ደቀ መዛሙርቱ የተወራውን ወሬ በማመናቸው ሲጠራጠሩ ታይተዋል፡፡የመግደሎሟ
ሴት “ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም … አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ”(ዮሐ.20፥13-16)
ማለቷ መሰረቁንና መወሰዱን ያመነች ይመስላል፡፡ጌታ ስለዚህ አለማመኗ “አትንኪኝ” በማለት ወቅሷታል፡፡ማርያም መግደላዊት ቀድሞ የት
እንዳኖሩት ወይም እንደቀበሩት ቆማ ተመልክታ ነበር ግና ከመነሳቱ መሰረቁን ተቀበለች፡፡(ማር.15፥47)፡፡የጠላት ወሬ ምን ያህል
ልብ እንደሚለውጥ አስቡ! ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ እነሳለሁ ያላቸውን ጌታ ረስተው፤ ቃሉን ዘንግተው ግን የተወራውን አብልጠው ተቀበሉ፡፡ደቀ
መዛሙርቱ ከወንጌሉ ይልቅ ለጊዜውም ቢሆን የጠላትን ወሬ ማመናቸው እጅግ ይደንቃል!
በእርግጥም የዛሬ ዘመን እልፍ አገልጋዮችና አማኞች የሚፈሩት ነገር ከሌላ
ወገን የሚወራን ወሬ ነው፡፡ከሁሉ ይልቅ በተለይ ብዙዎች አገልጋይና አማኞች በኢየሱስና በስሙ መታማት አንፈልግም፡፡ምክንያቱም ስሙን
ከደጋገምን አንድ ከባድ የሚለጠፍብን ታርጋ አለ፡፡“ጴንጤ ፣ተሐድሶ፣ጸረ ማርያም፣ጸረ ቅዱሳን፣መናፍቅ … ”የሚሉና ሌሎችም፡፡ ብዙ
ጊዜ የክርስቶስ ስሙን ለሆዳቸው የሚቸረችሩ አገልጋይና አማኞችን በማየቴ ብዙም አልደነቅም፡፡ነገር ግን ለእውነት ሳንቆም በገና ለገና
የሰው ወሬ የምንፈራ ከሆንን እውነተኛ ምስክር መሆናችን አይገለጥም፡፡
ወሬው በጊዜው ቀላል አይደለም፡፡ማቴዎስ ወንጌሉን ይጽፍ በነበረበት ዘመን
እንኳ ተሰርቋል የሚለው ወሬ በአይሁድ ዘንድ በጣም ይወራ ነበር፡፡(ማቴ.28፥15) አዎ! ታርጋ ከተለጠፈብን በኋላ ስለምንናገረው
እውነት ሰሚ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ለልባችን ቅርብ የነበሩቱ እንኳ በወሬው ብቻ በጠላትነት ጎራ ሊሰለፉብን ፣የማያውቁን አይናቸውን
ጨፍነውና በጨው አጥበው ስማችንን ጥላሸት ሲቀቡት ተለምዶ፣ተዋህዶ፣ሥርዓት ሆኖ ይኸው እያየን ነውና በእርግጥም ያማል፡፡
በተለይ መገናኛ ብዙሃን ለእውነት ሳይቆሙና ሳይቀኑ በእንቶፈንቶ ቋታቸውን ሲሞሉ
ለሀገርና ለወገን የሚረባውን ትተው ተራ ወሬና ያልተባለን እየቀጣጠሉ ሲያወሩና እንደመቃኞ በሬ ሰዎችን ሲነዱ ማየት የበለጠ ልብ
ይሰብራል፡፡ ብናስተውል ፖለቲካችን ያልተፈወሰው፣ስብከታችን የጠነዛው፣ክህነታችን የገረጀፈው፣ድቁናችን የነቀዘው፣ ቅስናችን የተናቀው፣ጵጵስናችን
የተነቀፈው፣ ንግግራችን የተጠላው … ወሬን ማለፍ ስላልቻለና ከተግባራችን ጋር ፍጹም ዝምድና ስለሌለው ነው፡፡