በእስጢፋኖሳውያን ላይ የደረሰው
መከራ
“እብለክሙ ኦ ሕዝበ ክርስቲያን ምዕመናኒሃ ለማርያም ድንግል በክልኤ” ኵሉ
ብዕሲ ዘተወክፈ ኪያሆሙ፥ ወዘተሳተፈ ምስሌሆሙ ወዘአንበሮሙ ውስተ ቤቱ ወኀበ ቤተክርስቲያን በውስተ ምድረ ርስቱ እሙኒ ሥዩም ይሠዐር
ወይትበርበር ቤተ ንዋዩ፥ ወምድረ ርስቱ ይኩን ለባዕድ።
ሊቃነ ካህናትኒ ወንቡራነ እድ ወኵሎሙ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ወመነኮሳትሂ
ወኵሎሙ ሕዝብ ለእመ ተረክቡ እንዘ እኀብኡ ኪያሆሙ፥ ፈድፋደ ኩነኔ ላዕሌሆሙ። ሢመቶሙ ወምድረ ርስቶሙ ይኩን ለካልዕ እስመ ኮኑ
ሱቱፋነ ምስሌሆሙ።
ወእሙንቱሰ ደቂቀ እስጢፋ በአማን አይሁድ እሙንቱ እለ አብዩ ሰጊደ ለማርያም
ድንግል በክልኤ ወለ መስቀለ ዋሕድ ወልድ ለእሙንቱሰ ኵነኔሆሙ ሞት።
ወዘረከቦሙሂ ይኵንኖሙ በፅኑዕ ኩነኔ ወቀቲልሰ ኢይቅትሎሙ፤ አላ ይብጽሖሙ ውስተ ኩርጓኔነ ከመ
ንሰማዕ ቃሎሙ። ወከመ ይኩን ፍትሕ ላዕሌሆሙ ወዘተረክበ። ብዕሴ እንዘ ይብሎ ሰላም ለእስጢፋዊ መክፈልቲ ምስለ እለ ተወክፋዎሙ ለደቀቂ
እስጢፋ።”
የዚህ አማርኛ ትርጉም፦
“በኹለቱም ጊዜያት ድንግል የምትሆን የማርያም ምዕመናን
የኾናችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ እንዲህ እላችኋለሁ። “ማናቸውም ሰው ሁሉ ደቂቀ እስጢፋን የተቀበለ ከእነርሱ ጋር የተባበረ በቤቱ
ውስጥም ያኖራቸው ወይም በቤተ ክርስቲያኑና በርስቱም ምድር ያኖራቸው ቢገኝ፥ ሹመት ያለው ከኾነ ከሹመቱ ይሻር፥ ቤቱም ይዘረፍ ገንዘቡ
ኹሉና ያለውም የምድሩ ርስት ለባዕድ ይሁን።
ሊቃነ ካህናት፥ ንቡረ ዕድ የቤተ ክርስቲያን ሹማምንትና
መነኮሳትም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ እነርሱን ሲደብቋቸው ከተገኙ በእነርሱ ላይ ከፍ ያለ ቅጣት ይፈጸምባቸዋል። ሹመታቸውና የምድር ርስታቸው
ለሌላ ይኹን። ከእነርሱ ጋር ተባብረዋልና ነው።
እነዚህ ደቂቀ እስጢፋ ግን ለድንግል ማርያምና ለአንድ
ልጅዋ መስቀል መስገድን እምቢ ያሉ ናቸው፥ በእውነት አይሁድ ናቸው። የእነርሱ ቅጣት ሞት መሆን አለበት። ያገኛቸው ሁሉ በጽኑ መከራ
ይቅጣቸው። ቃላቸውን ሰምተን በአደባባያችን ሸንጐ እንድንፈርድባቸው ወደ አደባባያችን ያምጣቸው እንጂ መግደልን ግን እርሱ ራሱ አይግደላቸው።
እንደዚሁም ከደቂቀ እስጢፋ የሆነውን ሰው አግኝቶ ሰላምታ የሰጠው ሰው ሁሉ ዕድል ፈንታው ደቂቀ እስጢፋን ከተቀበሉ እንደሚደረግባቸው
ይኾናል።”
የእስጢፋኖሳውያንን መከራ መናገር በራሱ ያምማል፤ አሰቃቂነቱም ኹለንተናው
በዲያብሎስ በተወረሰ ሰው የሚፈጸም እንጂ ሰብአዊ የኾነ ሰው እንኳ እንዲህ ሊያደርግ ፈጽሞ አይችልም። ሰው ለሰው ለመራራት ሰውነትን
ማየቱ ብቻውን ይበቃዋል፤ ሰው በእንሰሳ ላይ እንኳ የማይፈጸም አሰቃቂ ተግባርን ከፈጸመ ግን ከሰውነት አንሷል ብሎ ደፍሮ መናገር
ይቻላል። ታላቁ መጽሐፍ፣ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው” (ምሳ. 12፥10) እንዲል፣
እውነተኛ መንፈሳዊ ልብ ያለው ሰው እንኳ በእግዚአብሔር መልክ ለተፈጠረው ሰው ለእንሰሳ እንኳ ይራራል። እናም ለእንሰሳ መራራት
የሚቻለው ሰው፣ ለሰው መራራት ከተሳነው መንፈሳዊነቱ ደባይቷል ማለት ነው።