Sunday, 28 February 2016

ወንድሜ ማን ነው? (የመጨረሻው ክፍል)

ከማይጠፋ ዘር ተወልደን ወንድማማች የሆንበት ምስጢር
     ጌታ ኢየሱስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ የተወለደ ፍጹም ልጅ ነው፡፡ በእርሱ ልጅነት እኛ ደግሞ ልጆች ተብለናል፡፡ በዓመጽና ባለመታዘዝ ፊተኛው አዳም የእግዚአብሔር ልጅነትን ሲያጣ ሁለተኛው አዳም እግዚአብሔር ወልድ እንደልጅ ፍጹም በመታዘዝ (ዕብ.5፥8) ሁላችን ለእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ እርሱ በኵር ሆነ፡፡ እኛ ወደአባቱና ወደእርሱ ክብር የምንገባው የእርሱን “አማኑኤልነት” አብነት አድርገን ነው፡፡ የቀደመው አዳም ከኃጢአት የተነሳ ለሞት ወልዶን ነበርና፡፡
    ከማይጠፋ ዘር ስለመወለድ ወይም ስለዳግም ልደት ስንናገር በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መፈጠርን ወይም ፍጹም መለወጥን የሚያሳይ ነው፡፡ መፈጠር የሚለው ቃል አዲስ ማንነትን ማግኘትን ያሳያል ፤ ከዚህም የተነሣ ከእግዚአብሔር የሆነ የዘላለም ሕይወት ሠርጾ በአማኙ ልብ ውስጥ ይገባል፡፡ (ዮሐ.3፥16 ፤ 2ጴጥ.1፥4 ፤ 1ዮሐ.5፥11) አማኙም በእምነት ጌታ ኢየሱስን ተቀብሎታልና ፍጹም የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል (ዮሐ.1፥12 ፤ ሮሜ.8፥16 ፤ ገላ.3፥26) ፤ አዲስ ሰውነትን (2ቆሮ.5፥17 ፤ ቈላ.3፥9) የዘላለም ሕይወት (1ዮሐ.5፥20) ያገኛል፡፡

Tuesday, 23 February 2016

ኤርትራን ምን ነካት?

  
 ምንም እንኳ ቀን ሰባራ ሆኖ ካርታና ድንበር ቢለያየንም፥ መሳ ለመሳ ሆነን ባንተያይም አንድ ወንዝ አብረን ጠጥተናል ፣ ተጋብተናል ፣ ተዋልደናል ፣ ግማሽ እናቶቻችን እዚያ ግማሽ እናቶቻቸው እዚህ ፣ ግምሽ ወንድሞቻችን እዚያ ግማሽ ወንድሞቻቸው እዚህ ፣ ግማሽ ልጆቻችን እዚያ ግማሽ ልጆቻቸው እዚህ አሉ ፤ የጋራ መልካም እሴቶች ፤ የሃይማኖት አሻራዎች አሉን ፤ ተመሳሳይ መልክና ተመሳሳይ ታሪክ ፤ ተመሳሳይ ድኅነትና ቀና የማያስብልና የሚያሳፍር አስቀያሚ የጦርነት ገጽታዎች አሉን፡፡ ኤርትራውያን ከኢትዮጲያውያን ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ብቻ ሳይሆኑ ምናልባት እንደጀርመን የልዩነት ግንቦቻቸውን አፍርሰው “ወደፊት አንድ ሊሆኑ ከሚችሉ ሕዝቦች መካከል” አንዱ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡

Friday, 19 February 2016

“እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ” (ዮና.3፥10)

   
    ታላቂቱን የአሦርን መናገሻ ከተማ ነነዌን የመሠረተው፥ በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ አዳኝ የነበረው የኩሽ ልጅ ናምሩድ ነው፡፡ (ዘፍጥ.10፥11) የከተሞች መመሥረት የክፋትና የኃጢአት ዝንባሌዎችና ተጽዕኖዎች ሁሉ በአንድነት ለመገኘት ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ መጠንቀቅ ያለብን የከተማ ችግር ሰዎች በብዛት ሆነው በአንድ ላይ በመኖራቸው ምክንያት ሳይሆን፥ በአእስራኤልና በአህዛብ ከተሞች እናይ እንደነበረው የጦርነት ምሽጎችና መሣሪያዎች፥ እንዲሁም ያለእግዚአብሔር ከመኖር ዐመጸኝነትና አለመታዘዝ ማዕከልነት ውስጥ መመንጨቱ ነው፡፡ ነቢዩ አሞጽ፥ “በአዛጦን አዳራሾችና በግብጽ ምድር አዳራሾች አውሩና ፦ በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በመካከልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ በሉ፡፡ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው የሚያከማቹት ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አያውቁም፥  … ” (አሞ.3፥9-10) በማለት በከተማ የሚሠራውን ነገር በግልጥ ያስቀምጣል፡፡

Sunday, 14 February 2016

ቲያንስ - የማይዋደዱትንና ባላንጣዎቹን “አገልጋዮች” እንዴት አፋቀረ?

  
Please read in PDF
 መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሥጋ ከተገለጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዘመን የመጨረሻው ዘመን በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ የጌታን መምጣት ቶሎ እንደሚሆንና የቀረበ መሆኑን ደጋግሞ የሚናገረው፡፡ (ሐዋ.2፥17 ፤ 1ጢሞ.4፥1 ፤ ዕብ.1፥1 ፤ 1ዮሐ.2፥18 ፤ ራእ.1፥1 ፤ 3 ፤ 22፥6-7 ፤ 10 ፤ 20)በዚህ የመሲሑ ዘመን በሆነው በዘመን መጨረሻ ከሚሆኑት ነገሮች አንዱ ገንዘብ የሚያመልኩና የሚያፈቅሩ ሰዎች የሚበዙ መሆናቸውን ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
    የእግዚአብሔር መንፈስ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለዚህ ነው ከዘመናት በፊት ሐዋርያትን አንቅቶ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጽፋቸው የአገልጋይን ዋና መመዘኛ፥ “ራሱን የሚገዛ (1ጢሞ.3፥2 ፤ ቲቶ.1፥8 ፤ 2፥2 … ገንዘብን የማይወድ ፣ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የማይሮጥ(ረብ የማይወድ) [1] (1ጢሞ.3፥3 ፤ 8 ፤ ቲቶ.1፥7) በማለት የጠቀሰው፡፡ ጌታችንም ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ባሠማራበት ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውም ነገር ሁሉ፥ የሚመሰክሩላቸው ሰዎች በሚያደርጉላቸው ልከኛ እርዳታ ላይ ፍጹም መደገፍ እንዳለባቸው እንጂ የራሳቸውን ነገር መያዝ እንደሌለባቸው አስጠንቅቋቸዋል፡፡ (ማቴ.10፥8-11)

Tuesday, 9 February 2016

ክርስቲያን ያልሆኑት ኦርቶክሳውያን ወይስ ምህረተ አብ?! (ክፍል ሁለት)

Please read in PDF
እግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” ማለት ምን ማለት ነው?
    የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን” በዚህ ሥፍራ ተጠቅሷል፡፡ “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” በሚለው ቃል፥ “የእግዚአብሔርም” በሚለው ቃል ውስጥ “ም”፥ ነገር ግን ተብላ ልትጠቀስ ትችላለች፡፡ ምክንያቱም ፍጥረት ገና ሲፈጠር የነበረው ገጽታ አስፈሪና እጅግ ውስብስብ ነበር፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መጥቶ በውኃ ላይ በረበበ ጊዜ ይህ አስፈሪ ገጽታ ተወገደ፡፡ ስለዚህም የምድርን ጥልቅ ሥፍራ ሁሉ ውጦት የነበረው ጨለማ የሥርዓት ባለቤት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ፍጹም በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገላጭ ሃሳብ እንደሆነ እናምናለን፡፡

Monday, 1 February 2016

ደሙን ካንተ ይሻል!


እንሰሳት አራዊት ፤
አዋቂ ሕጻናት ፤
ምድር ተገልብጣ ፣ ልትተኮስ በʼሳት ፤
አመድ ብናኝ ልትሆን ፣ በፍህም ቀጠሮ ፤
ደስታዋ ሊሰበር ፣ በዋይታና ሮሮ …

Thursday, 28 January 2016

“በኦርጋን ልንዘምር ይገባል ፤ አይገባም” ከሚለው ክርክር ጀርባ ...


       የቤተክርስቲያንን ታሪክ እንደምናጠናው ቤተክርስቲያን እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ የአላውያን ነገሥታትን ስደትና መከራ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ድል አድራጊነት የተወጣችውን ያህል፥ የተድላውን ዘመን ማለፍ ሲሳናት አስተውለናል፡፡ ለምሳሌ ያህል፦ የመካከለኛው ዘመን በሚባለው ከ590-1517 ዓ.ም [1] ከብዙው መካከል በዋናነት ሁለት አስነዋሪና ዘግናኝ ስህተቶችንእ ናስተውላለን፡፡

Monday, 25 January 2016

“Qottoon hidda mukaa hundumaa irra kaa'amee jira;”(Maate.3፥10)




     Jecha kana kan dubbate Yohannis Cuuphaa dha. Kan dubbatees Fariisotaa fi Saduuqota laga Yordaanositti cuuphamuudhaaf gara isaatti dhufan erga argee booda dha. Yohannis cuuphaan “Mootumman waaqaa dhi’aateeraatii yaada garaa keessanii geedaradhaa!” jedhee jecha raajicha Isaayaas kaasuudhaan yeroo mootummaa Waaqayyoo labsuu; warri Yeerusalem jiraatan, warri Yihuuda, warri kutaa biyya naanna’aa Yoordanoositti jiraatan hundi gara isaatti dhuufuun cuuphamaYohannis cubbuu isaani himachaa ofii isaanii cuphsiisaa turan.
    CuuphaanYohannis jiruu fi umrii isaa guututti Waaqayyoof kan kennee waan ta’eef mootummaa waaqaa labsuu malee hojii biro hinqabu ture. Kanas kan labsaa ture soda tokko malee dha.Namootni isa bira dhufaa turan uummata hedduu, namoota qaraxa guuran, warri looltuuni fi… kaneen biros isa bira dhufanii “mee maal goodhu qabna?” yeroo jedhani gaafatan; hunda isaaniitiif waan isaan irraa eegamuu sirritti itti himaa ture. Yeroo ammaa kana keessatti rakkoon dhugaa mootummaa waaqaa ifatti fi sirritti barsiisuu(labsuu) dhabuu dha. Waldaaleen hedduun miseensoonni isaani cubbuu keessatti akka argamanitti himuu dhiisanii waljajanii qofa wajjiin jiraatu. Waaqayyoon garuu yaada namaa fi garaa namaa ni fonqolcha ykn sakkata’a.(Mula.2:23)

Monday, 18 January 2016

መንፈስ ቅዱስ በጥምቀቱ በኢየሱስ ላይ ለምን ወረደ?


እንኳን ለጌታችን ጥምቀት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡
    ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ያለወንድ ዘር ፤ ከሴት ዘር  ተወለደ፡፡ (ሉቃ.1፥31 ፤ 2፥6-7) እርሱ በኃጢአት ከወደቀውና በበደሉ ምክንያት ዘሩ ካደፈው አዳም ሳይሆን እኛን ከወንድ ዘር ያይደለ ፤ ከማይጠፋ ዘር ሊወልደን (ዮሐ.1፥13 ፤ 1ጴጥ.1፥23) በልዩና ፍጹም ቅዱስ በሆነ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ተወለደልን፡፡
    ጌታችን ከተወለደ በኋላ በአሥራ ሁለት አመቱ ወደኢየሩሳሌም ለበዓል ወጥቶ ከኢየሩሳሌም ሲመለስ፥ “ … ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር።” (ሉቃ.2፥51) ከሚለው በቀር እስከሠላሳ አመቱ ምን ይሠራ እንደነበርና የት እንደቆየ መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ብሏል፡፡ ሠላሳ አመት በሆነው ጊዜ ግን ሊጠመቅና ይፋዊ አገልግሎት ሊጀምር ወደዮርዳኖስ መጣ፡፡ ኦሪት “አንድ ሰው ሙሉ ሰው ነው ፤ ይፋዊ አገልግሎት ሊያገለግል ይገባል” ብላ “ፈቃድ የምትሰጠው” በሠላሳ አመቱ ነውና፡፡ (ዘኍል.4፥47)

Tuesday, 12 January 2016

ወንድሜ ማን ነው? (ክፍል ሦስት)




                                     ዮሴፍና የአባቱ ልጆች ተገናኙ፤

     ምድር ሁሉ በረሃብ በተያዘችበት ዘመን እግዚአብሔር ዮሴፍን በግብጽ ምድር ሀገረ ገዢ አድርጐ፥ ጥበብን ሰጥቶ እህልን አከማቸ፡፡ ያዕቆብ በግብጽ እህል እንዳለ ሲሰማ፥ (ዘፍጥ.42፥1) ልጆቹን ወደዚያ ላከ፡፡ ብንያም ከቤት ቀርቶ አሥሩ “ወንድሞች” ተነስተው ወደግብጽ ወረዱ፡፡ እግዚአብሔር በጊዜው ሊሠራ፥ እነርሱ ከእግዚአብሔር ሃሳብ “ገፋንህ” ብለው ዮሴፍን ወደክብር ሰገነቱ እያስቸኮሉ አቀረቡት፡፡
     ግብጽ ሲደርሱ ሰገዱለት ፤ የዮሴፍ ሕልም ተፈጸመ፡፡ እርሱ አወቃቸው እነርሱ አላወቁትም፡፡ አውቆም ተለወጠባቸው ፤ እነርሱ ግን ለጠየቃቸው ጥያቄ በብዙ መሃላ ሊያስረዱት ፈለጉ፡፡ ሐሰተኞች ሆነው እውነተኞች ነን አሉ ፤ ከፊታቸው ያለውንና ቆሞ የሚያወራቸውን ወንድማቸውን ጠፍቷል ብለው ተናገሩ፡፡ (ዘፍጥ.42፥13)

Tuesday, 5 January 2016

“ …ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴ.1፥21)


Please raed in PDF

እንኳን ለበዓለ ልደቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ አሜን፡፡
      ለሁለት ሺህ ዓመታት ያልተዘነጋ ፤ ለአንድም ቀን ሳይነሳ የተዋለበት ቀን የሌለ ድንቅ ስም፤ ክርክር ፣ ሙግት ፣ ክህደት ፣ ፍልስፍና ፣ ነቀፋ ፣ ስድብ ፣ ትችት ፣ መሸቃቀጥን ድል ነስቶ ያሸነፈ ፤ ነቢያት ሊሰሙትና ሊያዩት የወደዱት፣ መላዕክት በምስጋና ያደነቁት ግሩም ስም ፤ ባለፈው ፣ ባለውና ገና በሚመጣው ትውልድ ተወዶ ያልተጠገበ ስም ቢኖር ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
    ኢየሱስ የሚለው ቃል “የሹዋ” ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል አቻ የግሪክ መጠሪያ ስም ሲሆን፥ ትርጉሙም “እግዚአብሔር ያድናል ፤ እግዚአብሔር ድኅነት ነው” ማለት ነው፡፡ በሌላ ንግግር ኢየሱስ በግሪኩ ሲሆን በዕብራይስጡ ኢያሱ ነው፡፡ ትርጉሙም አንድ ነው፡

Wednesday, 30 December 2015

ሕይወት አልተስማማም!


ክፋትን በክፋት ፣ እያጠፉ መኖር
ርኩሰትን በርኩሰት ፣ እያጠፉ ማሴር

Thursday, 24 December 2015

ክርስቲያን ያልሆኑት ኦርቶክሳውያን ወይስ ምህረተ አብ?! (ክፍል አንድ)




     ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” (2ጢሞ.3፥16) የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትንም ሆነ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን መንፈስ ቅዱስ ለእኛ የሰጠው፥ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እናምን ዘንድ፥ አምነንም በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ” ነው፡፡ (ዮሐ.20፥30-31)
      የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንድና አንድ ፤ ግልጽና ግልጽ እንጂ ስውርና ውስብስብ ፣ ለሰዎች እንዳይገባና እንዳይረዱት ተደርጎ የተጻፈ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅን የማዳን ተስፋና ተስፋው በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ፤ መሞትና መነሳት የተፈጸመ መሆኑን በማስረዳት ይህን መዳን የምሥራች ብለን ለፍጥረት ሁሉ በድፍረት ከመንፈስ ቅዱስ ጉልበት የተነሳ እንድንናገር እንጂ ሌላ ስውር አጀንዳ የለውም፡፡ ጌታችን የመምጣቱን ምስጢር ራሱ ሲናገር፥ “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” (ዮሐ.10፥10) ሲል ፤ ደቀ መዛሙርቱም ፤ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው” (1ጢሞ.1፥15)  በማለት መሰከሩ፡፡ ለቤተ ክርስቲያንም የተሰጠው ትልቁ ተልእኮና አደራ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል አለም አቀፍ ጥሪና ሰፊ የመከር ሥራ ነው፡፡ (ማቴ.28፥19)

Friday, 18 December 2015

ግጭትና ጦርነት የማያስተምራት አገር



ስለራሳችን እንዲህ እንናገራለን ፦
-      እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች ነን ፤
-      ብዙ ብሔር ብሔረሶችና ሕዝቦች ተዋደው የሚኖሩባት አገር አለን ፤
-      ለቁጥር የሚታክት “ክርስቲያን” ፣ እልፍ አዕላፍ ገዳም ፣ መድረክ የሚያጨናንቁ አገልጋይ ጳጳሳት ፣ ካህናት ፣ ዲያቆናትና ዘማርያን አሉን ፤
-      ከእኛ ወዲህ ማን አለ አማኝ? ከእኛ በላይ ጸዳቂ ፤ ታማኝ አገር ወዳድ ወዴት አለ?! …
ስንታይ ግን፦
-      “ባዕድ እንግዳ” ለመቀበል ሆዳችንን እንደአገር ስናሰፋ ፥ ከጎረቤትና ከወገናችን ጋር ግን “ጠብ ያለሽ በዳቦ” በሚል መንፈስ የተያዝን ፤
-      አገልጋዮቻችን ጸንሰው ወልደው ፣ አሳድገው የሰጡን አንዱ መልክ ዘረኝነትና ልዩነት ነው ፤
-      ከእኛ በላይ ሁሌም ሰው የለም ብንልም ዘወትር ግን እየኖርን ያለነው ከሰው በታች ጅራት ሆነን ነው …
     ሰሞኑን በከፊል የአገራችን ክፍል ብጥብጥና ሁከት ፤ ደም ማፍሰስና ግድያ ነግሶ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ አድራጊው ሌላ ወራሪ ወይም እንግዳ አሸባሪ መጥቶብን አይደለም ፤ ሟችም እኛው፥ ገዳይም ያው እኛው ኢትዮጲያውያን ፤ ንብረት አውዳሚም፥ ንብረት የሚወድምበትም ያው የአንድ አገር ዜጎች ፤ የአንድ ርስት ወሰንተኞች ፤ የአንድ ወንዝ ጠጪዎች እኛው ነን፡፡
      እስኪ አስተውሉ፥ አንድ መቶ ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በእኛና እኛ መካከል የተደረጉ ጦርነቶችን ብናነሳ፦ በ1909 ዓ.ም በራስ ተፈሪና በንጉሥ ሚካኤል መካከል በሰገሌ ፣ በ1922 ዓ.ም በራስ ተፈሪና በራስ ጕግሳ በአንቺም ወይም በበጌምድር ፣ ከ1966-1983 ዓ.ም ወታደራዊው መንግሥት ደርግና ኢሕአዴግ በተለያየ ቦታ ያደረጉት አስቀያሚ ጦርነት ፣ በ1994 ዓ.ም ሁለቱ “ወንድማማች” ኢትዮጲያና ኤርትራ ያደረጉትን ጦርነት (ወታደራዊው መንግሥት በአንድ ጉድጓድ የፈጃቸው የንጉሡ ዘመን መሪዎችና ሌሎችም ሳይካተቱ) ይህን ሁሉ ስናነሳ ምን ይታወሰናል?!

Tuesday, 15 December 2015

ቃሉ የሚለው፥ “ከቶ አላወቅኋችሁም ፤” ነው!

     

   በመጽሐፍ ቅዱስ በአገባቡ ወይም እንደተጻፈው ከማይነበቡ ጥቅሶች መካከል አንዱ፦ “ … ከቶ አላወቅኋችሁም ፤ እናንተ ዓመፀኞች ፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” (ማቴ.7፥23) በማለት የተጻፈልን ቃል ነው፡፡ ይህ ክፍልና ሌሎችም ከዚሁ ጋር የተያያዙም ንባባት ለአፈጻጸም ከፍ ያለ የሥነ ምግባርና የፍጽምናን መንገድ ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙዎች የተራራው ትምህርት ተብለው የሚታመኑትን ቃላት ማንም ሰው መፈጸም እንደማይቻለው ያስተምራሉ፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔርን ማናቸውንም ሥራ በእግዚአብሔር ጉልበት ፤ ራሱ እግዚአብሔርንም መማር የሚቻለን በራሱ በእግዚአብሔር ዕውቀት ገላጭነትና የጥበብ አስተማሪነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የተራራውን ትምህርት በራሱ በእግዚአብሔር ጉልበትና መንፈስ መፈጸም ይቻለናል ማለት እንጂ ፈጽሞ መፈጸም አይቻልም ማለት አይደለም፡፡
     ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ትምህርቱ ያስተማራቸው ትምህርቶቹ በብዙዎች ዘንድ እጅግ የተደነቁና የሚያስደምሙ ትምህርቶች ናቸው፡፡ እውነትም! የእግዚአብሔር አምላካችን መንገድና ሕጉ ፤ ሥራውም ፍጹም ነውና (ዘዳግ.25፥15 ፤ መዝ.18፥30 ፤19፥7) ፤ እኛም በእርሱ ዘንድ (ዘዳግ.18፥13) ፤ እንደእርሱም ፍጹማን እንሆን ዘንድ ተጠርተናል፡፡ (ዘፍጥ.17፥1 ፤ ማቴ.5፥48 ፤ 19፥21) አዎን! የእግዚአብሔር ቅዱሳንም በፊቱ ያለነውርና ነቀፋ ነበሩ፡፡ (ዘፍጥ.6፥9 ፤ 1ነገ.11፥4 ፤ ኢዮ.1፥1 ፤ ሉቃ.1፥6 ፤ 2፥25) ፍጽምና ወይም በእግዚአብሔር ፊት የበቃ ሆኖ መገኘት ለሰው የሚቻል ነገር አይደለም (ሮሜ.3፥11 ፤ 2ቆሮ.3፥5) ስለዚህም ስለፍጽምናና ቅድስና ስናስብ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል በተሰጠን ጸጋ እንጂ (ሮሜ.3፥21-24) በሕግ ወይም በራሳችን የምናደርገውም ፤ እናደርገውም ዘንድ የሚገባን አንዳችም ነገር የለም፡፡