ከኦርቶዶክሳውያን
ጥቂት ጳጳሳትና መምህራን መካከል፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጠንከር ያሉ የተሐድሶ ድምጾች በተለያየ መንገድ እየተሰሙ ነው። በባለፉት
ወራት ፓትርያርክ አባ ማትያስ እንደ ተናገሩት፣
“ምዕመናን ገንዘባቸውን የሚሰጡት ለሃይማኖት ማስፋፊያ እንጂ ለዘረፋ አይደለም።”
በማለት የሙስናና
የገንዘብ መውደድ ነገር ሥር የሰደደ መኾኑን ጠቁመዋል። በመቀጠልም ጳጳስ አብርሃም እንዲህ አሉ፣
“ቤተ ክርስቲያን የሙሰኞች ዋሻ ኾናለች የሚለው ዘርፈ ብዙ ፍርጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ
እየተባባሰ እንጂ ሲቀንስ አይታይም … ይህን አስነዋሪ ድርጊት እያወገዝን እውነትን ተላብሰን ከሙሰኞች የጸዳችና የከበረች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለተተኪው ትውልድ ልናስተላልፍ ይገባል።”
በማለት ጠንከር ያለ
ድምጽ አሰምተዋል።
ከሰሞኑ ደግሞ አቡነ
በርናባስ በመናፍቅነት በመታማታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጠው በመናገራቸው ሳይኾን በመብል ጉዳይ በተናገሩት ብዙዎች
ሲዘልፉአቸውና ሊያዋርዱአቸው ሲሞክሩ ተመልክተናል። አቡነ በርናባስ እንዲህ ብለው ነበር የተናገሩት፤
“በቀኖናም፤ በልማድም የምንጠቀመው አለ። … ከልማድ የተነሳ ብዙዎቹ ኢትዮያውያን አንበላም። ብዙዎቹ አልኩ እንጂ ሁላችንም አንበላም አላልኩም። ምክንያም ብዙ ኦርቶክሳውያን በኦሪት የተከለከሉትን የሚመገቡ አሉ። ኦርቶክሳውያን ኾነው በኦሪት ዘሌዋውያን 11 ላይ የተከለከለውን የሚመገቡ አሉ፤ ተፈቅዶላቸዋል። ቢኾንም ግን ከአገር ልማድ የተነሳ የማይበሉ አሉ። ግድ ብሉ አልያ ግድ አትብሉ አልያ ግድ አትብሉ አይባልም። … ማር የማይልስ፣ ወተት የማይጠጣ አለ … ይህ በልማድ ስለማይወዱት እንጂ ስለ ረከሰ አይደለም … ”
የአቡነ በርናባስን
ንግግር ኾን ብሎ ለማቀሳሰር የሚጠይቃቸው ሰው፣ ነገር ለመጠምዘዝ ሲሞክር ይስተዋላል። ጳጳሱን፣ “አህያ መብላት ይፈቀዳል እያሉ
ነው?” ብሎ በግልጥ የመጠየቅ ያህል። ነገር ግን “የእግረኛው ሚዲያ” ጠያቂ፣ ጥቂት ቢያነብብና መጻሕፍት አገላብጦ ቢኾን ኖሮ፣
ይህ ጥያቄ ለርሱ እንግዳ ባልኾነበት ነበር። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና እንዲህ የሚል ተጽፎ አለና፤
“… አሳማን ስለ መብላት
እንደ አይሁድ ኾነን የኦሪትን ሕጎች በመጠበቅ አንከለክለውም። የበላውን አንጠየፈውም፣ ርኩስ ኾኖ አናየውም፤ የማይበላውንም ብላ
ብለን አናስገድደውም። አባታችን ጳውሎስ ለሮም ሰዎች እንደ ጻፈው፣ “እግዚአብሔር ኹላቸውን ተቀብሎአቸዋልና የሚበላ የማይበላውን
አይናቀው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመብልና በመጠጥ አይደለም። ለንጹሖች ኹሉ ንጹሕ ነው፤ በመሰነካከል መብላት ግን ለሰው ክፉ
ነው” (ሮሜ. ፲፬ ቍ. ፫-፲፯፤ ቲቶ. ፩ ቍ. ፲፭፤ ፩ቆሮ. ፰ ቍ. ፱-፲፫)። ደግሞም ማቴዎስ ወንጌላዊ እንዲህ አለ “ከአፍ
ከሚወጣ ነገር በቀር ሰውን የሚችል የለም። በአፍ ውስጥ ያለው ወደ ሆድ ይገባል፥ በፀጥታ ይከተታል፥ ይወድቃልና ይፈስሳል”
(ማቴ. ፩፭ ቍ. ፲፩-፲፯) መብልንም ኹሉ አነጻው። (ማር. ፯ ቍ.፲፭) ይህን ቃል በመንገሩ አይሁድ ከመጽሐፈ ኦሪት
የተማሩትን የስህተታቸውን ሕንፃ አፈረሰው።
ይህ የእኔ ሃይማኖትና
በመንግሥቴ በረት ውስጥ ያሉ በትእዛዜ የሚያስተምሩ የተማሩ ካህናት ሃይማኖት ነው። ከወንጌል መንገድና ከጳውሎስም ትምህርት ወደ
ቀኝ ኾነ ወደ ግራ ፈቀቅ አይሉም። …”[1]
በማለት አጼ
ገላውዴዎስ በዘመኑ “ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኦሪታዊት ናት” ብለው፣ ቅሬታና ነቀፋ ላቀረቡባት ሰዎች በግልጽ መልስን
ሰጥተውበታል።
እናም በዚህ መሠረት፣
አባ በርናባስ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለየ አስተምህሮ አላስተማሩም። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱንና ቀኖናዋን እንኳ በትክክል
በማያውቁ ሰዎች ዘወትር ይሰደባሉ፤ ይተቻሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ይህን እውነት ስንናገር፣ “ኢየሱስን እንስበክልሽ የምትሏት
ቤተክርስቲያን ከ3000 ዓመት በሃይማኖት የጸናች ናት” ይላሉ፤ ምናልባት እኒህ ሰዎች፣ ግብዝነታቸውና አለማመናቸው ኢየሱስ
በናዝሬት ሰዎች እንደ ተደነቀው ይደንቁኛል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
እንደ ተናገረው፣ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል”
(ዮሐ. 8፥31-32) ብሎ እንደ ተናገረው፣ ሰው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ብቻ እንጂ ሌላ ምንም አርነት ሊያወጣው አይችልም።
ለወንጌል እውነት መታዘዝ መታደልና ብጽዕና ነው፤ አለመታዘዝ ግን ፍርድና ጥፋት ማስከተሉ አይቀርም። ለቃሉ መታዘዝ፣ በእውነትና
በፍቅር ለክርስቶስ በታደሰ ሕይወት መመላለስ ሊያስፈራና ሊያሸማቅቅ አይገባም።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ
ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።
[1] ጽድቀ ሃይማኖት፤ ገጽ 78-81 እና አቡነ ጎርጎርዮስ (ሊቀጳጳስ)፤ የኢትዮጲያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 3ኛ ዕትም፤ 1991 ዓ.ም፤ ገጽ 150
አሜን አሜን ጌታ ይባርክህ ያብዛልህ ይጨመርልህ
ReplyDeleteAmen! Amen! Egziabher yebarkeh
ReplyDelete