የእውነተኛ ዓቃብያነ እምነት ሕመም!
በራሳችን ድካምና የኀጢአት ውድቀት የሚደርስብንን መናቅና ስድብ መታገሥ አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔርና ስለ ስሙ መታገሥና መከራ መቀበል እጅግ ሌላ ነገር ነው። ዓለሙ በክፉ እንደ ተያዘ ለሚያውቅ አማኝ (1ዮሐ. 5፥19)፣ ከእግዚአብሔር ጋር በመወገኑ ብቻ ለዓለሙና ለወገኖቹ መሳለቂያ ሊኾን ይችላል።ዘማሪው እውነተኛ ጻድቅ ነውና፣ ለሕዝቡ ኀጢአት ለማልቀስ ማቅ በለበሰ ጊዜ፣ እየተዘባበቱ ስቀውበታል (69፥11)፤ “በአደባባይ የሚቀመጡት ያሙኛል፤ ሰካራሞች በዘፈን ይሰድቡኛል” (ቊ. 12) እንዲል።
በዓለሙ ፊት ለእግዚአብሔር በጽድቅ
ምስክር መኾን፣ ለብዙዎች መጠቋቆሚያና ለስድብ ተጋላጭ ሊያደርገን፣ ደግሞም ይህ ስድብ ምናልባት ከገዛ ወገናችንና ቤተ ሰባችን
ሊገጥመን ይችላል። ዘማሪው እንደ ዘመረው፣ በወንድሞቹ እንኳ ሳይቀር እንግዳና ባይተዋር፤ ባዕድ የመኾን ዕጣ ደርሶበታል። ለእግዚአብሔር
በእግዚአብሔር ጸንቶ መቆም፣ በስሙ መከራና ስድብን መቀበልና መታገሥ፣ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት
ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ”
የሚል አምላካዊ ምስጉንነትን ያጐናጽፋል፤ (ማቴ. 5፥11)።
በርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር መቆም በዚህ
ምድር ላይ በጉድለትና በስብራት ሊያመላልስ ይችላል፤ ልክ መዝሙረኛው በእግዚአብሔር ፊት በጾመና ባለቀሰ ጊዜ፣ የገዛ ቤተ ሰቦቹ
እንደ ቀለዱበትና እንዳላከበሩት (69፥10)። ጌታችን ኢየሱስ በነበረበት ዘመን፣ የክብሩ መቅደስ ለሌላና ከእግዚአብሔር ፈቃድ
ውጭ ለኾነ ዓላማ በዋለ ጊዜ፣ መቅደሱን ለማንጻት ይህን የቅዱስ ቃሉን ክፍል ጠቅሶአል።
ጌታችን ኢየሱስ በመቅደሱ ላይ
የተፈጸመውን ተግባር ፈጽሞ ተጠይፎት ነበር፤ እናም ከአይሁድ መሪዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት በተመለከተ የመጨረሻ ትእግሥቱ
በማብቃቱ፣ ብዙዎችን ከዚያ እየገረፈ አወጣቸው። ጌታችን ኢየሱስ ይህን በማድረጉ ሌሎች ንቀውታል፤ ተዘባብተውበታል። ርሱ ግን
ለእግዚአብሔር የነበረውን ቅንአት በተግባር ገለጠ።
ኹሉም ክርስቲያኖች በጠባብዋና ጥቂቶች
ብቻ በሚጓዙበት መንገድ የሚመላለሱ ከኾነ፣ ክርስትናን በሕይወት በመኖር ከሌላው ተለይተዋልና የእምነታቸው ዓቃብያን ወይም
ጠባቂያን ናቸው የሚል አቋም አለኝ። ክርስትናን መኖር በራሱ፣ ለወደቀውና ከእግዚአብሔር ተለይቶ በስብራት ላለው ዓለም፣ ሕመምና
ግልጽ ዘለፋ ነውና። ከዚህ ባሻገር፣ በክርስቶስ እውነት ላይ የተመሠረተውን ክርስትና፣ ሾላኮች (ገላ. 2፥4፤ 2ጢሞ.
3፥6-7፤ ይሁ. 4)፤ ለመንጋው
የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች
(ማቴ. 7፥15፤ ሐ.ሥ. 20፥29) መከሩን እንዳያበላሹ በጌታ ጸጋ መጠበቅና መንከባከብ የዓቃብያነ እምነት ታላቅ ተጋድሎ ነው።
ዓቃብያነ እምነት ይህን ሥራ ሲሠሩ
ከሚሰጣቸው ስያሜዎች መካከል፣ “የፈጣሪ ሚሊሻዎች”፣ “የእግዚአብሔር ጠበቆች” … የሚሉ ይገኝባቸዋል። እንዲኹም በዐሳብ ደረጃ፣
“እግዚአብሔር ጠበቃ አይሻም”፣ “እናንተ ማን ናችሁና ነው ስለ ርሱ የምትሟገቱለት?” … ብለው የዓቃብያንን ሥራ የሚያንኳስሱና
የሚያጣጥሉ ጥቂቶች አይደሉም፤ በዚህ ኹሉ ውስጥ ግን አልፈው፤ እኒህን ጥዝጣዜዎች ኹሉ ችለው የሚያገልግሉ ወንድሞችና እህቶችን
ጌታ በብዙ ጸጋዎች እንደሚባርካቸው ፈጽሞ አልጠራጠርም!
ከኹሉ ይልቅ እኒህ ተቃውሞዎች ደግሞ፣
ከቅርብና “ወንጌል ተረድተዋል” ከሚባሉ ሰዎች መቅረቡን ላስተዋለ፣ ሕመሙ ከባድና ጠንካራ ነው። መዝሙረኛው ይህ ጥልቅ ስሜት
የጎዳው ይመስለኛል፣ “በወንድሞቼ መካከል እንግዳ፣ በእናቴም ልጆች መካከል ባይተዋር ኾንኩ። ለቤትህ ያለኝ ቅናት በውስጤ እንደ
እሳት ይነዳል፤ በአንተ ላይ የተሰነዘረው ስድብ በእኔ ላይ ዐረፈ” (መዝ. 69፥8-9) እንዲል።
ለእግዚአብሔር፣ ለስሙና ለመንግሥቱ
ለምንሠራው የትኛውም ሥራ፣ ለሚደርስብን ነቀፋና ትችት “ሙሉ ኃላፊነቱን ወሳጅ” ራሱ እግዚአብሔር ነው። በትክክል ርሱን
እያገለገልን እንወቀስ፣ እንነቀፍ፤ እንተች እንጂ “እግዚአብሔር የአንዲት ቀዝቃዛ ውኃ ዋጋ” የማይዘነጋ ታማኝ አምላክ ነው። አሜን።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ
ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።
ተባረክ በብዙ
ReplyDelete