Thursday, 28 August 2014

የመቶ አለቆቹ (የመጨረሻ ክፍል)





4. የመቶ አለቃው ዩልዮስ (ሐዋ.27፥43)

“የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ … ”
      ቅዱስ ጳውሎስ ለቁጥር በሚታክቱና ምላሳቸው በሳለ ከሳሾች መካከል “እየተብጠለጠለ” ቅንጣት ታህል አለመፍራቱን ሳስብ የጌታ ኢየሱስ “ … አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና፡፡” የሚለው የትንቢት ቃል መፈጸሙን ትዝ ይለኝና ልቤ ይረካል፡፡(ማቴ.10፥19-21) የእስያ አይሁድ፣ የኢየሩሳሌም አይሁድ፣ ጠርጠሉስ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ … ስለእርሱ በጎነት የላቸውም፡፡ ፊስጦስም እንደቀደሙት ባዕለ ሥልጣናት ክፉ ልማድ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲዳኝ ይጐተጉተዋል፡፡(ሐዋ.25፥9፤21)
        ቅዱስ ጳውሎስ ነገሩ እንዳላማረ፤ ፊስጦስ ራሱ ወደአይሁድ እንዳደላ ያወቀ ይመስላል፡፡ አሁን በቆመበት የሮማ የፍርድ ችሎት ፊት መዳኘት እንደሚፈልግ በጽናት ተናገረ፡፡ ምክንያቱም በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቢዳኝ የልባቸውን ክፋት ያውቀዋል፡፡ ይገድሉታልና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለሌለው ሞት ራሱን አሳልፎ አልሰጠም፡፡(ዮሐ.8፥59) ጳውሎስ “ሰማዕትነት አያምልጠኝ” ብሎ ለስንፍና ሞት ሳይሸነፍ ወደቄሳር ይግባኝ በማለት በሮማዊ ዜግነቱ የተሰጠው መብቱን ተጠቀመበት፡፡(ሐዋ.25፥11)

Monday, 25 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል አራት)



የሮማ መቶ አለቆች
3.2. በሰፈሩ ውስጥ(ሐዋ.23፥10)

       ቅዱስ ጳውሎስ ከመገረፍና ጭካኔ ከተመላበት ድብደባ በኢየሱስ መንፈስና ብርታት፤ በየመቶ አለቃውም ቅንነት ተርፏል፡፡ በማግስቱ ሻለቃው አይሁድ እርሱን የከሰሱበትን እርግጡን ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቦ ከፈታው በኋላ፤ ሸንጎውንና የካህናት አለቆችን እንዲሰበስቡ አዞ፤ ጳውሎስን በፊታቸው አቆመው፡፡ የአይሁድ ሸንጎ እንዲሰበሰቡ የተፈለገበት ምክንያት ሻለቃው የጳውሎስን ጥፋት ማወቅ ስለተሳነው የእርሱ ወገኖች እንዲያጣሩ ነበር፡፡ ግን ዳኝነቱ ቀድሞ በአድሎአዊነት አጋድሏል፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስ በሸንጎው ፊት በቆመ ጊዜ ሁለት የማይስማሙ ወገኖች ጳውሎስን ለመክሰስ ግን ተስማምተው ቆሙ፡፡ ሁል ጊዜ ይደንቀኛል፡፡ የጌታ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለመግደል፤ ለማሳደድ፤ ለመክሰስ ሁለት ፈጽሞ የማይስማሙ አካላት ይፋቀራሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በሁለት ፍጹም ተቃራኒ የእምነት አካላት የተከሰሱ አማኞችን የአለማዊ ፍርድ ቤት ችሎት እየደነቀው የማየት ዕድል አጋጥሞታል፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን አብረው ለመኖር አይስማሙም፣ ይበላላሉ፤ ክርስቶስ ኢየሱስንና እንደጳውሎስ ያሉ አማኞችን ግን ለመክሰስ ከባልና ሚስት ይልቅ ይዋሃዳሉ፡፡

Thursday, 21 August 2014

በድንግል ማርያም ላይ የአይሁድ አሽሙር (የመጨረሻ ክፍል)



     አረጋዊው ቅዱስ ስምዖን የናዝሬቱን ህጻን ኢየሱስን ለግዝረት ወደቤተ መቅደስ በእናቱ ክንድ ታቅፎ በወጣ ጊዜ፤  ህጻኑን  ከእናቱ ክንድ ተቀብሎ የደስታና የሚያስጨንቅ ትንቢት ለህጻኑና ለእናቲቱ ተናገረ፡፡ እንዲህም አለ፦   “እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት።”(ሉቃ.2፥35) እመቤታችን ጥልቅ የመከራ ሥቃይ እንደምትቀበል የሚያመለክትና፤ ኢየሱስ ገና በስምንተኛ ቀኑ ሊሞት እንዳለው ለመጀመርያ ጊዜ ተነገረለት፡፡
     በራስ የሚደርስን መከራንና ስቃይን ገና በልጅነት መስማት ከማስደንገጥ አልፎ ያሰቅቃል፡፡ ድንግል ማርያም በነፍሷ ሰይፍ ማለፍ የጀመረው ጌታን መጽነሷ ከታወቀባት ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ ከኤልሳቤጥ ዘንድ ወደናዝሬት ከመጣች በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አይሁድ የጌታ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ከድንግል ማርያም መወለድ ሲያስተምር በነበረበት ዘመኑ እንኳ አልተቀበሉትምና፡፡
      ጌታ “አባታችን አብርሃም ነው” ብለው በባዶ ትምክህት የሚመኩትን አይሁድ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር፡፡ … እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ ዲያብሎስ የሚያደደርገውን ነው” (ዮሐ.8፥38፤44) ባላቸው ጊዜ የመለሱት መልስ የአሽሙር ስድብ ነበር፡፡

Monday, 18 August 2014

“ … እርሱን ስሙት” (ማቴ.17፥5)



እንኳን ለደብረ ታቦር መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!



    ቃሉን የተናገረው አብ ነው፤ የተነገረለት ደግሞ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ … የሰው ልጅ “ምን እንደሚሰማ እዝነ ልቡናውን አለመጠበቁ” (ማር.4፥24) የህይወት ዘመኑን በጭንቅ እንዲጓዝ፤ ፈቃዱም ከፈጣሪው ይልቅ ወደፍጡር እንዲያዘነብል፤ ሊሰማ የሚገባውን የበላዩን ጌታ ትቶ ከጎን ያለችውን “ወዳጅ ሚስቱን” መስማቱም ማንነቱን ድካም፤ እሾህና አሜኬላ ደግሞ ዙርያውን ለመከበቡ ምክንያት ሆኗል፡፡(ዘፍ.3፥10-21)
     አዳም ሁሉን አዋቂውንና ሰምቶ ከመመለስ ቸል የማይለውን ጌታ አለመስማቱ፥ ለማይሰማውና በጭካኔ ለተሞላው ለሰይጣን አገዛዝ ማንነቱንና ነጻነቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የእስራኤል ልጆች ወደእግዚአብሔር እረፍት ያልገቡት ጌታ እግዚአብሔር በድምፁና በሙሴ አማካይነት እየተናገራቸው ከመስማት ይልቅ “እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም?”(ዘጸ.17፥7)፤ “ … ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው የሚጠጣም ውኃ የለበትም።”(ዘኅ.20፥5-6) ብለው ፍጹም ድምጹን እየሰሙ እግዚአብሔርን በአመጻ ቃል በማስመረራቸውና አልታዘዝ በሚል ልብ በመከራከራቸው ነው፡፡(ዕብ.3፥7)

Saturday, 16 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል ሦስት)




3. የሮም መቶ አለቆች
3.1. በማረፊያው ሥፍራ (ሐዋ.22፥24)
     ቅዱስ ጳውሎስ ወደኢየሩሳሌም ጉዞ ከመጀመሩ በፊት የተነገረበት ትንቢት አስጨናቂ ነው፡፡(ሐዋ.21፥10-14) እንደሚገረፍና ለአህዛብ ተላልፎ እንደሚሠጥ ቢያውቅም፤ ጨክኖ ወደኢየሩሳሌም እየወጣ፦ ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን “ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ ቅዱሳንን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ ጸልዩ።”(ሮሜ.15፥33) በማለት እንዲጸልዩለት ያሳስባል፡፡ ጸሎቱና ጸሎታቸው ተሰምቶ “ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።” ብሎ ጸሐፊው ያስረግጠዋል፡፡(ሐዋ.21፥17)
   ሐዋርያው በኢየሩሳሌም የሚታወቀው “የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና በመዛቱ፤ በቅዱሳንም ላይ ብዙ ክፉ በማድረጉ”ና (ሐዋ.9፥1፤13) ለኦሪት ህግ እጅግ በመቅናቱ ነው፡፡ አሁን ግን ታሪክ ተለውጦ ያሳድድ በነበረው በዚያ ነገር መሰደድ ጀምሯል፡፡ ብዙዎች ወደኢየሩሳሌም እንዳይሄድ አብዝተው የለመኑት ስለዚህ ነገር ነው፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ግን ለእስራት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌምም እንኳ እንዲሞት ልቡን አስጨከነ፡፡ አገልግሎት ሰዎች ባዩልን አልጋ በአልጋ በሚመስለው ይቀናችኋል ቢሉንም ጌታ ባየልን በእሾሁና በጐርባጣው መንገድ በደስታ የሚቀበሉ እጆችን ያሰናዳል፡፡ ምስክርነትና ንስሐ በተካደበትና በተበደለበት መንገድ ሲሆን ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡ በግልጥ ያሳደደውን ጌታን ባሳደደባትና ብዙዎችን በበደለባት ከተማ ቅዱስ ጳውሎስ በዚያች ከተማ ተገኝቶ ታላቅ ምስክርነትን መሰከረ፡፡ በአደባባይ ያሳደደው በአደባባይ ተሰደደ፡፡ ዛሬ ግን በዘፈን፣ በከህደት ትምህታቸው፣ በፖለቲካ … መርዝ ብዙውን ህዝብ በአደባባይ የበደሉ ንስሐቸውን በጓሮ መጨረሳቸውን ከየት እንደተማሩት ግራ ይገባል፡፡ እውነተኛ ንስሐና ምስክርነት በተሠራበት በዚያው መንገድ ቢሆን ብዙ ምህረት ከጌታ በሆነችልን ነበር፡፡

Wednesday, 13 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል ሁለት)



ፈጣን ጉዞ ወደ ተራራማው የኤፍሬም አገር
   
    ድንግል ማርያም “እንደቃልህ ይሁንልኝ” ባለች ጊዜ እንደመንፈስ ቅዱስ አሠራር ህጻኑ በማህፀኗ ተፀንሷል፡፡ ይህ ነገር ከሆነ በኋላ ሳትቆይ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ወደዘካርያስ ቤት ተጓዘች፡፡ ከመልአኩ አንደበት የሠማችው የኤልሳቤጥ መፅነስ ሳያስደምማት አይቀርም፡፡ በእርግጥም ዝጉ ማህፀን ሲከፈት፤ አይቻልም የተባለው ሲቻል፤ አይሆንም ተብሎ የተደመደመው ሆኖ ሲታይ በእርግጥ ያስደምማል፡፡ ደስታ የበዛላቸው በአንድ ተገናኙ፡፡ “አንዱ ለአንዱ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” እያሉ ሊያወሩ፡፡ አዎ! ሠላምታቸው እንኳ ለእግዚአብሔርን ክብርና አምልኮን በመስጠት የደመቀና የሚማርክም ነው፡፡

Friday, 8 August 2014

ድንግል ማርያምና የአይሁድ አሽሙር(ክፍል አንድ)




    
እመቤታችን ድንግል ማርያም በጌታ ያመነች ብጽዕት ናት፡፡(ሉቃ.1፥45) ከዳዊት ቤት ወገን የምትሆን ድንግል ብላቴና(ኢሳ.7፥13) ዕድሜዋ ወጣት፣ የገሊላ ናዝሬት ወደምትሆን … “ብዙ ገሊላ አለና ከዚያ ሲለይ እንተ ስማ ናዝሬት፤ ብዙ ደናግል አሉና እንተ ተፍኀረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ፤ ብዙ ዮሴፍ አለና ከዚያ ሲለይ ዘእምቤተ ዳዊት አለ፡፡”(ወንጌል ቅዱስ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባብና ትርጓሜው፤1997፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፡፡) ኑሮዋም ባላመኑና በክፉዎች መካከል ቢሆንም(ሉቃ.1፥26) በእግዚአብሔር የምታምን፤ የእስራኤልን አምላክ ብቻ በመፍራት የምታመልክ ነበረች፡፡ ድንግል ማርያም ምንም መልካምነት በሌለባት ናዝሬት(ዮሐ.1፥47) የሚደነቅ መልካም ነገር ተገኝቶባታል፡፡
የመልአኩ ገብርኤል ብሥራት አጭር ቅኝት
    ወደገሊላ ናዝሬት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ሲወርድ፤ የሄደው ወደአንዲት፤ ማርያም ወደምትባል ድንግል ሴት ነው፡፡(ሉቃ.1፥27) ይህ ቃል እግዚአብሔር በየትኛውም ክፉ ዘመንና ሁኔታ ውስጥ የራሱ የሆኑትን ፍጹም ጠብቆ እንደሚያኖር ያሳየናል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰው ህሊናና ማስተዋል በላይ የሚደንቅ ነው፡፡ ቅዱስ ኤልያስ በእርሱ ዘመን ጣዖት ተስፋፍቶ ሰው ሁሉ በዓልን ይከተል ነበር፡፡ ከእርሱ በቀር ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ያለ አልመሰለውም፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ቅዱስ ኤልያስ በማያስተውለውና በማያውቀው መንገድ እንደኤልያስ “ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ።”(1ነገ.19፥9፤18)፤ሮሜ.11፥5) ያለ እግዚአብሔር፤ በናዝሬትም በጸጋው የመረጣትን ቅሬታ፤ ድንግል ማርያምን እናገኛለን፡፡

Saturday, 2 August 2014

ብትሮጥም አክሊል የማትደፋው …


Please read in PDF

ፍቅርና ርህራሄ፣ ደስታና ቸርነት፤
የውሃት፣ ቅንነት፣ የበዛ ምህረት፤
ለማድረግ ምክንያቶች የምትደረድረው፤
እኔ በሚል ብቃት ለማድረግ ‘ም‘ጥረው፤
እንዳይመስልህ ፍጹም አንተ የምትችለው፡፡

Tuesday, 29 July 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል ሁለት)


2. የቂሳርያው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ(ሐዋ.10፥1-48)
      ቆርኔሌዎስ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር “እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ሰው” ነበር፡፡ እግዚአብሔርን የመፍራቱና የማክበሩ መገለጫ እግዚአብሔርን ያከብራል(ሐዋ.10፥22)፣ ለህዝቡ እርዳታና ቸርነትን ያደርጋል፤ የጸሎት ህይወትም ነበረው፡፡(ሐዋ.10፥2) ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የአይሁድን ሥርዐት በመከተል አልተገረዘም፣ ምስክሮች ባሉበት የውኃ ጥምቀት አልተጠመቀም፤ በመቅደስም መሥዋዕት አላቀረበም፡፡ ይህ ደግሞ አህዛብ ወደይሁዲ እምነት እንዳይመጡ ከልካይ ከነበሩት ሥርዐት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ነበሩ፡፡
    ከአህዛብ ወደአይሁድ እምነት ሙሉ ለሙሉ የገባና ሥርዐታቸውን ሳያጓድል የሚፈጽም ባይሆንም፤ ቆርኔሌዎስ በአንድ አምላክ አምኖ የአይሁድን ሃይማኖትና ምግባር የሚከተል ሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ፦ እንደአይሁድ ሥርዐት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጸልይ ነበር፡፡(ሐዋ.3፥1) በዛሬ ዘመን ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያሉ አማኞችን ተቀብለው፤ የጸጋውንና የመዳኑን ወንጌል ከመስበክ ይልቅ የራሳቸውን ሥርዓትና መመሪያ በማሸከም አማኞችን ማጉበጣቸው ያሳዝናል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንደመናፍቅና ቀኖና ጣሽ ቆጥረው ማውገዝ እንጂ ማቅረብ አይሆንላቸውም፡፡

Tuesday, 22 July 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል አንድ)




     እግዚአብሔር ሥልጣንን ለሰው ሁሉ የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ምክንያቱም “ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።”(ሮሜ.13፥1) የሥልጣን መገኛው እግዚአብሔር ከሆነ ሥልጣንን የጨበጡ ወገኖች ቀዳሚ ተግባራቸው ደግሞ ህዝብ መምራታቸው ሳይሆን እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ “እግዚአብሔርን መፍራታቸው ክፋትን ፤ ትዕቢትንና እብሪትን፤ ክፉንም መንገድ፤ ጠማማውንም አፍ እንዲጠሉ ይረዳቸዋል።(ምሳ.8፥13)
  በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት የሥልጣን እርከኖች መካከል መቶ አለቅነት አንዱ ነው፡፡ የመቶ አለቃ በሥሩ መቶ ወታደሮችን የሚያዝዝ የሮማዊ ጦር መኰንን የማዕረግ ሥልጣን ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱት ሮማውያን የመቶ አለቆች ደግሞ፤ አህዛባውያን ሆነው ካመኑት የተሻለ ህይወትና እምነት ይዘው ተገኝተዋል፡፡ ጌታ ቢረዳን እነዚህን የመቶ አለቆች አንድ በአንድ እናያለን፡፡

1.    የቅፍርናሆሙ የመቶ አለቃ (ሉቃ.7፥1-11)
   

Friday, 18 July 2014

በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ(ሐዋ.7÷39) (የመጨረሻ ክፍል )

የእግዚአብሔር ሀሳብ - የእግዚአብሔር እስራኤል

    
 በአንዱ እስራኤል መካከል ክርስቶስን በማመንና ባለማመን ምክንያት ልዩነት ሆኗል፡፡ በሥጋ የአንድ ዘር ወገን ነኝ ማለት የእግዚአብሔር ወገን ስለመሆን ዋስትና አይደለም፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ምንም እንኳ በመገረዝና እስራኤላዊ በመሆን ብቻ የእግዚአብሔር ወገን እንደሆኑ በቀደመው ኪዳን ቢታወቅም፤ አሁን ግን ይህ የለም፡፡ በግልጥ ቃሉ “ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉም” ብሏል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር እስራኤል ከአይሁድ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ህዝብ በክርስቶስ በማመን አዲስ ፍጥረት በመሆን የእግዚአብሔር እስራኤል ይሆናሉና፡፡

Monday, 14 July 2014

“በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ”(ሐዋ.7÷39) (ክፍል - 2)


v ሙሴ ከእግዚአብሔር “እርሱን ስሙት” የተባለለት ሰው ነበር፡፡ ምክንያቱም “ይሰጠን ዘንድ ህይወት ያላቸውን ቃላት የተቀበለ” ነውና፡፡(ሐዋ.7፥37-38) ነገር ግን “አባቶች” የነበሩቱ ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ይልቁንም ገፉት እንጂ፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ፤ታናናሽና ታላላቅ አይሁድም ነቢያት የመሰከሩለትና አብ በድንቅ በተገለጠው የደብረ ታቦር መገለጡ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት…”(ማቴ.17፥5) ብሎ የተናገረና በሥጋ የወለደችው እናቱ ድንግል ማርያምም “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት የተናገረችለት ናት፡፡ነገር ግን ሙሴን ባለመታዘዝ እንደገፉት ሁሉ፤ ልጆች የተባሉቱም ክርስቶስ ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ጠሉት፤ገፉት፤ሊገድሉትም ይፈልጉት ነበር፡፡(ዮሐ.5፥16)
    የእስራኤል ልጆች በዚያን ጊዜ በምድር ካሉት ሁሉ እጅግ ትሁት የነበረውን(ዘኁ.12፥3) ሙሴን  ባለመስማታቸው ካገኛቸውና ሙሴንም ካስቆጣው አንዱ ኃጢአት ክፉ ምኞት ነው፡፡(ዘኁ.11፥4፤10)፡፡ ክፉ ምኞታቸው ለገዛ መቃብራቸውና ለሞት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡(ዘኁ.11፥34)፡፡ ጲላጦስ፦ አይሁድና “…የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደሰጡት ያውቅ ነበር”(ማር.15፥6) ማወቅ ብቻ አይደለም ፤ “ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ የሰጠው”(ሉቃ.23፥25) መሪው ጲላጦስ ከአይሁድ ጋር የተባበረበት አንዱ መንገድ ክፉ መሻታቸውንና ሃሳባቸውን እያወቀ፤ ህግ ተላልፎ ለክፉ ምኞታቸው አሳልፎ መስጠቱ ነው፡፡ ይህ ድርጊት አይሁድን “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” እስኪሉ ዕውር አድርጓቸዋል፡፡(ማቴ.27፥25)

Wednesday, 9 July 2014

ተበልጧል በሁሉ

Please Read in PDF

ትዳር ያቀለጠህ፣ ሥልጣን ያባለገህ፤
ሀብት ያሞላቀቀህ፣ ዝና ያሰከረህ፤
ዕውቀት ጨርቅ ያስጣለህ፤
ለዚህ አለም ነገር፣ የምትንቆራጠጥ፤
በሌላውስ ይቅር፣ በክርስቶስ ጌታ፣ በዚህ አትበለጥ፡፡

Friday, 4 July 2014

“በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ”(ሐዋ.7÷39) (ክፍል - 1)

Please read in PDF
     
     የጌታ ኢየሱስ መንግስት እየሰፋች፤ ብዙዎችንም እየወረሰች የመጣችውን የመጀመርያቱን የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ለማስቀጠል “በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ሐዋርያት መርጠው ለማዕድ አገልግሎት ሾሟቸው፡፡”(ሐዋ.6፥6) ከእነዚህ ከሰባቱ ታላቁ ዲያቆን እስጢፋኖስ “ ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።”(ሐዋ.6፥8)፡፡ ይህ ብርቱ የእግዚአብሔር ሰው ሰማዕት ሆኖ፤ ሞቱ ብዙዎችን ለጥቅም ከመበተኑ በፊት  የቀደሙትን የእስራኤልን ዘሥጋ ህይወትና አሁን የኪዳኑን ፍጻሜ እያዩ ያላመኑትን ፈሪሳውያንና የመቅደሱን ታላላቅ ካህናት እያነጻጸረ ሳይሸነግልና ሳይፈራ በብርቱ ቃል ወቀሳቸዋል፡፡

የግብጽ እስራኤል

     እስራኤል ልጆቹ ወደግብጽ ሲወርዱና በኋላ ላይ እርሱም አብሮ በረሃብ ምክንያት ሲሰደድ የመረረ ልቅሶ፣የልጁ የዮሴፍን ውለታ የሚረሳ አዲስ ንጉስና ህዝብ … እንደሚነሳ ያስተዋለ አይመስልም፡፡ እነርሱም ጥቂት በጥቂት ልባቸው በዚያ እየቀለጠ፣ የተገባላቸውን ኪዳንና ተስፋ ረስተው፣ ፈጽሞ ልባቸው በጣዖት አምልኮ ሊያዙ እንደሚችሉ ለቅጽበት እንኳ አላስተዋሉትም፡፡ ሰባ የእስራኤል ነፍስ ወደግብጽ ሲወርዱ (ሐዋ.7፥14)ሁለት ሚሊየን ገደማ ይሆኑም እንደሆነ ማን ለአፍታ እንኳ አሰላሰለ? አዎ! እስራኤል ወደግብጽ ሲወርዱ ሆዳቸውን እንጂ ጌታ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያሰባትን ሃሳብ ፈጽመው ያስተዋሉም አልነበሩም፡፡
      ግብጽ ለእስራኤል ዘሥጋ የባርነት ቀንበር በመጫን ለእስራኤል ዘነፍስ ደግሞ መዳን ምክንያትና ቤዛ ለሆነው ስደተኛ ህጻን አባቱ እስኪጠራው (ሆሴ.12፥2፤ማቴ.2፥15) ማረፊያ በመሆኗ በታላቁ መጽሐፍ ተቀምጣለች፡፡ የእስራኤል ልጆች ግብጽን ባሰቧት ጊዜ በብዙ ቅንአት ይቃጠላሉ፡፡ ወንዶች ልጆቻቸውን ገና በማህጸን የገበሩባት፣ ጉልበቶቻቸው አለልክ የተበዘበዘባት ፣ ስድብን የጠገቡባት፣ ውለታቸውና ብድራታቸው በባዶ የተጣፋባት፣ የድካማቸውን ወዝ ያጡባት ፣ ምግብ ለጌቶቻቸው እያበሰሉ የተራቡባት ፣አስገባሪዎቻቸው ወዛቸውን የመጠጡባት ፣በልቅሶ ሸለቆ እንባቸውን የታጠቡባት ፣በዋርካዎቿና በዛፎቿ ጥላ ሥር የተከዙባት ፣በኮረብታዎቿ ሁሉ ላይ ምሬታቸውን ያሰሙባት ፣ራሔል እንባዋን ወደራማ የረጨችባት፣ እንግዶች አማልክት ነፍስና መንፈሷን ያስጨነቁባት ፣ እየዳኸች በባርነት ምጥ የተንፏቀቀችባት … የምድር ተስፋዋ ሁሉ ተሟጦ ክንድ ከኤሎሒም የተላከላትን ያቺን የግብጽ ምድር ኑሮ፣ ፊትና መልክ እንኳንስ እርሷ እስራኤል እኛም መቼም አንዘነጋውም፡፡

Monday, 30 June 2014

የጠፋው ልጅ ወንድሞች(ሉቃ.15፥28)


ከሌሎች ወንጌላት ይልቅ ጠፍቶ ስለመገኘት ሉቃስ ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጠናል፡፡“ጠፍቶ የተገኘው” ህጻኑ ኢየሱስ(ሉቃ.2፥46)፣ ጠፍቶ የተገኘው በግና ድሪም (ሉቃ.15፥3-11) ሉቃስ የዘገባቸው እውነትና ምሳሌዎች ናቸው፡፡በእርግጥ በኃጢአት ጠፍቶ ለበጎነት እንደመገኘት ያለ ፍጹም ሰማያዊ ደስታ የለም፡፡(ሉቃ.15፥10)
     የጠፋው ልጅ የአባቱን ሀብት ለመካፈል ሲነሳ ወደአባቱ ቤት ለመመለስ ፈጽሞ ያሰበ አይመስልም፡፡ከአባቱ ቁጥጥር ውጪ በመሆን ያሻውንና የወደደውን ሊያደርግ በመፈለግ ወጥቶ የሄደ ነው፡፡“ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ የሄደው ወደሩቅ ሀገር ነው፡፡”(ሉቃ.15፥13) በሄደበት ሀገር ግን ሀብቱን በተነ፡፡ እንዳይመለስም እጅግ ርቆ ሄደ፡፡ የኃጥዕ መንገድ ከእግዚአብሔር የተለየ ነውና ሩቅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተለየው አዳም መልካም በሚመስለው መንገድ ሲጓዝ ፤በገነት እያለ ከእግዚአብሔር ሩቅ ነበር፡፡(ዘፍ.3፥6) በተመሳሳይ መንገድ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ወደተርሴስ የሄደው ዋጋ ከፍሎ፤ከስሮ ፤ርቆም ነው፡፡(ዮና.1፥3)
     የጠፋው ልጅ ከመራቁ ባሻገር በረሃብ ምክንያት የሚጨነቅም ሆነ፡፡ የረሃቡን ጭንቀት ለማስታገስ “ … ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።”(ሉቃ.15፥15) ይላል፡፡ የጠፋው ልጅ የእሪያ እረኛ በመሆን ያደረገው ይህ ድርጊት በአይሁድ ልማድና  በኦሪት ህግ እጅግ ርኩሰት ነው፡፡(ዘሌ.11፥7) ይህ ብቻ አይደለም ለእንሰሳት የሚሰጠውን የእህል ገለባ (አሰር) ሊበላ እየተመኘ እንኳ ሊያገኝ ያልቻለ ነበር፡፡