እሳት በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ዓይነት መንገድ ተገልጦአል። ለኹላችንም ግልጥ የኾነው እሳት፣ ሰዎች ለመሥዋዕት
አገልግሎት (ዘሌ. 6፥13፤ 1ነገ. 18፥38፤ 2ዜና. 7፥1-3)፣ ለምግብ ማብሰያ (ዮሐ. 21፥9)፣ ለብረት ማቅለጫና
(ዘጸ. 32፥24) ለሌሎችም አገልግሎት የሚውል ነው። ይህን እሳት ዓላውያን ነገሥታት አንዳንድ ጊዜ በእነርሱ ላይ
ለተነሣሱባቸው ሰዎች፣ የፍርድ መቀጣጫ አድርገው ይጠቀማሉ። ንጉሥ ናቡከደነጾር፣ ለእርሱ ምስል ወይም ጣዖት አልሰግድም ያሉትን
ሦስቱን ወጣቶች፣ “… ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት
ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ።” (ዳን. 3፥20)።
ነገር ግን ሦስቱን ወጣቶች የእስራኤል አምላክ ያህዌ ኤሎሂም ታደጋቸው፤ አዳናቸውም፤ ከእስራኤል አምላክ ከቅዱሱ እግዚአብሔርም በቀር ሌላ የሚያድን አምላክ እንደሌለ፣ ያ ዓላዊ ንጉሥ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለም” (ዳን. 3፥29)፤ በእርግጥም ከእሳት የሚያድን ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ እንደሌለና በእሳትም ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ቅዱሳት መጻሕፍት በምልአት ይመሰክራሉ፤











