በሥጋ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል
ማርያም የተወለደው ኢየሱስ፥ ዓለምን ብቻውን ሊያድን ብቃት ያለው አዳኝ፣ መሲህ ክርስቶስ ሆኖ የሰውን ልጅ ሊያድን ተገልጧል፡፡
ነቢዩ "ሕጻን ተወልዶልናልና …"(ኢሳ.9÷6) ያለውን ያንን ሕጻን፥ ማቴዎስም ሕጻን ብሎ ይጠራዋል፡፡ ይህ ሕጻን
ገና ሳያድግና አንደበቱን ከፍቶ ሳይናገር የንጉሥ ፍርሐት፤ የዲያብሎስ ጭንቀት ሆነ፡፡ ኢየሱስ ገና የሁለት ዓመት ሕጻን ቢሆንም፥
ጎልማሳው ሄሮድስ ግን የመግደል ሴራን በስውር ጠነሰሰ፡፡ ጠላት ዓላማ ቢስ ከሆነ ሽማግሌና ጎልማሳ ይልቅ ዓላማ ያለውን ሕጻን በአላማ
አጽንቶ ይዋጋል፡፡ ጉዳዩ አላማ እንጂ ዕድሜ አይደለምና፡፡
የሁለት አመት ሕጻን በሰው ፊት ትርጉም ላይሰጥ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር
ግን እጅ በአፍ እስክንጭን በድንቅ ቃል ምስጢር
ያወራዋል፡፡ በነቢዩ ሳሙኤልም የሆነው እንዲህ ነው፡፡ እግዚአብሔር ታላላቅ ነን ከሚሉት ጋር ሳይሆን ስለእስራኤል ጉዳይ ከሁለት
አመቱ ብላቴና ጋር ያወራ ነበር፡፡ ዓለማውያንና የመቅደሱ አገልጋዮች በእግዚአብሔር ላይ በኃጢአት ሲያምጹ እግዚአብሔር ሳሙኤልን
በትሑት ቃል ተናገረው፡፡
