Monday, 30 December 2013

የኢየሱስ ደም - ክፍል አራት

Please read in PDF                                                                           

የኢየሱስ ደም አገልግሎት

 “ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ” (1ዮሐ. 1፥9)

 “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን የሚታይ” (ዕብ. 9፥24)

 “በቅዱስ ደሙ ኃጢአታችንን የሻረ” (ትምህርተ ኅቡዐት)

 “መዓዛው የጣፈጠ ንጹሕ መስዋዕት” (ቅዱስ ቄርሎስ)

ፊተኛው የደም አገልግሎት ኀጢአትን ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ፣ ከማንጻት ይልቅ እያዳፈነ የኀጢአት ፍህም በየማለዳው አዲስ እየኾነ ምድን በእድፈትና በርኩሰት ስላካለለ ኢየሱስ ከዕድፈትና ከርኩሰት ከፊት መጨማደድም ንፁሕ የኾነች (ኤፌ. 5፥27) ቤተ ክርስቲያንን ያዘጋጅና ይሞሽር ዘንድ ወደደ። ስለዚህም በገዛ ደሙ የዋጃትንና ያነጻትን ቤተ ክርስቲያን ርሱ በገዛ ፈቃዱ መሠረተልን፤ (ሐ.ሥ. 20፥28)።

ቤተ ክርስቲያን የደሙን አገልግሎት ፍጹም ታምናለች የደመቀችበት፤ ያጌጠችበት ለሙሽራው ኢየሱስ የተሞሸረችበትና ሙሽሪት ኾና የቀረበችበት የጌታ የኢየሱስ ደም ነው። የደሙን አገልግሎት የማታምን ቤተ ክርስቲያንና የማያምን አማኝ ፈጽሞ ክርስቶሳዊ ክርስቲያን መኾን አይችልም። የኢየሱስ የደሙ አገልግሎት ዛሬም ያልተቋረጠ የደሙን አቅራቢው ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ኢየሱስም የማይለወጥና የዘላለም ክህነት ያለው ነው፤ (ዕብ፣ 7፥24)። አስተውሉ፤ የታረደው በግ ዛሬም በዙፋኑ ሕያው ኾኖ አለ፤ በእግዚአብሔር አኹን ውስጥ ኾኖም በዙፋኑ የሚታየው እንደ ታረደ በግ ኾኖ ነው።

በዳግመኛ መምጣቱ የሚመጣው እንኳ የታረደበትን ችንካር እያሳየ ነው፤ (ራእ. 1፥7፤5፥9፤ ማቴ. 24፥30)። በጉ ሊታረድ ግድ የኾነው ምንም ኃጢአት የሌለበት ኾኖ ለኃጢአተኛው አዳም ሊሞት በሥላሴ ዘንድ ምክሩ ስለ ጸና ነው። የሞተውንና የወደቀውን ሊያነሣ የማይሞተው ሞቶ፤ እንደ ታረደም ኾኖ ታየ።

የታረደው በግ ደም ዋና አገልግሎት፦

  1. ደሙ አዲሱንና ኪዳንና ሕያውን መንገድ መርቆ የከፈተ ነው፤

ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለደም አልተመረቀም፤ ጌታ ደካማዋንና ሙት የነበረችውን የኵነኔ አገልግሎት መንገዷን መርቆ የከፈተውና ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስቱ ሊገባ ድፍረት የኾነው በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርበውና በእጁ የያዘው ደም ነው። ያለ ደም ወደ ቅድስት ፈጽሞ መግባት አይቻልምና።

በአንድ አገር የሚሠሩ ታላቅ የመንገድ ሥራዎች የምረቃ ሥርዓታቸው የሚከናወነው በአገሪቱ ዋና ባለሥልጣን (መሪ) ነው።  ዋናው ባለ ሥልጣን የምረቃዋን ሪባን ገመድ ቆርጦ  በመንገዱ ከተራመደበት በኋላ ሌሎች ርሱን ተከትለው ይጓዛሉ። ከዚያን ቀን ጀምሮ መንገዱ ለኹሉም አካላት ክፍት ይኾናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በር ኾኖ በደሙ መርቆ የከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ርሱ የምሕረቱ ዓመት አዲስ ኪዳን ነው። “በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት … አለን” (ዕብ. 10፥19)፤ ምንም አንኳ ኀጢአተኞችና በደለኞች ብንኾንበልጁ በኩል የምንገባው  ወደ ዘላለም ክብሩ፤ የምንወርሰውም የዘላለም ሕይወትን ነው፤ (ቈላ. 2፥13፤ ዮሐ. 3፥15)፤ ሕይወታችን የኾነው ክርስቶስ በሚገለጥበት በዚያን ጊዜ እኛም ደግሞ ከርሱ ጋር በክብር እንገለጣለን፤ (ቈላ. 3፥4፤ 1ተሰ. 4፥17)።

“ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤” (ኤፌ. 2፥8) ያለርሱ ጸጋና ያለርሱ መንገድነት ወደ አብ መድረስ አይቻልም (ዮሐ. 14፥6)፤ ቅዱሳን ኹሉ የሄዱበት መንገድ ርሱ መርቆ በከፈተው ቅዱስና ሕያው መንገድ ነው።ወደ አብ የሚያደርሰው ይህ መንገድ የማያሳስት መንገድ ነው። ቅዱሳን ኹሉ የሄዱበት መንገድ ርሱ መርቆ በከፈተው ቅዱስና ሕያው መንገድ ነው። ወደ አብ የሚያደርሰው ይህ መንገድ የማያሳስት መንገድ ነው።

በደሙ ተመርቆ ከተከፈተውም መንገድ በቀር ሌላ ወደ ሕይወትና ወደ እረፍት የሚያደርስ መንገድ ፈጽሞ የለም። ደሙ የከፈተልን መንገድ የሕይወትና የልምላሜ መንገድ ነው። ክርስትና የሚለው አዲስ መንገድ ላይ መጓዝ የጀመርነው ክርስቶስ መርቆ ከከፈተው በኋላ ነው። አዲሱም ኪዳን ላያረጅ ፍጹም የታተመበት ኅትመት ሕያውና ለዘላለም ትኩስ በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው።

2.   ደሙ ቤዛችን ነው

“በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።”

“በኋለኛው ዘመን የምክርህን አበጋዝ መድኀኒት ቤዛ የሚኾን ልጅህን ሰደድህልን” (የሐዋርያት ቅዳሴ)

“ስለ ፍጥረትህ ኹሉ ቤዛ ኾኖ በእግዚአብሔር ቸርነት በሥጋ ሞተ”[1]

“ከአዳም ጀምሮ እስከ ዛሬ ከተፈጠረው ፍጥረት ኹሉ ማንም ማን ሊያድነን አልቻለም፤ ከእግዚአብሔር ቃል በቀር በሰው ቢኾን አለኝታችን ከንቱ እዳይኾን የባሕርይ አምላክ ርሱ ሰው ኾነ እንጂ። ከሰው ወገን የሚሾም ሊቀ ካህናት ኹሉ በመጽሐፍ እደ ተነገረ ስለ ሰው ይሾማል፤ ስለዚህም ጌታ ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከሰው ወገን ተወለደ፤ እግዚአብሔር ቃል ሰው ኾነ፤ አምላ በመኾኑ ያድነን ዘንድ ሰው በመኾኑም ለእኛ ቤዛ ኾኖ ይሞትልን ዘንድ።” [2]

“ቤዛ” የሚለውን ቃል “አዳኝ መድኃኒት። ዋቢ ኃላፊ መድኅን። በካሳ መልክ ወይም እንደ ምትክ፤ እንደ መለወጫ፣ እንደ መያዣ የሚቀርብ …” ብሎ ይፈታዋል።[3] በሌላ ትርጉም ደግሞ “የተያዘን ወይም የተወሰደን ነገር ለማስመለስ የሚከፈል ዋጋ፣ ካሳ፣ ለውጥ …” ነው ይላል።[4]

በሞቱ ለሚያምንበት ኹሉ ቤዛ ኾኖ በእግረ አጋንንት፤ በሞት ይገዛ የነበረውን አዳምንና ዘሩን በሞቱ ካሳ ክሶ፤ ደሙን አፍስሶ በመከራና በሐዘኑ ኹሉ ምትክ ኾኖ ወደ ቀደመና ሕያው ክብሩ የመለሰው ሥጋ የለበሰው ክርስቶስ ነው፤ (ማር. 10፥45፤ 1ጢሞ. 2፥5)።

ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች በልዩ የነገረ መለኮት ዕውቀታቸው፣ “ቤዛነት አምላክነት ያሻዋል” ይላ። ክርስቶስ ቤዛችን ነው የምንለው፣ የእኛ ምትክ ኾኖ ከታላቅ የፍቅሩ ባለጠግነት የተነሳ እኛን ተገብቶ፤ ዕዳችንን ኹሉ ከፍሎ በመቤዥ በደሙ ነጻ ስላወጣን ነው። ቤዛነት የክርስቶስ ብቻ ነው፤ ከፍጡር ወገን ቤዛ መኾን የሚቻለው ማንም የለም። የዕዳ ዋጋ የሚከፍል አካል ርሱ ቀድሞ ከዕዳው ነጻ መኾን መቻል አለበት። ከክርስቶስም በቀር ከአዳም በደልና ዕድፈት ነጻ ኾኖ ዕዳችንን ከፍሎ መድኃኒትና ቤዛ የኾነን የለም።

ቤዛነት የክርስቶስ ብቻ ነው፤ ከፍጡር ወገን ቤዛ መኾን የሚቻለው ማንም የለም። ዋጋ የሚከፍል አካል ርሱ ደግሞ ከዕዳ ነጻ መኾን መቻል አለበት። ከክርስቶስም በቀር ከአዳም በደልና ዕድፈት ነጻ ኾኖ ዕዳችንን ከፍሎ መድኀኒትና ቤዛ የኾነን የለም። ርሱ በንጹሕ ደሙ ለበደለኛው ለሰው ዘር ኹሉ ዋጋ የኾነና በዋጋውም ገዝቶ የዋጀን ነው።

“ቤዛነት አምላክነት ያሻዋል” የሚባለው ከአምላክ በቀር ፍጹምና ንጹሕ ቤዛ ፈጽሞ ስለሌለ ነው፡፤ ምንያቱም ሰው የማይበድል አይደለምና፤ በተጨማሪም “ጻድቅ አንድስ እንኳ የለም” (2ዜና. 6፥36 ሮሜ 3፥11) በማለት ቃሉ ስለደመደመ ንጹሕና ፍጹም ቤዛ መኾን የሚቻለው ከብርሓን የተገኘው ብርሃን፣ ከእውነተኛው አምላክ የተገኘው እውነተኛው አምላክ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋን የነሳውና ዘመዳችን የኾነው ኢየሱ ክርስቶስ ብቻ ነው። ርሱ አምላክ የኾነ ሰው፣ ሰው የኾነ አምላክ ነውና።

ክርስቶስ የመጣበት ዋና ዓላማው “ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” እንደ ኾነ ገልጦአል፤ (ማቴ. 20፥28፤ ማር. 10፥45) አዎን፤ ከአምላክ በቀር ሰው ስለ ራሱ ነፍስ ቤዛ መኾን (መስጠት) አይችልም፤ (ማቴ. 16፥26)። ቤዛነት ምትክ ኾኖ ከእስራት ነጻ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋ ከኾነ፣ ኢየሱስ ብዙዎች ስለ ኾንነው ስለ ኹላችን ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ከኀጢአትና ከዘላለም ሞት ነጻ ሊያወጣን ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ። አምላክ ለፍጡር እንጂ ፍጡር ለፍጡር ቤዛ መኾን ከቶ አይቻለውም። ኀጢአት ላረከሰው የሰው ልጅ፣ ኀጢአትና ዕድፍ ፈጽሞ የሌለበት የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ያስፈለገው ለዚህ ነው።

ስለዚህ የኀጢአት ክስ ያለበት የትኛውም አዳማዊ ፍጡር መዳን የሚችለው በአንዱ ቤዛ በተሰቀለው መድኃኒት ማመን ሲቻለው ብቻ ነው። እስከ ዛሬ ለበደለ ባሪያ የሞተ ጌታ ወይም አንድ የስስት ልጁን የሰጠ አልሰማንም። ጌታ አብ ግን ልጁን እስኪሰጠን በእዲሁ ፍቅር ወደደን፤ (ዮሐ. 3፥16)፤ ወልድም ገና ደካሞች ሳለን ቤዛ ኾኖ በሞቱ ሊታረቀንና ሊያስታርቀን ወደ እኛ መጣ፤ (ሮሜ 5፥6)፤ እኛ ወደ ርሱ የሚያቀርብ ምንም ነገር ስለሌለንና የሕይወት በራችንን በራሳችን ላይ ስለ ዘጋን ርሱ ወደ እኛ የተዘጋውን በር ከፍቶ መጥቶ ተቤዠን።

ፍቅሩ ከኅሊና መረዳት ከማስተዋልም ይረቃል፤ ተመርቆ የተከፈተውን ሕያውና አዲስ መንገድ የሚያስተዋውቀውና የሞቱን ነገር በልባችን የሚስለውም ጌታ መንፈስ ቅዱስ ድንቅና ፍቅር ነው። አዎን፤ ኢየሱስ መሥዋዕት ኾኖ ባፈሰሰልን ደሙ ቤዛችን ኾነልን፤ ከርሱ በቀርም ማንም፤ ምንም ቤዛ የለንም።

በቤዛችን እንዲህ ተወደናልና ደስ ይበለን፤ አሜን።

ይቀጥላል … 


[1] (ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምዕ. 70 ክ. 1. ቊ.10)

[2] (ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ምዕ. 58 ቊ. 49-50)

[3] አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ 2001 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 243

[4] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ አሳታሚ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር 9ኛ እትም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት።

1 comment: