Friday, 27 November 2026

ፍትሕ ማድረግ ይሻላል!

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹም ኀጢአተኞች ይልቅ፣ የሃይማኖት ካባ የለበሱ ጻድቃን መሳይ ግብዞችን አብዝቶ ይጠየፋል፤ ምክንያቱም ፈሪሳውያን ለሕጉ የቀኑ በመምሰል በንቀትና በጥላቻ የታወሩ፤ ከእግዚአብሔርም ይልቅ ለራሳቸው ጥቅምና ድሎት አብዝተው የሚጨነቁ እንጂ አንዳችም ለእግዚአብሔር ክብርና ለኀጢአተኞች መዳን የሚጨነቁ አልነበሩምና። ከዚህ የተነሣ የሃይማኖትን ሥርዓት ያለ ፍትሕና ምሕረት ትርጕም አሳጥተውት ነበር።  ነቢያት አባቶቻቸው ግን ሲወቅሱአቸው የነበረው፣ “አንተ ሰው ሆይ፥ መልካም የሆነውን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትመላለስ ዘንድ አይደለምን?” (ሚል. 6፥8) በማለት ነበር። ግን አልሰሙአቸውም!

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ፣ “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፥ የተበደሉትን አድኑ፥ ለድሀ አደግ ፍረዱ፥ ለመበለት ተሟገቱ።” (1፥17) ሲል፣ ገዢዎች እኒህ የተጠቀሱትን ሰዎች መደበል እንደሌለባቸው አበክሮ ይናገራል። እንዲሁም ጠቢቡ ሰለሞን፣ “ለድዳውና ስለ ባለዕዳዎች ሁሉ አፍህን ክፈት፤ አፍህን ክፈት፥ በጽድቅም ፍረድ፥ ለድሀውና ለችግረኛውም ፍረድ።” (31፥8-9) በማለት ሲናገር፣ ነገሥታት ወይም ገዢዎች የእግዚአብሔር ተወካይ ኾነው ድኾችንና ችጋረኞችን መጠበቅ እንዳለባቸው ፈጽሞ ያመለክታል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፣ ሕግ እናውቃለን በማለት የሳቱ ሕግ አዋቂ ፈሪሳውያንን እንዲህ በማለት ወቅሷቸዋል፤ “ከሕግ የሚበልጠውን ፍርድንና ምሕረትንና ታማኝነትን፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።” (ማቴ. 23፥23)። በትክክል አለመፍረድ ብቻ ሳይኾን፣ ፍርድን ከምሕረትና ከታማኝነት ነጥሎ ማየት በደል ነው። ምድራውያን ዳኞች በትክክል እንዲፈርዱ፣ የሃይማኖት ሰዎች ደግሞ ትክክለኛ ፍርድ ብቻ ሳይኾን ምሕረትና ታማኝነትን ጭምር ገንዘብ ሊያደርጉ ይበልጥ ይገባቸዋል።

ታድያ ምድራውያን ገዢዎች ይህን ያህል አደራ ከተጣለባቸው፣ መንፈሳውያን መሪዎችማ ከዚህ እጅግ በተሻለ መንገድ ጨውነታቸው ጣፍጦ፤ ብርሃንነታቸው በርቶ ለሌሎች ሊታይ ይገባዋል። ዛሬ ላይ በተቃራኒው ግን “መንፈሳዊ መሪ” የተባሉ አካላት በጉቦና በሙስና ቅሌት ተጨማልቀው ሲያበቁ፣ ነውራቸው እንዳይገለጥና እንዳይነገር የማይቆፍሩት ጉድጓድ፤ የማይምሱት ምስ አለመኖሩን ስናስብ እንደነቃለን፤ እንሳቀቃለን፤ ከዚያም እጅግ በከፋ መንገድ፣ ይህ ቅጥ ያጣ ክፋታቸውን ንስሐ እንዲገቡና እንዲመከሩ ሲነገራቸው፣ ከዓለማውያን የፍትሕ አካላት ጋር በመሻረክ ሰዎችን ለማሳሰር መጨከናቸውን ስናስብ፣ መንፈሳዊ መሪነታቸውን እንጠራጠራለን።

የቱንም ያህል ግን ክፉና መረን የለሽ ቢኾኑ፣ እንዴት ሰው ማሳሰርንና እውነትን ለማፈን ጥግ ድረስ መሄድን መረጡ?! ነውር የዳቦ ስም የለውም፤ ኀጢአትም ስሙ ኀጢአት ብቻ ነው! በምንም መንገድ የገዛ ወንድምን አሳስሮ፣ መንፈሳዊ ነኝ ማለት፣ ገብርኤልን የሰይጣን ሎሌ ለማድረግ የማለምና የመመኘት ያህል ነው፤ ጨርሶ አይቻልም!

አንድ እውነት ግን ለዘላለም እናምናለን፤ እንዲህ ያለ ፈሪሳዊነት፤ በሃይማኖት ካባ ተደብቆ የራስን ክብርና ዝና የማቆም ሃውልት፤ ራስን የማምለክ ጣዖት አምልኮ ለዘላለም አይቀጥልም፤ ኢየሱስ ሲመጣ ኹሉ እንደ ሥራው የእጁን ይቀበላል፤ ጠቢቡ እንዲህ ይላል፣ “እግዚአብሔር በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ ይፈርዳል፤ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ በዚያ ጊዜ አለ።” (መክ. 3፥17) አዎን፤ አሳሪዎችን፤ አሳሳሪዎችንም ፈራጅ በደጅ እንዳለ ልናስታውሳቸው ይገባል፤ ምናልባት እኮ፣ የሃይማኖት መሪዎችም ኾነው ይህን የማያውቁ ሊኖሩ ይችላሉ!

No comments:

Post a Comment