Wednesday, 4 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (ክፍል 2)

በክፍል አንድ ላይ ለተሰጡ አስተያየቶች “ሚጥጥዬ መደምደሚያ”
    የተሰጡት አስተያየቶች ሁለት መልክ ያላቸው ናቸው[ሦስተኛውን የስድብ ክፍል መጥቀስ ባልሻም]፤ አንደኛው ቀድሞ በግል መምከርና ማናገር ይገባ ነበር እና አንተ ራሱ ማን ኾነህ ነው እርሱን “የምትኰንነው?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ለአስተያየቶቹ መልስ መስጠትን ባላምንበትም፣ በአብዛኛው በዙርያዬ ያሉ ሰዎች ያዘነቡትን ስድብና[በተለይ በኢሜይል] አስተያየት ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እጅግ ስለወረደብኝ፣ የትምህርቱን ኢ ክርስቶሳዊነት ለሚረዱት የማጥራት ሥራ ለመሥራት፣ ትምህርቱን አምነው ለተከተሉት ደግሞ በክርስቶስ ትምህርት ላይ ለሚመጣው የትኛውም ሰውም ኾነ ማኅበር ጭካኔዬን ለማሳየት ነው፡፡ አንድ ነገር ማስታወስ እወዳለሁ፤ አሁን እየተቃወሙ ካሉ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት ግብረ ሰዶማውያን አገልጋዮች በግልጥ ተደርሶባቸው እንዲመለሱ ብዙ ተመክረው አልመለስ ሲሉ፣ ከአደባባይ ነውራቸው አልመለስ ብለው ልባቸውን ሲያደነድኑና እውነታውን ለማድበስበስ ሲጥሩ በአደባባይ ሰዎች እንዲጠነቀቋቸው ስጽፍ የተቃወሙኝ መኾናቸውን አሁንም ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
    በጋሻውን በተመለከተ በተደጋጋሚ ማውራቴንና በዚህ ትምህርት ማመን አለማመኑን ስለመጠየቄ፣ እርሱም ስለመናገሩ ያልጻፍኩት፣ ብዙም አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነው፤ አስፈላጊና ሁሉ ማወቁ የግድ ተገቢ ነው ከተባለ ግን እንዴትና ምን ብዬ እንዳወራሁት፤ እርሱም በዚህ ትምህርት ዙርያ ያለውን አቋሙን ምን ብሎ እንደነገረኝና ይህን የሐሰት ትምህርትም ሊለውጠውም እንደማይፈቅድ የመለሰልኝን በዚህ ጽሁፍ ማብቂያ ላይ ለመግለጥ ቃል እገባለሁ፡፡

Monday, 2 October 2017

በጋሻው ደሳለኝ ና አዲሱ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” ትምህርቱ (ክፍል 1)

ግቢያ
     በዚህ ዘመን በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታወቁትን(ማቴ.7፥23) በሕዝብ ዘንድ የገነኑትንና የታወቁትን አገልጋዮች “ተሳስታችኋል ተመለሱ” ማለት፣ ራስን በስለት ላይ የማቆም ያህል ሕመሙ ጽኑና እጅግ አደገኛ ነው፡፡ አደገኛነቱም ከሁለት ነገር አንጻር ነው፤
1.     ደጋፊዎቻቸው ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ ተቃውሟቸው ተራ ተቃውሞ ሳይሆን፣ ልክ እንደቅዱሳን ሰማዕታት ስለመምህሮቻቸው በነፍስ ተወራርደው እስከመግደልና ስም ለማጥፋት የሐሠት ታሪክን ፈብርከው ከማኅበረሰቡ እስከማግለል ሊያደርስ በሚችል ጽኑ ቁጣ ውስጥ ስለሚገቡና፤
2.    ሕዝብ[አማንያንም ጭምር] ደግሞ እንዲህ ያለውን ነገር በቅንነትና በልበ ሰፊነት ከእግዚአብሔር ቃልና ከስህተት መምህራን ጠባይ አንጻር ከመመዘን ይልቅ፣ እንዲህ ያሉ መምህራንን የሚቃወሙትን አካላት ቀንተው ወይም ከጥላቻ አንጻር ... አንዳንዴም ሲከፋ የራስን ቅቡልነት በሕዝቡ ለማስረጽ የሚደረግ ደባ ነው በማለት፣ ተግሳጽና ተቃውሞውን በትክክል ለሕዝቡና ለእግዚአብሔር ከመቅናት አንጻር እንደተደረገ አድርጎ መውሰድ ፈጽሞ አልተለመደም፡፡

Saturday, 30 September 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF 
4.   ስሐ እንግባ
    አማንያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ በትክክል እንዲሰሙ፣ ክርስቶስን ሳይኾን ራሳቸውን የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ከመስማት ተከልክለው ለቃሉና ለፈቃዱ እንዲታዘዙ ለማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ጠባይ እንደቃሉ ማረቅና ዘወትር በቅዱስ ቃሉ መስታወትነት ራሷን መመልከት ይገባታል፡፡ ንስሐ ራስን ለእግዚአብሔር በትክክል ማቅረብና አራቁቶ ማቅረብ ብቸ ያይደለ፣ ድርጊታዊ ምላሽን ይሻል የምንለውም ከዚህ ተነሥተን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሌሎችን ከክፋታቸው እንዲመለሱ ለመምከር ከመዘጋጀቷ በፊት፣ ከምትወቅስበት ወቀሳ ለራሷ ንጹህና በዚያም ነውርና ክፋት ያልተያዘች፤ ፈጽማም የጠራች ልትኾን ይገባታል፡፡
     የራሳችንን ክፉ ጠባይ ሳናስተካክል፣ ሌሎች ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉና ወደትክክለኛው እውነት እንዲመጡ ጫና ከማድረግ መከልከል አለብን፡፡ ከዚህ ነገራችን ንስሐ ሳንገባ ይህንን የምናደርግ ከኾነ ግን ቅዱስ ቃሉ፦አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና” (ሮሜ.2፥1) እንዲል፣ “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” (ማቴ.7፥3) በማለት በጽኑ ወቀሳ ሁላችንን ይወቅሰናል፡፡

Monday, 25 September 2017

መስቀል ማለት ለኔ …

          Please read in PDF

መስቀል ማለት ለኔ …
ጌታዬ ኢየሱስ እኔን ስለመውደድ
ሊያድነኝ ሊቤዠኝ የሄደበት መንገድ
ከጲላጦስ ሄሮድስ ከሄሮድስ ጲላጦስ

Thursday, 21 September 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ሃያ)


Please read in PDF
3. ጌታችን ጋር ጸንታችሁ ቁሙ፦ መጽናት፣ አለመናወጥን፣ መረጋጋትን፣ መቆምን፣ አለማወላወልን፣ ወደግራም ወደቀኝም አለማለትን፣ አንድን ነገር አጥብቆ መያዝንና ለዚያም ነገር ዋጋ መክፈልን ... የሚያሳይ ነው፡፡ መጽናት የብዙ መታገስ ውጤት[እጅግ ብዙ ትእግስት] ነው፡፡ ብዙ የማይታገስ የማይናወጠውን በመመልከት ሊጸናና ሊቆም አይችልም፡፡ በመከራ የሚታገሱ ሁሉ(ሮሜ.12፥12) በክርስቶስ መንግሥት የሚካፈሉት ሕይወትና ደስታ አላቸው፡፡ የማይጸኑና በክርስቶስ ትምህርት ታግሰው የማይኖሩ ግን እጅግ አስጨናቂ ነገር ይገጥማቸዋል፡፡
     መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድመን በክርስቶስ ኢየሱስ ባመንነው እምነታችን መጽናትና በዚያም ማወላወል እንደሌለብን በተደጋጋሚ ይነግረናል፤ ምክንያቱም ራሱ ክርስቶስ ኢየሱስ መከራን ሁሉ በቅድስናና ባለማጉረምረም በመጽናት የእውነተኛ ጽናት ዋና ተምሳሌት ነውና፣ (1ጴጥ.2፥21)፤ “ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤” (ኢያ.1፥7)፤ “ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ” (1ቆሮ.16፥13)፤ “… ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል” (ቈላ.1፥23) “እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና” (1ተሰ.3፥8)፤ “እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥” (2ተሰ.2፥15)፤ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” (ዕብ.12፥3) እንዲል፡፡

Friday, 15 September 2017

የኢትዮጲያ ከፍታችን፤ ያለመብሰል ምኞት ወይስ ከልብ የምንሻው እውነት?!



     Please read in PDF

    መጽሐፍ ቅዱስ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ ይላል፥ “ … በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤” (ፊልጵ.2፥9) በማለት ሲናገር ምክንያቱንም፣ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ የመኾኑ” ነገር ነው በማለት ይነግረናል፤ (ቁ.6-8)፡፡
   ጌታችን ኢየሱስ አንድ ባሪያን ይዞ ሳይሆን የባሪያን መልክ፣ የሰውን ትስብእት ይዞ፤ የማይሞተው እርሱ መዋረዱንና ሰው በመኾኑም ሞትን ሊቀምስ እንዳለው ያስተምረናል፡፡ ሰው ለመሆን ሲፈቅድ አገልጋይነትንና እስከሞት መታዘዝን መከራንና ስድብን ሁሉ መቀበልን(ማር.15፥29) ፍጹም ዝቅ ዝቅ ማለትን ያሳየናል፡፡ ሰማያዊ መብቱንም በፈቃዱ በመተው ፍጹም ዝቅታን መርጧል፡፡ በዚህ ክፍል ያለው ሃሳብ እጅግ ሰፊና ታላቅ ትምህርት ቢኾንም፣ ጌታችን ኢየሱስ በአብ ፊት አለልክ ከፍ ከፍ ለማለት ምክንያቱ ስለሰው ልጅ ማዳን አለልክ ዝቅ ዝቅ ማለቱን ከርእሳችን ጋር ተወራራሽ ነውና ልናነሣው ወደድን፡፡

Sunday, 10 September 2017

ሠርክ አዲስ ዘመኔ!

Please read in PDF


ለምንድር ነው እንባ ስለምንስ ልቅሶ?
ከዘመናት በፊት ደምህ ለ‘ኔ ፈሶ፤
ሰቀቀን ለምኔ ማፈርና ፍርሃት?

Thursday, 7 September 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ዘጠኝ)


Please read in PDF
1.     ንጸልይ፦ ጸሎት ሰባተኛው መሣርያ አይደለም፡፡ ከስድስቱም ጋር በአንድነት ዘወትር የምንታጠቀው ነው እንጂ፡፡ ስለዚህም እንደሰባተኛ ራሱን የቻለ መሣርያ አድርገን የምንቆጥረው አይደለም፡፡ ጸሎትን ዘወትር በትጋት መታጠቅ ይገባናል፡፡ ለክርስቲያን ጸሎት ዋና መንፈሳዊ መሣርያው ነው፡፡ ማናቸውንም መልካም ነገሮችን በጸሎት ልንጀምር፤ በጸሎትም ልንጨርሳቸው ይገባናል፡፡ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር” የሚለው ቃል ስናጠቃም ኾነ ስንከላከል ጸሎት መሠረታዊና በማናቸውም ሰዓትና ሁኔታ ውስጥ ዘወትር መከናወን ያለበት ነገር እንደኾነ ያስገነዝበናል፡፡

Saturday, 2 September 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ስምንት)




6.    መንፈስንም ሰይፍ ያዙ፦ ሰይፍ፣ “ከብረት የሚሠራ የጦር መሣርያ፤ (1ሳሙ.13፥19 ፤ 22)፡፡ አንዳንዱ ሰይፍ ባለሁለት አፍ ነው፤ (መዝ.149፥6)፡፡”[1] ሰይፍ ከማይታዩ ከክፉ ኃይላት ጋር አማኙ ለሚያደርገው ጦርነት በዋናነት የሚጠቀምበትና ከማጥቂያ መሣርያዎች የሚካተት ነው፡፡ ወታደር ዘወትር ከሚይዛቸው መሣርያዎችና ጥብቅ ስልጠና ከሚወስድበት አንዱ ስለሰይፍና አጠቃቀሙ ነው፡፡ በዚህ ክፍል በሰይፍ ምሳሌነት የቀረበው “እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” ተብሎ የተነገረው ነው፡፡
    ሰይጣን ከምንም በላይ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያለንን መታመን ዋጋ ለማሳጣት ወይም ለማጥፋት በኹለንተናው የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፤ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው፡፡ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ፡፡ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው፤” (ዘዳግ.6፥6-9)፣ “በልብህ ጽላት ጻፋቸው” (ምሳ.3፥3 ፤ ኤር.31፥33)፣ “እንድንሰውራቸውም” (መዝ.119፥11) የታዘዝነውን የእግዚአብሔር ቃል ሰይጣን እንድንጥለው ብርቱ ጥረት ያደርጋል፡፡ ቃሉን በመጣል ውስጥ ያለውን ቀላልና አስቀያሚ ሽንፈት ዲያብሎስ በሚገባ ያውቀዋል፡፡

Thursday, 24 August 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ሰባት)


   “ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል፡፡ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፤” (ሮሜ.13፥12) ሌሊቱ ተብሎ የተጠቀሰው አሁን ያለው ክፉ ዘመን ነው፡፡ ጊዜውም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሚያካትት ነው፡፡ ቀጥሎም ሐዋርያው የክርስቶስን መምጣት አጽንቶ ይናገራል፡፡ “ቀኑም ቀርቦአል” ሲልም፣ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ “ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ” (ማቴ.24፥33)፣ “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤”(1ቆሮ.7፥29)፣ “ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል”(1ጴጥ.4፥7)፣ “የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ” (2ጴጥ.3፥11)፣ “ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ … ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን” (1ዮሐ.2፥18) “ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ” (ያዕ.5፥7)፣ “ዘመኑ ቀርቦአል” (ራእ.1፥3) ተብለው ከተገለጡት ምንባባት ጋር በመስማማት የዘመኑን  ከፊት ይልቅ ወደእኛ መቅረብና ክርስቶስ ሊመጣ በደጅ መኾኑን ይገልጥልናል፡፡

Monday, 21 August 2017

ኾኜ ያንተ ሎሌ!

በዚህ በኛ ዘመን፣ ሁሉ ነቢይ ኾኖ፤
ሐዋርያነትም፣ ስሙ ብቻ ገኖ፤
ቅስናም ድቁናም፣ ሁሉ እየተካነው፤

Wednesday, 9 August 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ስድስት)

                            Please read in PDF
3.    ሠላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፦ የጫማ ዋና ሥራ ከማናቸውም እንቅፋት፣ እሾኽና እግርን ከሚጎዳ አደጋ መከላከልና መደገፍ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ፡፡ ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው” (መዝ.119፥104-105) አለ፤  በጥንት አይሁድ አንድ ሰው የሩቅ መንገድ ሲጓዝ ድንገት ቢጨልምበት፣ በሚሄድበት መንገዱ እንዳይሰናከል በእግሮቹ ላይ መብራትን ያሥራል፡፡ ይህም የሚረግጥበትን በትክክል እንዲያስተውልና ወድቆም ከመሰበር እንዲድን ይረዳዋል፡፡
   ዳዊት በማናቸውም የሕይወት መንገዱ የእግዚአብሔር ሕግ መብራትና ብርሃኑ ነው፤ ስለዚህም በማናቸውም መንገዱ ቢሆን ከሐሰት ጋር አያመቻምችም፣ አይስማማምም፡፡ የሐሰትን መንገድ ከነፍሱ እጅግ ይጠየፋል፡፡ መብራትና ብርሃኑ የሕጉ ቃል ነውና፣ ይህንንም ሕግ በማናቸውም መከራ ውስጥ እንኳ ቢያልፍ ከመጠበቅና በሕጉም ከመጽናናት ቸል አይልም፡፡ በዳዊት ንግግሮች ውስጥ ሁል ጊዜ ዝግጁነትና ፍጹም ታማኝነት አለ፡፡

Tuesday, 1 August 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ አምስት)

Please read in PDf
የምንዋጋባቸው መሣርያዎቻችን
    መጽሐፍ ቅዱስ ከማን ጋር መዋጋት እንዳለብን አበክሮ የተናገረውን ያህል ከጠላታችን ጋር በመዋጋት በትክክል ስለምናሸንፍበት መሣርያም በግልጥ ይናገራል፡፡ ከዚህ በፊት እንዳየነው የምንዋጋው የእምነት ጦርነት ነው፡፡ የውጊያውም የጊዜ ቆይታ እስከክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ “በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታን ሆነን … የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም እንዲቻለን፣ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ ያስፈልገናል”፡፡ ልብሱንና የጦር ዕቃውን መልበስና መለማመድ ግድ ነው፤ ያልተለማመድንበትና አብረን “ያልሰለጠንበት” ልብስ ለውጊያ ሊሆነን ፈጽሞ አይችልም፡፡
     የመሣርያው ዓይነት፣ የትጥቆቹ ይዘት በመከላከልና በማጥቃት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም ሥራዎች[መከላከልና ማጥቃትን] ክርስቲያኖች መፈጸም እንዳለባቸው ያስተምራል፡፡ ለጌታ መታዘዝን በባርያ ማንነት ውስጥ ሆነን የምናሳየውን ትጋት ያህል፣ ለጠላትና ለሚያስጨንቀው ገዢ አለመታዘዛችንና ግልጥ ተቃውሞዓችንን የምናሳይበት መንፈሳዊ ጠባይ የጌታ መንፈሳዊ ወታደር በመሆን ነው፡፡

Tuesday, 18 July 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ አራት)

                                                                                   Please read in PDF
2. ዋጉ፦ በክርስቶስ ኢየሱስ ካመንንበት ቀን ጀምሮ ከክፋት ሁሉ አሠራርና ከዲያብሎስ ጋር ውጊያ ለመግጠም ፊት ለፊት ተፋጥጠናል፡፡ ደጋግመን እንዳነሣነው ውጊያችንም ከሥጋ ለባሽ ፍጡር ጋር ሳይሆን፣ ከጀርባው ለራሱ ክብርና አምልኮን ለመቀበል ከሚሠራው[ወንጌል የጨበጡ አገልጋዮችንም ጭምር በመጠቀም] ከክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት አለቃ ከሆነው ከዲያብሎስ ጋር ነው፤ (ኤፌ.6፥12)፡፡ ውጊያውን በተመሳሳይ መንገድ በመቆም እንጂ በግል ማንነታችን ብቻ ማሸነፍ እንደማንችል መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡
     “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን፤ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፤” (2ቆሮ.10፥3-5) እንዲል፣ ሰይጣን የሚሰወርበትንና የሚሰውርበትን የክፋትን ምሽግ፣ የስህተትን ትምህርት፣ ርኩሰትና ኃጢአትን ሁሉ ለማፍረስና ለመደምሰስ ፍጹም የሆነ ብቃት ያለውና ጠንካራው መሣርያ ከእግዚአብሔር የምናገኘው ጦር ዕቃ ብቻ ነው፡፡

Friday, 14 July 2017

ላ'ንተ ብቻ

የበገናው የመሰንቆው ኅብረ ዜማ
የዋሽንቱም የክራሩም የከበሮው ጥዑም ቃና
የግዕዛን ፉጨት የሕያዋን ቅኝት
የአምልኮ እልልታ የእንሰሳት የአራዊት
ላንተ ብቻ ይሁን ለክብር መንግሥትህ
ክብር ተጠቅልሎ አንተን ብቻ ያክብርህ!!!