በአገራችን ትኩረትን የሚስበው ድርጊት
እንጂ ዝግጅት አይደለም፤ አንድ ከባድና ዘግናኝ ድርጊት ሲፈጸም ብዙ ጊዜ ስሜቶቻችን ተጋግሎ መንጫጫት፤ ድርጊቱ እንዳይፈጸም ቀድመን
ከመሥራት ይልቅ ከድርጊቱ በኋላ በጣም መጯጯህ ፣ ሰላማዊ ሰልፎች ፣ ብዙ ስብሰባዎች ፣ የአቋም መግለጫዎችና የስሜት ዕርምጃዎችም
ይወሰዳሉ፡፡ ማሳያዎችን በምሳሌ ብናነሳ፦ በባለፈው ወር የአዋሽ ፓርክን
በሚያቋርጠው ትልቁ የምሥራቅ ኢትዮጲያ መንገድ በጉዞ ላይ ሳለ በአንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ ላይ በደረሰው አደጋ ከሐያ ሰባት ሰዎች በላይ
የሞት አደጋ መድረሱን ሰምተን ሳናባራ፤ ወዲያውኑ በተወሰደው እርምጃ መንገዶች ላይ በተደረገው (በዋናው አስፓልት ላይ መኪናዎች
በጉዟቸው እንዲያቀዘቅዙ ለማድረግ በተደረገው ሌላ የአስፓልት ጉማጅ ሥራ) በተወሰደው የስሜት ዕርምጃ ሌሎች የመኪና አደጋዎች መከሰታቸውን
ከቦታው ሄዶ ማስተዋል ይቻላል፡፡
አሁንም ሌላ ማሳያ ብናነሳ ፦ በባለፈው ወር ከተከሰተው ጆሮን ጭው ከሚያደርጉ
ነገሮች አንዱ የእህት ሐና ላላንጎ ጉዳይ ነው፡፡ ድርጊቱ ከዳር እስከዳር
ብዙ በጣም ብዙ አነጋግሯል፡፡ ከወረዳ እስከ ሚኒስቴር ቢሮ ፤ ከሆስፒታል እስከ የፖሊስ መምሪያና ጣቢያዎች ፤ ከመንገድ ዳር “ታዛቢ”
እስከመኪና አሽከርካሪዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ያሉበትን ልልነትና ግድ የለሽነት በሚገባ አጢነናል፡፡ ጥቂት ስህተት ምን ያህል ዋጋ
እንደሚያስከፍል አይተናል፡፡ የፖሊስ ዳተኝት ፣ የሆስፒታሎቻችን ከልክ ያለፈ ቸለተኝነት ድርጊቱን ከፈጸሙት የማይተናነስ መሆኑን
ሌላ ምስክር ሳያሻ የአደባባይ ገመና ሆኗል፡፡
