሐድሶ አገልግሎት እጅግ አደገኛና አዳጋች ናቸው። አገልግሎቱ ለብዙዎችም እንዳይደርስ የማሰናከያ
ዐለትነታቸው ያይላል።
ለእውነተኛ ተሐድሶ እሠራለኹ የሚል የትኛውም አካል፣
መጀመሪያ ራሱን በቅዱስ ቃሉ ማደስ፣ ማነጽና መገሰጽ ይገባዋል። ከአገልግሎት በፊትም ወንድማማችነትና የመንፈስ አንድነት እንደሚቀድም
መናገር ያስፈልገናል። እንዲህ ያሉ “ስመ ገናና ግን ድኩም ሐዳስያን” ራሳቸውን ቢያስተካክሉ መልካም ነው!
ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶነት ለሕዝባችን በመራራትና እጅግ
በማዘን እንደ ሙሴ፣ “… አሁን
ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ…” ወይም እንደ ጳውሎስ፣ “ብዙ ኀዘን
የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ
ይመሰክርልኛል። በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። … ወንድሞች
ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው።” እንዳሉት ለሕዝባችን የምናምጠው ታላቅ ምጥ ነው።
ይህ ደግሞ እንደ ነህምያ፣ “ … በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት
እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። …” ከሚለው ከእውነተኛ ንስሐና ኑዛዜ የሚመነጭ ቅዱስ መራራት ነው!
እግዚአብሔር እውነተኛ ተሐድሶና ታሪካዊ ኦርቶዶክሳዊነትን በምድራችን ላይ እንዲያመጣ በብርቱ እንናፍቃለን!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24)
አሜን።
መልካም ጽፈሀል
ReplyDelete