Wednesday, 4 November 2015

ጣሊያናዊው የደብር አለቃና - የተከሰሰበት ግብረ ሰዶማዊነቱ




 Please read in PDF

       ስለተከሰሱ ሰዎች መብት የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት “በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር ፥ መብት አላቸው፡፡” በማለት ይገልጣል፡፡ (ሕ/መን.አን.20(3)) ነገር ግን “ሕጻናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ፥ ወይም በግል የበጎ አድራጎት ተቋሞች ባለ ሥልጣኖች ወይም በሕግ አውጪ አካላት፥ የሕጻናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት፡፡”
    በቀደምትነት መታሰብ ያለበት ብቻ ሳይሆን ፦
“ማንኛውም ሕጻን ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ ፥ በትምህርቱ፥ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ መብትም እንዳለው” በግልጥ አስቀምጧል፡፡
(ሕገ መን.አን.36(1)መ)

Wednesday, 28 October 2015

ኢየሱስን የሚጋርዱ - ባህላዊ “ሰባኪ” ዎቻችን



       
                                                 Please read in PDF

     የክርስቶስ አገልጋይ ትጥቁ አጭር (ማቴ.10፥5-11) ፤ ዕለት ዕለት መስቀሉን ተሸክሞ በመከተል የሚኖር (ማር.8፥34) ፤በቁም ሳለ ከሚገድል ቅምጥልነት የራቀና “ወደዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።” የሚል ቅዱስ አቋም ያለው (1ጢሞ.5፥6 ፤ 6፥7-8) ፤ በሕይወቱ (ሮሜ.12፥2) ፣ በንግግሩ (ቈላ.4፥6) ፣ በመንገዱ ሁሉ የአምላኩን ስም የሚያስመሠግንና ከማስነቀፍ ፈጽሞ የራቀ ፤ ለሁልጊዜ ለፈጣሪው የሚያደላና የሚኖር ፤ ለሕይወቱ ምሳሌና መርሕ የሚሆነውን ነገር ለመፈለግ ሁልጊዜ እግረ ልቡን ወደ ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ የሚያቀና ሊሆን ይገባዋል፡፡ (ሐዋ.17፥10 ፤ 1ዮሐ.4፥1)
እንዲህ ስል አገልጋይ ባዕለ ጠጋ መሆን የለበትም የሚል አቋም የለኝም ፤ ዳሩ ግን አማኝም ሆነ አገልጋይ መሠረታዊ የሆነውን ነገር፥ ማለትም ምግብን ፣ ልብስንና መጠለያ በማግኘቱ ፣ እርካታ ይኖረው ዘንድ አስፈላጊ ፤ የተገባም ነው፡፡ ይህ ማለት አገልጋይ እንደሚሠራው ሁሉ አገባብ ያለው ደመወዙ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ገንዘብ የሚጠይቅ የተለየ ነገ ርቢከሰት ፣ በልግስና በመስጠት እግዚአብሔርን እያገለገለ (2ቆሮ.8፥3 ፤ 9፥6) “በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ።” እንዲል፥ እግዚአብሔር እንዲሰጠው ወደእርሱ መመልከት ይኖርበታል፡፡ (መዝ.50፣15) ይህንን የምንለው ሁልጊዜ መንግሥቱንና ጽድቁን መቅደምና ማስከተል ከሌለብን ብቻ ነው፡፡ (ማቴ.6፥33)

Friday, 23 October 2015

የፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ንግግር ሳጤነው ምጥ አለበት!!!


ብዙዎች ያልጨከንለትና ያልደፈርንለት እውነት!!!

      በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተካሄደው 34  መደበኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ፥ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥቅምት 8 ቀን  2008 ዓ.ም ካስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የሚከተለው መልዕክት ላይ ማተኮር ፈለግሁ፡፡
 
“ … የምዕመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ የመሄዱ መነሻ ምስጢር ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ልታጤነው ይገባል ፤ በዚህ ዙርያ የሚታየው ክፍተት ፈጣን ምላሽ በመስጠት መግቻ ካላበጀንለት ነገ ከባድ የሃይማኖትና የታሪክ ወቀሳ ማስከተሉ እንደማይቀር ልብ እንበል፡፡
     ለመሆኑ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ  ወደሌላ ካምብ ለመግባት ለምን መረጡ?
-       የሚያስተምራቸውን ካህን አጥተው ነውን?
-       የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት ነው?
-       የቤተ ክርስቲያችን አስተዳደር የማያረካ ሆኖ ነውን?
-       የካህን እጥረት ስላለ ነውን?
-       ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው፤?
የዚህ ሁሉ መልስ በእያንዳንዳችን ኅሊና ውስጥ ቁልጭ ብሎ ስለሚታወቅ የጥያቄው መልስ ለእናንተው ሰጥተናል፡፡  … ”

     ደግሞም ልቀጥል፦ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መጀመርን አስመልክቶ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም  ቅዱስነታቸው በሰጡትም መግለጫም እንዲህ አሉ፦

Wednesday, 21 October 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት ክፍል - 5






4.  በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የተመላችም ነበረች

     ደስታ ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ (ገላ.5፥22) ደስታ፥ የመብልና የመጠጥ ፣ በወገን መካከልም የመቀመጥ ፣ በተድላ የመንቀባረር ፣ የመልበስና የማማር ጉዳይም አይደለም ፤ ተድላና ደስታን ለማየት ለመቅመስም የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ያሻል፡፡ “ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” (መክ.2፥25) እንዲል ደስታችንም ፍጹም የሚሆነው በእርሱ ብቻ ነው፡፡ (ዮሐ.15፥11) ዘወትር ለሁልጊዜ በጌታ ልንደሰት እንደሚገባንም ቃሉ ይነግረናል፡፡ (ፊልጵ.4፥4 ፤ 1ተሰ.5፥16)
    ድንግል ማርያም ትልቁ ሐሴትና ደስታዋ በእግዚአብሔር መድኃኒትነት ላይ ያላት መደገፍ ነው፡፡ “መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” የሚለው መዝሙሯ፥ “እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።” (መዝ.18፥46) ከሚለው ከዳዊት መዝሙር ጋር ፤ “ … የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፥ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች።” (ኢሳ.61፥10) ከሚለው ከኢሳይያስ መወድስ ጋር ፤ “ … እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕንባ.3፥18) ከሚለው ከዕንባቆም የጽናት ዝማሬ ጋር ፍጹም የሚዛመድ ነው፡፡

Tuesday, 13 October 2015

አድመኝነት - ከማን የተማርነው ነው?



      
                                   Please read in PDF
            

   ጌታ ኢየሱስ በተያዘባት በሐሙስ ማታው ግርግር፥ ደቀ መዛሙርት አይሁድ ጌታን ቆርጠው ለመግደል በብዙ ጦርና አድማ ተደራጅተው ምክራቸውን እንደጨረሱ ሲያውቁ ፦ “ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት።” (ሉቃ.22፥38) የአይሁድ የካህናት አለቆች ሙሉ ለሙሉ በአድማ ሲነሳሱ ስላዩ፥ ደቀ መዛሙርቱም ምላሽ ለመስጠት በሰይፍ ለሚያስታጥቅ አድማ ለራሳቸው ተዘጋጁ፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንዳያደርጉት በምፀት ቃል “ይበቃል” ቢላቸውም፥ እነርሱ ግን ቃል በቃል ተርጉመው፥ አድማቸውን ወደጥቃት አሸጋግረው የአንዱን ወታደር ጆሮ በመቁረጥ ደመደሙ፡፡ ጌታ ግን “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።” በማለት በተግሳጽ ቃል ተናገረ፡፡ (ማቴ.26፥52)
     ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ከእነርሱ ጋር የተስማማ መስሏቸው ይህን ቢያደርጉም፥ ጌታ ግን ድርጊቱን አብዝቶ ተጠይፏል፡፡ በእርግጥም አድመኝነት የሥጋ ፍሬ ነው ፤ (ገላ.5፥20) ትርጉሙንም ስናሰላስለው ለመለያየት የመጀመርያ ምልክት የሆነ ፤ የግል መሻትና ፍላጎት ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጠር መለያየት ፤ በፍጻሜም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያጠፋ  ወይም የሚቃወም ድርጊት ነው፡፡ ይህም በአንድ ሃሳብ የሚስማሙና የግል ሃሳባቸውን የሚያስቀድሙ ሰዎች ወገናዊነትን ፤ እኛዊነትን ፤ እኔዊነትን በመፍጠር ፥ በሌላው ላይ በማሾክሾክ ፤ በማማት ፤ በመጥላትም ጭምር ራሳቸውን በማግለል ቡድናዊነትን በመመሥረት በሌላው ላይ የበላይነትን ለማሳየት የሚያደርጉት ድርጊት ነው፡

Wednesday, 7 October 2015

አንተ ስትደክም …


          Please read in PDF                     


ብትጠቁር ብትከሳ
ብትሞግግ በአበሳ
አጀቡ የሐዘን
ምትክህ ሰቀቀን …

Friday, 2 October 2015

ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቃወም ሙጋቤያዊ አቋምም ከመሪዎቻችን ያስፈልጋል!

   
                          Please read in PDF     

                        እኛ ግብረ ሰዶማውያን አይደለንም!!!” (ሮበርት ሙጋቤ)


    በዘመናችን መንፈሳዊ ማንነታችን ስለተጐሳቆለብን ኃጢአትን በአለም መድረክ የሚቃወሙት አለማውያን መሪዎች፥ ከእኛ ይልቅ በብዙዎች ዘንድ የመደመጥን ዕድል ያገኙ ይመስላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ፍጹም ስትዋብ በአለማውያን መሪዎች ላይ ተጽዕኖ ስለማሳደሯ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መለያ ባሕርያት መካከል አንዱ ክርስቶስ በገዛ ደሙ መሥርቷታልና ቅድስት መሆኗ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቅድስናን ጠባይ ገንዘብ ያደረገችው፥ ከመሠረታትና ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሚሆን ከክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡
     ቤተ ክርስቲያን ከአለማውያን መሪዎች ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ ጤናማ መሆን አለበት፡፡ ግንኙነቱ ጤናማ መሆን አለበት ስንል፥ መርሑ ቅድስናና ንጽሕናን ብቻ በተከተለ መንገድ መሆን መቻል አለበት ማለታችን ነው፡፡ ቅድስና በኃጢአተኛው ላይ እጅግ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በስደት ዘመን የሰማዕታትን አንገት ይቀሉ የነበሩት ወታደሮች፥ በሚያስደንቅ መንገድ የጌታ ባለሟሎች የሆኑትና ከመግደል ለጌታ እስከመሞት የደረሱት የሰማዕታቱን የቅድስና ጉልበት አንገት በመቁረጥ ፤ በማቃጠልና በብዙ መከራ ማሸነፍ ስላልቻሉ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የክርስቶስ ኢየሱስን ሕይወትና ቃሉን እጅግ በመውደድና በማንበብ ለአገራቸው ሕዝቦች እጅግ ቅን የነበሩትን እንደመሃተመ ጋንዲ ያሉ መሪዎችንም ማንሳትም ይቻላል፡፡

Tuesday, 29 September 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት ክፍል - 4


                             Please read in PDF          

3.  እምነት

      ያለእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ፤ ያለእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ካልተቻለ ልናምን የሚገባን እግዚአብሔርን ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ (ዕብ.11፥6) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ላይ ሁለት ጊዜ የተደነቀውና ምስክርነትም የሰጠው ከእስራኤል መካከል ያጣውን እምነት ከአህዛባውያን አማኞች በማግኘቱ ነው፡፡ (ማቴ.15፥28 ፤ ሉቃ.7፥9) ብዙ ቅዱሳንም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙት “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” እንዲል በእምነታቸው ነው፡፡ (ዕብ.11፥4 ፤ 5 ፤ 7 ፤ 8 ፤ 17 ፤ 20 ፤ 21 ፤ 22 ፤ 23 ፤ 28-40)

Saturday, 26 September 2015

መስቀልና ራስን (እኔነትን) መካድ

     
                            Please read in PDF      

   ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከመሰቀሉ በፊት ስለመስቀሉ፥ “ … መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” (ማቴ.10፥38) በማለት አስተማረ፡፡ በአሁን ጊዜ፥ ይህ የጌታችን ትምህርት ከመሰቀሉ በፊት እንደተናገረውና እንደተጻፈው ሃሳብ ሳይሆን እንደራስ ሃሳብ ከሚተረጎሙ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ በእርግጥም ጌታችን ከመሰቀሉ በፊት ሰሚዎቹ መስቀልን እንዴት ነበር ሲረዱት የነበረው? ጸሐፊው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊስ ሰሚዎቹ እንዴት መረዳታቸውን አስተውሎ ይሆን የጻፈው? “መስቀል” ተብሎ የተነገረው ቃል ጌታ ከመሰቀሉ በፊትና ከተሰቀለ በኋላ ሁለት አይነት መልክ አለው ወይም የቃሉ ሃሳብ አንድና አንድ ነው? ሰሚዎቹ ያስተዋሉት መስቀል ጌታ ወደፊት የተሰቀለበትን መስቀል ነው ወይስ ጌታ የዚያኔ ሊናገር ያሰበውን ነው? እኛስ እንዴት ነው እየተረዳን ያለነው? የሚለውን ሐቲታዊ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ሃሳቡን የጌታን ሃሳብ በአገባቡ ለመረዳት ያግዘናል፡፡
     “ታላላቅ” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ አንድና ወጥነት ያለው መሆኑን በመስማማት ቃል ይናገራሉ፡፡  ከሁሉም ይልቅ ደግሞ ወንጌላውያን ወንጌልን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወይም ቃኚነት ሲጽፉ ታሪክ ቀመስ እንደመሆኑ መጠን አንዳች በማያቅማማ ሁኔታ የጌታችንን ቀጥተኛ ንግግሮችንና ትምህርቶችን አስፍረውታል፡፡  መንፈስ ቅዱስ፥ ቅዱሳን አባቶችን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲጽፉ ሲነዳቸው ውስብስብና እንዳይገባቸው ወይም እንዳይገባን አድርጎ አልገለጠም ፤ አላጻፈውምም፡፡  በእርግጥም “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” (ኢሳ.54፥13 ፤ ዮሐ.6፥45) ተብሎ እንደተነገረ፥ የሚድኑትና የዘላለም ሕይወትን የሚያገኙት ስለእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ከራሱ የተማሩት ብቻ ናቸው፡፡

Thursday, 17 September 2015

እኔን ዛሬ ማረው!




ጉብዝናዬን ላ’ጢአት ፣ ብርታቴን ለነውር ፤
ውበቴን ለወጥመድ ፣ አውዬ የማድር ፤
እኔ ነኝ ጌታዬ ፣ እኔ ነኝ ፣ እኔ ነኝ፤
በግ ከሚያርዱ ጋራ ፣ እሳት ስሞቅ ’ምገኝ፡፡

Wednesday, 9 September 2015

ዘመናችን የመባረኪያው ምስጢር



እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ፡፡ አሜን፡፡

       መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሚለውን ቃል፥ አንድ ረዥም ጊዜን (ገላ.4፥4) ፣ የአንድ ወቅት አገዛዝን (ማቴ.2፥1-2 ፤ ሐዋ.12፥1) ፣ አንዳንዴ ሰዓት በሚለው አገላለጥ አምልኮን ወይም የመዳንን ጊዜ (ማር.1፥15 ፤ 2ቆሮ.6፥2 ፤ኤፌ.2፥6 ፤ 2ጢሞ.1፥9) ፣ ሌላም ተግባር የተከናወነበትን ወይም የሚከናወንበትን ጊዜ (1ጢሞ.4፥1-2 ፤ 1ጴጥ.1፥5-6) ፣ ውስን ጊዜንና (መዝ.102፥24) የመሲህ ኢየሱስ በምድር የነበረበትን ጊዜና (1ጢሞ.2፥6 ፤ ዕብ.1፥1) ሌሎችንም ለማመልከት ቃሉን ይጠቀምበታል፡፡  ስለዚህ ዘመን የሚለውን ቃል እንደሚገኝበት አውዱ፥ በጥንቃቄ ልናየውና ልንተረጎመው ይገባናል ማለት ነው፡፡
   ጊዜያትን የፈጠረ፥ “የዘመኑ ቍጥር የማይመረመር” (ኢዮ.36፥26) ፣ “ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ  … አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።”(መዝ.90፥2 ፤ 102፥27) የተባለለት ቅዱስ  እግዚአብሔር ነው፡፡ (ዘፍጥ.1፥5 ፤ መዝ.102፥24) ስለዚህም ዘመን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች በስጦታነት ተሰፍሮ ፤ እንኖርበት ዘንድ የተሰጠን በረከት ነው፡፡ ( ዘፍጥ.6፥3 ፤ ኢዮ.14፥5 ፤ 21፥21 ፤ 31፥15 ፤ 39፥4-5 ፤ 139፥16 ፤ ሐዋ.17፥26) የዘመናችን መርሑም አንዱ ሲያልፍ ሌላው እንዲተካ “በብዙ ተባዙ” (ዘፍጥ.1፥28 ፤ 9፥1) ፤ በማለፍ ሕግ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ (መዝ.103፥15)

Saturday, 29 August 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት (ክፍል - 3)

1.    ምስጋና
       ለምስጋና የተሟሸ ቃል የምናወጣው፥ መንፈስ ቅዱስ አንደበታችንን ሲቃኘውና እኛም ቃሉን ከጸሎት ጋር በማጥናት የበሰለ ማንነትን መያዝ ሲቻለን ነው፡፡ እንዳንዶች ተአምራቱን አይተው ድንቅ መዝሙርን (ዘጸ.15፥1-21) ፤ አንዳንዶች በፊቱ ራሳቸውን በማፍሰስ ላደረሱት ጸሎት ምለሹን ከለመኑት ጌታ ባገኙ ጊዜ (1ሳሙ.2፥1-10) ፤ ሌሎች ደግሞ ድልን በፊቱ ባገኙ ጊዜ (መሳ.5፥1-31 ፤ 16፥24) ፤ የበረቱቱ ደግሞ ሙሉ ተስፋቸው እግዚአብሔር መሆኑን በመታመን (ዕን.3፥1-19) በእግዚአብሔር ፊት እንደዘመሩ ድንግል ማርያምም ልዩና ድንቅ ነገር በእርሷ እንደተደረገ ባመነች ጊዜ በቃሉ መሞላት ውስጥ ሆና የዘመረችው መዝሙር እጅጉን ልብ የሚነካ ነው፡፡
      አባቷ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት (ማቴ.1፥20 ፤ ሉቃ.1፥27 ፤ 32) በገና እየደረደረ መልካም አድርጎ ይዘምር የነበረ መዝሙረኛ (1ሳሙ.16፥18-23 ፤ መዝ.33፥2) ፤ የመዝሙር መጽሐፎቹም በምስጋናና በውዳሴ እጅግ የተመሉ ነበሩ፡፡ (መዝ.111-117) ድንግል ማርያምም ከእርሱም ተምራለችና በምስጋና ተመልታ ስታመሰግን እናያታለን፡፡ ቃሉም ፥ “… በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” (1ተሰ.5፥17-18) እንዲል፡፡
       ምስጋና የማጉረምረም ፤ የሽንገላ ፤ የሐሰተኝነት ፤ የስድብና ያለማመስገን ተቃራኒ ነው፡፡ (ዘጸ.16፥2 ፤ ዘኊል.14፥26-30) ዲያብሎስ ዘማሪ ስለነበር ፥ ከዚህ ክብሩ በገዛ ትዕቢቱ ሲዋረድና ሲወርድ ሸንጋይ (ኤፌ.4፥14 ፤ 6፥11) ፣ የእግዚአብሔርን ክብርና ሥራ በመንቀፍ የሚሳደብ (መዝ.74፥10 ፤ ኢሳ.52፥5 ፤ ራዕ.13፥5) ፣ በድምጹ ብቻ እያገሳ የሚያስፈራራ (1ጴጥ.5፥8) ፣ ሐሰተኛ (ዮሐ.8፥44) ሆነ፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔርን (ዘሌ.24፥16 ፤ 1ነገ.20፥10) ፤ እናትና አባቱን የሚሰድብ (ዘጸ.21፥17 ፤ ምሳ.20፥20) እንዲገደል ፍርዱ እንዲሆን በሕግ የተደነገገው፡፡

Wednesday, 19 August 2015

አርሞንዔም - ጌታ ክብሩን የገለጠበት ተራራ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስድስት ቀን በፊት በጥንት ስሟ “ፓኒያስ” ፥ በአሁን ስሟ ደግሞ “በናያስ” በምትባለው ከገሊላ ባሕር በስተሰሜን ከሔርሞን ተራራ ተዳፋት ሥር በነበረችው በፊልጶስ ቂሣርያ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፡፡” (ማቴ.16፥13) ንጹሐ ባሕርይው ጌታ፥ ደካሞችና ገና በእውቀት ያልጎለመሱትን ደቀ መዛሙርት “ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም የሰሙትን ሁሉ ሳያስቀሩ ነገሩት፡፡ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው” ብለው ተናገሩ፡፡ ሰዎች ስለጌታ የሰጡት ስያሜ፥ ቀርበውት ያዩት ወይም ከእርሱ የሰሙት አይደለም፡፡ የየራሳቸውንና ከሌሎች ጋር ሲያወሩት የደረሱበት “እምነታቸውን” እንጂ፡፡
      ሰዎች ስለእኛ የሚሉት አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር አላቸው ፤ የሚሉት ነገርም ከእኛ ጋር ምንም ዝምድና ያለውም ፤ የሌለውም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ስለጌታ የተናገሩት ከእርሱ ጋር ምንም ዝምድና የሌለውን ነው፡፡ እኛም በተለይ ከታወቀ ነውርና ከኃጢአት ሕይወት ነጽተን በእውነተኛው በጌታ ወንጌል አገልግሎት ውስጥ ስንመላለስና ቤተ ክርስቲያንን በቅዱስ ቅንአት ስናገለግል ብዙ ጊዜ የምንባለው፥ ከእኛ ጋር ምንም ዝምድና የሌለው ነገር እንደሆነ ከዚሁ ለጌታ ከተነገረውና ከደቀ መዛሙርቱ ሕይወት እንማራለን፡፡ (ማቴ.9፥34 ፤ 12፥24 ፤ ሐዋ.21፥37-38 ፤ 24፥5-6) ስለዚህ ብዙ መባላችን ፤ ተብሎም በድርጊት ቢገለጥ ምንም ሊያስደንቀን ፤ ሊያስበረግገንም አይገባም፡፡ (1ጴጥ.4፥12)
    ጌታችን ሁሉንም ነገር ከደቀ መዛሙርቱ ካደመጠ በኋላ ጥያቄውን፥ “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” በማለት የጥያቄውን አቅጣጫ ወደእነርሱ ቀየረው፡፡ በአገልግሎት አለም ከብዙ አማኞችና አገልጋዮች ሕይወት የራቀው ጥያቄ ቢኖር ይህ ጥያቄ ነው፡፡ በዙርያችንም ያሉ ይሁኑ ከአጠገባችን ያሉ ምን እንደሚሉን በትክክል አለመረዳት ብዙ ጊዜ የንስሐ በራችንን እንኳ ሲዘጋብን ከማስተዋል እንዘነጋለን፡፡ አንድ አገልጋይ ወይም አማኝ የእግዚአብሔር ቤት እውነተኛ አገልጋዮችና አማኞች ለእርሱ ያላቸውን ነገር በሚገባ ማጤን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ስል አገልግሎቱን ሁሉ በጌታ ከመደገፍ ይልቅ በእነርሱ ቅኝት ሊመራ ይገባዋል እያልኩ አይደለም፡፡

Saturday, 15 August 2015

እንደብዙ አጋር!


          Please read in PDF


እንደሚራራ እንደሚያሻግር
እንደሚያጽናና እንደሚያፈቅር
ከጐን እንዳለ ቀኝ ደግፎ
በብርታት ቆሞ በድካም ታቅፎ

Tuesday, 11 August 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት ስትገለጥ(ክፍል - 2)



         ድንግል ማርያም የክርስቶስ የቃሉ ሙላት እንዳላት በታላቁ መጽሐፍ ከዘመረችው መዝሙር ዋቢ ብንጠቅስ ፥ ለምሳሌ ፦
  
       ነፍሴ ጌታዬን ታከብረዋለች ፤ (መዝ.34፥2 ፤ 44፥8 ፤ 103፥1-4) ድንግል ማርያም የወለደችውን ጌታ “ጌታዬ” ብላ ታከብረዋለች ፤ ታመልከዋለችም፡፡ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች” እንዲል ፤ እርሷ ፈጣሪዋን ታከብረዋለች ፤ በፍርሃት ታመልከዋለችውም፡፡
       መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች ፤ ( መዝ.18፥46 ፤ 42፥11 ፤ 43፥5 ፤ 69፥32 ፤ 107፥42 ፤ 119፥74 ፤ ኢሳ.45፥15-17 ፤ 45፥21 ፤ 61፥10 ፤ ኤር.9፥24 ፤ ሆሴ.13፥4 ፤ ዕን.3፥18 ፤ 1ጢሞ.2፥3 ፤ 4፥10) የወለደችውን ያንኑ ጌታዋን “መድኃኒቴ” ብላም ትጠራዋለች፡፡ መድኃኒቱ ለእርሷም ፤ ለእኛም ፤ ለአለሙ ሁሉ ነውና፡፡