Tuesday, 30 September 2014

ሞት ደጅ ደጄን እያየ …


                          Please read in PDF              
                                     
ደምህ ነው ህይወቴ ፣ መከራህ ጉልበቴ፤
ህማምህ ድጋፌ ፣ መድከምህ ብቃቴ፤

Thursday, 25 September 2014

የመስቀሉ ቃል


                                   

                                 
      የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ አህዝብ ሞኝነት፤ ለአይሁድም ማሰናከያ ነው፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የመስቀሉን ቃል  በእንጨት ላይ መዋልና መሰቀልን እንደተረገመ ስለሚቆጥሩት ነው፡፡(ዘዳግ.21፥23 ፤ ገላ.3፥13) ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሰቀሉ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ … ” እንደኃጢአተኛ የተቆጠረ ሆነ፡፡(2ቆሮ.5፥21) ለግሪክ ሰዎች ደግሞ በእንጨት ላይ መሰቀል የአማልክትን ክብርና ልዕልና ዝቅ የሚያደርግና እንደድኩም የሚያስቆጥር ስለሆነ ፈጽሞ አይቀበሉትም፡፡
      ቀድሞ የጥንት ፋርሶች በኋላም ሮማውያን አንድን ወንጀለኛ በመስቀል ላይ በመስቀል የሚቀጡት “ኦርዝሙድ” የተባለ የመሬት አምላካቸው እንዳይረክስባቸው በመጠንቀቅና ለአማልክታቸው ክብርን ለመስጠት በማሰብ ነበር፡፡(አባ ጐርጐርዮስ(ሊቀ ጳጳስ)፤ የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 3ኛ ዕትም፤ 1991፤ አዲስ አበባ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ.104)

Monday, 22 September 2014

ሦስቱ ባህታውያን(የመጨረሻ ክፍል)


                                            Please read in PDF
      
     ነገር ግን ሁለተኛው ባህታዊ ቃላቶቹን አቀላቅለው አሳስተው ተናገሩ፡፡ ራቁታቸውን ያሉት ረዥሙ ባህታዊም አጣርተው አልደገሙትም፡፡ ጢማቸው አፋቸውን ሸፍኖት ስለነበር የተጣራ ድምፅ ሊያወጡ አልቻሉም፡፡ ጥንታዊው ደግሞ ጥርሶቻቸው ስለረገፉ በግልጽ የማይሰማ ነገር ነው ያጉተመተሙት፡፡
   አቡኑ እንደገና ደገሙላቸው፡፡ ባህታውያኑም እንደገና ደገሙት፡፡ አቡኑ በትንሽ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ባህታውያኑም በአጠገባቸው ቆመው አፍ አፋቸውን አፍጠው እየተመለከቱ የሚሏቸውን ይደግሙላቸው ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ እስከአመሻሽ ድረስ ሊያስተምሯቸው ደከሙ፡፡ አንዲቷን ቃል አስር፣ ሃያ፣ መቶ ጊዜ እየመላለሱ አስጠኗቸው፡፡ ቃላት እየተቀለቀሉባቸው ሲቸገሩ ያርሟቸውና እንደገና ከመነሻው ያስጀምሯቸዋል፡፡
     የጌታን ጸሎት ሙሉ ለሙሉ እስከሚያስተምሯቸው ድረስ አቡኑ ከባህታውያኑ ዘንድ ቆዩ፡፡ በመጨረሻም ያለ አቡኑ ድጋፍ እያንዳንዳቸው በራሳቸው ሙሉ ጸሎቱን ወረዱት፡፡
    አቡኑ ወደ መርከቡ ሊመለሱ ሲነሱ ጨለማው እየከበደ ከባህሩም ጨረቃ እየወጣች ነበር፡፡ ባህታውያኑን ሲሰናበቱ ሁሉም እስከመሬት አጐንብሰው ሸኟቸው፡፡ እሳቸውም እያንዳንዳቸውን ካጐነበሱበት ቀና እያደረጉና እያቀፏቸው ባስተማሯቸው መሠረት እንዲጸልዩ ካዘዟቸው በኋላ ወደ ጀልባዋ ገቡ፡፡

Friday, 19 September 2014

ሦስቱ ባህታውያን (ክፍል - ሁለት)

    
        Please read in PDF

       አቡኑ ከመርከቢቷ የፊት ጫፍ ላይ ወንበር ቀርቦላቸው ሲቀመጡ ሌሎቹም ሁሉ መጥተው ወደ ትንሿ ደሴት መመልከታቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥሩ የማየት ችሎታ ያላቸው ሰዎች በደሴቷ ላይ የሚገኙትን አለቶችና የጭቃ ጎጆዋንም ማየት ችለው ነበር፡፡ ከመሃላቸው አንዱ ሦስቱን ባህታውያን ጭምር መለየት ችሎ ነበር፡፡ ካፒቴኑ አጉሊ መነጽር አምጥቶ ከተመለከተ በኋላ ለአቡኑ እየሰጣቸው፦
   “ትክክል ነው፡፡ ከባህሩ ጠረፍ ላይ ከትልቁ አለት እንዲህ ወደ ቀኝ ሲሉ ሦስቱ ባህታውያን ቆመው ይታያሉ፡፡” አለ፡፡
    አቡኑ በመነጽር ተመለከቱ፡፡ ወደትክክለኛው አቅጣጫም አዞሩት፡፡ የተባለው እውነት ነው፡፡ ሦስቱም እዚያው ቆመዋል፡፡ አንደኛው ረዥም ሌላኛው ትንሽ አጠር የሚሉና ሦስተኛው ደቃቃ ትንሽ፡፡ ሦስቱም ከባህሩ ጠረፍ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመው ነበር፡፡

Monday, 15 September 2014

ሦስቱ ባህታውያን (ክፍል አንድ)



አጭር ልብወለድ
(ምንጭ ብሪቱ መጽሔት ጥር - የካቲት 1991)
(ደራሲ፦ ሊዎ ቶልስቶይ)
(ተርጓሚ፦ ሁነኛው ጥላሁን)

“አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።” (ማቴ.6፥7-8)

     አቡኑ ከአርካንጌልስክ ከተማ ወደ ሶሎቬትስኪ ደሴት በመርከብ እየተጓዙ ነበር፡፡ ቅዱሱን ሥፍራ ለመሳለም የሚሄዱ ምዕመናንም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ የነፋሱ አቅጣጫ አመቺ፣ አየሩም ማለፊያ ነበረ፡፡ ባህሩም ጸጥ ብሏል፡፡ ምእመናኑ ገሚሱ ጋደም ብለው ከፊሉም ከያዙት ስንቅ እየቀማመሱ የተቀሩትም በቡድን በቡድን ተቀምጠው እርስ በእርስ ያወራሉ፡፡ አቡኑ ከነበሩበት ተነስተው ወደ መርከቡ መተላለፊያ መራመድ  ጀመሩና ወደጫፉ ሲቃረቡ ሰብሰብ ያሉትን ሰዎች አዩዋቸው፡፡ አንድ ባላገር ወደባህሩ እያመለከተ አንድ ነገር እያሳያቸው ሲናገር ሰዎቹ ያዳምጡት ነበር፡፡ አቡኑ ቆም ብለው ባላገሩ ወደሚያመለክትበት በኩል ተመለከቱ፡፡ በፀሐይ ከሚያብረቀርቀው ባህር በስተቀር ምንም የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡ ወደሰዎቹም ጠጋ ብለው ባላገሩ የሚለውን ማዳመጥ ጀመሩ፡፡ ባላገሩ አቡኑን እንዳየ ባርኔጣውን በማውለቅ ንግግሩን አቋርጦ ፀጥ አለ፡፡ የሚያዳምጡትም ሰዎች ባርኔጣዎቻቸውን በማንሳት በአክብሮት ተቀበሏቸው፡፡
    “በመምጣቴ አትጨነቁ ወዳጆቼ” አሉ አቡኑ፡፡ ወደባላገሩም ፊታቸውን አዙረው “የመጣሁት አንተ የምትነግራቸውን ለመስማት ብዬ ነው” አሉት፡፡

Tuesday, 9 September 2014

የተወደደችው የጌታ አመት (ሉቃ.4፥19)



እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም በፍቅር አሸጋገራችሁ!!!

    ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለማቋረጥ ከብዙ ህዝብ ጋር ለአምልኰ በመገኘት ለተከታዮቹ ደቀ መዛሙርት የሚደነቅ ምሳሌ የሚሆን ልምድ አለው፡፡(ማቴ.13፥54፤ ማር.1፥21፤ ሉቃ.4፥16፤ ዮሐ.7፥14) ጌታ ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር ዘወትር “መሰብሰብን ባለመተው” ለደቀ መዛሙርቱ አብነት ሆኗል፡፡(ዕብ.10፥24) ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት፤ ቃሉን ለመመርመርና ለማስተማር መሆንን ጌታ በእውነት እኛንም አስተምሮናል፡፡ ናዝሬት ጌታን ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆንም እርሱ ግን ወዳደገባትና ወደሚያውቃት ከተማ ምኩራብ መጥቶ አስተማረ፡፡ ዕድገታችንን፣ ማንነታችንን፣ ገመናችንን፣ ልጅነታችንንና፣ ውድቀታችንን … ምናልባትም “ልካችንን” በሚያውቁን ሰዎች ፊት ማገልገል ከባድ ህመም ይኖርበት ይሆናል፤ ጌታ ግን አድርጎታልና ልጆቹ በህይወቱ ልንታዘዝ፤ ህይወቱም ሊያስተምረን ይገባል፡፡
    ጌታ  ወደምኩራብ በገባ ጊዜ የኢሳይያስን ትንቢት ጥቅልል አንስተው ሰጡት፡፡ እርሱም ተነስቶ መጽሐፉን በመተርተር ማንበብ ጀመረ፡፡ አይሁድ ምንም እንኳ ወደ ተስፋው ፍጻሜ ባይደርሱም፤ የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ብቻ ሳይሆን መጻህፍትን በመቅደሱና በየምኩራቦቻቸው በአግባቡ የማስቀመጥ ልማድ ነበራቸው፡፡ በምኩራባቸው የእግዚአብሔር ቃል ጥቅልል ትልቁንና የመጨረሻውን ሥፍራ በክብር ይይዛል፡፡ ትልቅና የመጨረሻው አምልኰ ለእግዚአብሔር ቃልና ላስተማረን ትምህርቱ ልዩ ክብርን በመስጠት መታዘዝ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ቤት “መጻህፍት መደርደርያ” የተመሉት በልቦለድና በፍልስፍና “ጥቅልል ጽሁፎች” ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቃል ቸል በማለት ለሌሎች “ፍጡራን ጥቅልሎች” ትልቅ ክብርና ሥፍራ የሰጠ ትውልድ ይህ የእኛ ዘመን ትውልድ ነው ብል ያልተጋነነ እውነት ነው፡፡

Tuesday, 2 September 2014

ማስተስረያውን ክዶ


                               Please Read in PDF 


ሳይጐድል ደምግባቱ፣ አምሮ እንደደመቀ፤
ትኩስ ሥጋነቱ፣ ግሎ እንደሞቀ፤
ሸጋ ቆንጆነቱ፣ ጉድ አጀብ አስብሎ፤
ከደሙ ቤዛነት፣ ከ‘ርሱ ተነጥሎ፤

Thursday, 28 August 2014

የመቶ አለቆቹ (የመጨረሻ ክፍል)





4. የመቶ አለቃው ዩልዮስ (ሐዋ.27፥43)

“የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ … ”
      ቅዱስ ጳውሎስ ለቁጥር በሚታክቱና ምላሳቸው በሳለ ከሳሾች መካከል “እየተብጠለጠለ” ቅንጣት ታህል አለመፍራቱን ሳስብ የጌታ ኢየሱስ “ … አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና፡፡” የሚለው የትንቢት ቃል መፈጸሙን ትዝ ይለኝና ልቤ ይረካል፡፡(ማቴ.10፥19-21) የእስያ አይሁድ፣ የኢየሩሳሌም አይሁድ፣ ጠርጠሉስ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ … ስለእርሱ በጎነት የላቸውም፡፡ ፊስጦስም እንደቀደሙት ባዕለ ሥልጣናት ክፉ ልማድ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲዳኝ ይጐተጉተዋል፡፡(ሐዋ.25፥9፤21)
        ቅዱስ ጳውሎስ ነገሩ እንዳላማረ፤ ፊስጦስ ራሱ ወደአይሁድ እንዳደላ ያወቀ ይመስላል፡፡ አሁን በቆመበት የሮማ የፍርድ ችሎት ፊት መዳኘት እንደሚፈልግ በጽናት ተናገረ፡፡ ምክንያቱም በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቢዳኝ የልባቸውን ክፋት ያውቀዋል፡፡ ይገድሉታልና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለሌለው ሞት ራሱን አሳልፎ አልሰጠም፡፡(ዮሐ.8፥59) ጳውሎስ “ሰማዕትነት አያምልጠኝ” ብሎ ለስንፍና ሞት ሳይሸነፍ ወደቄሳር ይግባኝ በማለት በሮማዊ ዜግነቱ የተሰጠው መብቱን ተጠቀመበት፡፡(ሐዋ.25፥11)

Monday, 25 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል አራት)



የሮማ መቶ አለቆች
3.2. በሰፈሩ ውስጥ(ሐዋ.23፥10)

       ቅዱስ ጳውሎስ ከመገረፍና ጭካኔ ከተመላበት ድብደባ በኢየሱስ መንፈስና ብርታት፤ በየመቶ አለቃውም ቅንነት ተርፏል፡፡ በማግስቱ ሻለቃው አይሁድ እርሱን የከሰሱበትን እርግጡን ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቦ ከፈታው በኋላ፤ ሸንጎውንና የካህናት አለቆችን እንዲሰበስቡ አዞ፤ ጳውሎስን በፊታቸው አቆመው፡፡ የአይሁድ ሸንጎ እንዲሰበሰቡ የተፈለገበት ምክንያት ሻለቃው የጳውሎስን ጥፋት ማወቅ ስለተሳነው የእርሱ ወገኖች እንዲያጣሩ ነበር፡፡ ግን ዳኝነቱ ቀድሞ በአድሎአዊነት አጋድሏል፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስ በሸንጎው ፊት በቆመ ጊዜ ሁለት የማይስማሙ ወገኖች ጳውሎስን ለመክሰስ ግን ተስማምተው ቆሙ፡፡ ሁል ጊዜ ይደንቀኛል፡፡ የጌታ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለመግደል፤ ለማሳደድ፤ ለመክሰስ ሁለት ፈጽሞ የማይስማሙ አካላት ይፋቀራሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በሁለት ፍጹም ተቃራኒ የእምነት አካላት የተከሰሱ አማኞችን የአለማዊ ፍርድ ቤት ችሎት እየደነቀው የማየት ዕድል አጋጥሞታል፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን አብረው ለመኖር አይስማሙም፣ ይበላላሉ፤ ክርስቶስ ኢየሱስንና እንደጳውሎስ ያሉ አማኞችን ግን ለመክሰስ ከባልና ሚስት ይልቅ ይዋሃዳሉ፡፡

Thursday, 21 August 2014

በድንግል ማርያም ላይ የአይሁድ አሽሙር (የመጨረሻ ክፍል)



     አረጋዊው ቅዱስ ስምዖን የናዝሬቱን ህጻን ኢየሱስን ለግዝረት ወደቤተ መቅደስ በእናቱ ክንድ ታቅፎ በወጣ ጊዜ፤  ህጻኑን  ከእናቱ ክንድ ተቀብሎ የደስታና የሚያስጨንቅ ትንቢት ለህጻኑና ለእናቲቱ ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ፦   “እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት።”(ሉቃ.2፥35) እመቤታችን ጥልቅ የመከራ ሥቃይ እንደምትቀበል የሚያመለክትና፤ ኢየሱስ ገና በስምንተኛ ቀኑ ሊሞት እንዳለው ለመጀመርያ ጊዜ ተነገረለት፡፡
     በራስ የሚደርስን መከራንና ስቃይን ገና በልጅነት መስማት ከማስደንገጥ አልፎ ያሰቅቃል፡፡ ድንግል ማርያም በነፍሷ ሰይፍ ማለፍ የጀመረው ጌታን መጽነሷ ከታወቀባት ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ ከኤልሳቤጥ ዘንድ ወደናዝሬት ከመጣች በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የጌታ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ከድንግል ማርያም መወለድ ሲያስተምር በነበረበት ዘመኑ እንኳ አልተቀበሉትምና፡፡
      ጌታ “አባታችን አብርሃም ነው” ብለው በባዶ ትምክህት የሚመኩትን አይሁድ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር፡፡ … እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ ዲያብሎስ የሚያደደርገውን ነው” (ዮሐ.8፥38፤44) ባላቸው ጊዜ የመለሱት መልስ የአሽሙር ስድብ ነበር፡፡

Monday, 18 August 2014

“ … እርሱን ስሙት” (ማቴ.17፥5)



እንኳን ለደብረ ታቦር መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!



    ቃሉን የተናገረው አብ ነው፤ የተነገረለት ደግሞ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ … የሰው ልጅ “ምን እንደሚሰማ እዝነ ልቡናውን አለመጠበቁ” (ማር.4፥24) የህይወት ዘመኑን በጭንቅ እንዲጓዝ፤ ፈቃዱም ከፈጣሪው ይልቅ ወደፍጡር እንዲያዘነብል፤ ሊሰማ የሚገባውን የበላዩን ጌታ ትቶ ከጎን ያለችውን “ወዳጅ ሚስቱን” መስማቱም ማንነቱን ድካም፤ እሾህና አሜኬላ ደግሞ ዙርያውን ለመከበቡ ምክንያት ሆኗል፡፡(ዘፍ.3፥10-21)
     አዳም ሁሉን አዋቂውንና ሰምቶ ከመመለስ ቸል የማይለውን ጌታ አለመስማቱ፥ ለማይሰማውና በጭካኔ ለተሞላው ለሰይጣን አገዛዝ ማንነቱንና ነጻነቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የእስራኤል ልጆች ወደእግዚአብሔር እረፍት ያልገቡት ጌታ እግዚአብሔር በድምፁና በሙሴ አማካይነት እየተናገራቸው ከመስማት ይልቅ “እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም?”(ዘጸ.17፥7)፤ “ … ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው የሚጠጣም ውኃ የለበትም።”(ዘኅ.20፥5-6) ብለው ፍጹም ድምጹን እየሰሙ እግዚአብሔርን በአመጻ ቃል በማስመረራቸውና አልታዘዝ በሚል ልብ በመከራከራቸው ነው፡፡(ዕብ.3፥7)

Saturday, 16 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል ሦስት)




3. የሮም መቶ አለቆች
3.1. በማረፊያው ሥፍራ (ሐዋ.22፥24)
     ቅዱስ ጳውሎስ ወደኢየሩሳሌም ጉዞ ከመጀመሩ በፊት የተነገረበት ትንቢት አስጨናቂ ነው፡፡(ሐዋ.21፥10-14) እንደሚገረፍና ለአህዛብ ተላልፎ እንደሚሠጥ ቢያውቅም፤ ጨክኖ ወደኢየሩሳሌም እየወጣ፦ ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን “ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ ቅዱሳንን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ ጸልዩ።”(ሮሜ.15፥33) በማለት እንዲጸልዩለት ያሳስባል፡፡ ጸሎቱና ጸሎታቸው ተሰምቶ “ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።” ብሎ ጸሐፊው ያስረግጠዋል፡፡(ሐዋ.21፥17)
   ሐዋርያው በኢየሩሳሌም የሚታወቀው “የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና በመዛቱ፤ በቅዱሳንም ላይ ብዙ ክፉ በማድረጉ”ና (ሐዋ.9፥1፤13) ለኦሪት ህግ እጅግ በመቅናቱ ነው፡፡ አሁን ግን ታሪክ ተለውጦ ያሳድድ በነበረው በዚያ ነገር መሰደድ ጀምሯል፡፡ ብዙዎች ወደኢየሩሳሌም እንዳይሄድ አብዝተው የለመኑት ስለዚህ ነገር ነው፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ግን ለእስራት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌምም እንኳ እንዲሞት ልቡን አስጨከነ፡፡ አገልግሎት ሰዎች ባዩልን አልጋ በአልጋ በሚመስለው ይቀናችኋል ቢሉንም ጌታ ባየልን በእሾሁና በጐርባጣው መንገድ በደስታ የሚቀበሉ እጆችን ያሰናዳል፡፡ ምስክርነትና ንስሐ በተካደበትና በተበደለበት መንገድ ሲሆን ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡ በግልጥ ያሳደደውን ጌታን ባሳደደባትና ብዙዎችን በበደለባት ከተማ ቅዱስ ጳውሎስ በዚያች ከተማ ተገኝቶ ታላቅ ምስክርነትን መሰከረ፡፡ በአደባባይ ያሳደደው በአደባባይ ተሰደደ፡፡ ዛሬ ግን በዘፈን፣ በከህደት ትምህታቸው፣ በፖለቲካ … መርዝ ብዙውን ህዝብ በአደባባይ የበደሉ ንስሐቸውን በጓሮ መጨረሳቸውን ከየት እንደተማሩት ግራ ይገባል፡፡ እውነተኛ ንስሐና ምስክርነት በተሠራበት በዚያው መንገድ ቢሆን ብዙ ምህረት ከጌታ በሆነችልን ነበር፡፡

Wednesday, 13 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል ሁለት)



ፈጣን ጉዞ ወደ ተራራማው የኤፍሬም አገር
   
    ድንግል ማርያም “እንደቃልህ ይሁንልኝ” ባለች ጊዜ እንደመንፈስ ቅዱስ አሠራር ህጻኑ በማህፀኗ ተፀንሷል፡፡ ይህ ነገር ከሆነ በኋላ ሳትቆይ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ወደዘካርያስ ቤት ተጓዘች፡፡ ከመልአኩ አንደበት የሠማችው የኤልሳቤጥ መፅነስ ሳያስደምማት አይቀርም፡፡ በእርግጥም ዝጉ ማህፀን ሲከፈት፤ አይቻልም የተባለው ሲቻል፤ አይሆንም ተብሎ የተደመደመው ሆኖ ሲታይ በእርግጥ ያስደምማል፡፡ ደስታ የበዛላቸው በአንድ ተገናኙ፡፡ “አንዱ ለአንዱ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” እያሉ ሊያወሩ፡፡ አዎ! ሠላምታቸው እንኳ ለእግዚአብሔርን ክብርና አምልኮን በመስጠት የደመቀና የሚማርክም ነው፡፡

Friday, 8 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል አንድ)




    
እመቤታችን ድንግል ማርያም በጌታ ያመነች ብጽዕት ናት፡፡(ሉቃ.1፥45) ከዳዊት ቤት ወገን የምትሆን ድንግል ብላቴና(ኢሳ.7፥13) ዕድሜዋ ወጣት፣ የገሊላ ናዝሬት ወደምትሆን … “ብዙ ገሊላ አለና ከዚያ ሲለይ እንተ ስማ ናዝሬት፤ ብዙ ደናግል አሉና እንተ ተፍኀረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ፤ ብዙ ዮሴፍ አለና ከዚያ ሲለይ ዘእምቤተ ዳዊት አለ፡፡”(ወንጌል ቅዱስ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባብና ትርጓሜው፤1997፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፡፡) ኑሮዋም ባላመኑና በክፉዎች መካከል ቢሆንም(ሉቃ.1፥26) በእግዚአብሔር የምታምን፤ የእስራኤልን አምላክ ብቻ በመፍራት የምታመልክ ነበረች፡፡ ድንግል ማርያም ምንም መልካምነት በሌለባት ናዝሬት(ዮሐ.1፥47) የሚደነቅ መልካም ነገር ተገኝቶባታል፡፡
የመልአኩ ገብርኤል ብሥራት አጭር ቅኝት
    ወደገሊላ ናዝሬት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ሲወርድ፤ የሄደው ወደአንዲት፤ ማርያም ወደምትባል ድንግል ሴት ነው፡፡(ሉቃ.1፥27) ይህ ቃል እግዚአብሔር በየትኛውም ክፉ ዘመንና ሁኔታ ውስጥ የራሱ የሆኑትን ፍጹም ጠብቆ እንደሚያኖር ያሳየናል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰው ህሊናና ማስተዋል በላይ የሚደንቅ ነው፡፡ ቅዱስ ኤልያስ በእርሱ ዘመን ጣዖት ተስፋፍቶ ሰው ሁሉ በዓልን ይከተል ነበር፡፡ ከእርሱ በቀር ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ያለ አልመሰለውም፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ቅዱስ ኤልያስ በማያስተውለውና በማያውቀው መንገድ እንደኤልያስ “ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ።”(1ነገ.19፥9፤18)፤ሮሜ.11፥5) ያለ እግዚአብሔር፤ በናዝሬትም በጸጋው የመረጣትን ቅሬታ፤ ድንግል ማርያምን እናገኛለን፡፡

Saturday, 2 August 2014

ብትሮጥም አክሊል የማትደፋው …


Please read in PDF

ፍቅርና ርህራሄ፣ ደስታና ቸርነት፤
የውሃት፣ ቅንነት፣ የበዛ ምህረት፤
ለማድረግ ምክንያቶች የምትደረድረው፤
እኔ በሚል ብቃት ለማድረግ ‘ም‘ጥረው፤
እንዳይመስልህ ፍጹም አንተ የምትችለው፡፡