መጽሐፍ ቅዱስ ከማን ጋር መዋጋት እንዳለብን አበክሮ የተናገረውን ያህል
ከጠላታችን ጋር በመዋጋት በትክክል ስለምናሸንፍበት መሣርያም በግልጥ ይናገራል፡፡ ከዚህ በፊት እንዳየነው የምንዋጋው የእምነት ጦርነት
ነው፡፡ የውጊያውም የጊዜ ቆይታ እስከክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ “በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታን ሆነን
… የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም እንዲቻለን፣ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ ያስፈልገናል”፡፡ ልብሱንና የጦር ዕቃውን መልበስና
መለማመድ ግድ ነው፤ ያልተለማመድንበትና አብረን “ያልሰለጠንበት” ልብስ ለውጊያ ሊሆነን ፈጽሞ አይችልም፡፡
የመሣርያው ዓይነት፣ የትጥቆቹ ይዘት በመከላከልና በማጥቃት ላይ የተመሰረቱ
ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም ሥራዎች[መከላከልና ማጥቃትን] ክርስቲያኖች መፈጸም እንዳለባቸው ያስተምራል፡፡ ለጌታ መታዘዝን
በባርያ ማንነት ውስጥ ሆነን የምናሳየውን ትጋት ያህል፣ ለጠላትና ለሚያስጨንቀው ገዢ አለመታዘዛችንና ግልጥ ተቃውሞዓችንን የምናሳይበት
መንፈሳዊ ጠባይ የጌታ መንፈሳዊ ወታደር በመሆን ነው፡፡
