ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ነው። ለመናገር ምክንያት የኾነው ደግሞ፣ የአይሁድ ራሳቸውን ንጹሕ አድርገው፣ ሌላውን ግን ፍጹም በደለኛ፤ ኃጢአተኛ አድርገው
ማቅረባቸውን በታላቅ የተግሳጽ ቃል በመንቀፍ ነው። አይሁድ ራሳቸውን ንጹህና የተሻሉ አድርገው ለማቅረብ በሌላው ሰው ላይ የደረሰውን
ነገር እንደ ታላቅ ማስረጃ አድርገው አቀረቡ። እናም፣ “ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት”
(ቁ.1)። ጲላጦስ ይህን ነገር ለምን እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን አይነግረንም። ነገር ግን ጲላጦስ ይህን ነገር ሥልጣኑን
ለማሰንበት ወይም የሮማን ሕግ ስለመሻራቸው ሲል አድርጐት ሊኾን ይችላል፤ በጭካኔው ወደር የለሽ ነበርና።
ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ሰዎቹ ያወሩለትን ነገር፣ “እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን?”
(ቁ.2) በማለት፣ እጅግ ሞጋች ጥያቄን በማቅረብ መለሰላቸው። ደግሞም በተጨማሪ፣ “ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው
እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን?” (ቁ.4) በማለት ያልተብራሩና እጅግ
ግልጽ ያልኾኑ ድርጊቶችን ብቻ ተከትለው ፍርድን ለሚሰጡ ወገኖች ምክንዩ ጥያቄን አቀረበላቸው።
ሰዎቹ ድርጊቱን ለጌታችን ኢየሱስ ያወሩበት ኹኔታ፣ እጅግ ጤናማ እንዳልኾነ
መጽሐፍ ቅዱስ የልባቸውን ሃሳብ በማጋለጥ ይናገራል። ሰዎች አንዳች አስከፊ ነገር ሲገጥማቸው፣ የገጠማቸውን ነገር የተመለከቱት ሰዎች
በአብዛኛው ከኃጢአታቸው ጋር ያያይዙታል። እርግጥ ነው፤ ጲላጦስም መሥዋዕት እያቀረቡ ሳለ የገደላቸውም ኾኑ፣ በሰሊሆም ግንብ ተደርምሶ
የወደቀባቸውና የሞቱት ሰዎች አሟሟታቸው አሰቃቂና አስደንጋጭ ነው። እንዲህ ዓይነት አሟሟቶችን ደግሞ ብዙዎች ከመቅሰፍትና ከኃጢአት
ውጤት ጋር በማያያዝ ሲናገሩ እናደምጣለን። አዎን! አንዳንዶች በኃጢአታቸው በግልጥ የሚቀጡ ይኖራሉ፤ ይህ ግን እጅግ በጣም ጥቂት
ጊዜ ብቻ ነው። ይልቁን ከፍርድ ይልቅ ኃጢአት ብዙ ጊዜ ፍርድን እያመለከተ ይገለጣል፤ “የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው
ፍርድንም ያመለክታል፥” (1ጢሞ. 5፥24) እንዲል። በተለይ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር በብዙ ምሕረት እንጂ በብዙ ቊጣ አልተገለጠም፤
ይህ ማለት ግን ኃጢአት ፍርድን አያመለክትም፤ አማኝም ስለኃጢአት ይናገር ዘንድ አይገባውም የሚል ሃሳብን አይይዝም።
አይሁድ ኾኑ
ሌሎች ወገኖች ግን ፦ በሰዎቹ ላይ ከደረሰው ነገር ተነሥተው፣ “እንዲህ ያለ ነገር የሚደርሰው እጅግ ኃጢአተኛ በኾኑ ሰዎች ላይ
ብቻ ነው” በማለት ብዙ ጊዜ መደምደሚያ ሲሠሩ እንመለከታለን። ለምሳሌ፦ በኢዮብ ላይ ስለደረሰው መከራ ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ “እባክህ
አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው? እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥ መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ
ያጭዳሉ።” (ኢዮብ 4፥7-8) በማለት ነበር የተናገረው። በኤልፋዝ ሃሳብ [ክስ] የኢዮብ የመከራ ምንጭ ኃጢአቱን አለማሰቡ እንደ
ኾነ ይነግረናል። ነገር ግን ሃሳቡ ፈጽሞ ትክክል አልነበረም፤ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኖቹ ስለማያዩ ስለአንድ ሰው፣ “ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት
የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ?” በማለት ሲጠይቁ (ዮሐ. 9፥2)፣ ያ ሰው ዓይኖቹ እንደዚያ ሊኾኑ የቻሉት በአንዳች ኃጢአት
ምክንያት እንደ ነበር ከሚያምን ከራሳቸው ልብ አመንጭተው ነበር።
ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ግን ለኹለቱም ድርጊቶች የሰጠው መጠቅለያ ሃሳብ የሰው ዘርን ኹሉ የሚመለከት ነው። “እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን
ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።” (ሉቃ. 13፥3፤ 5)፤ አዎን! በሰዎቹ ላይ የኾነው ነገር ኹሉ የኾነው በኃጢአታቸው
ምክንያት አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድርጊቱ ይልቅ የሰዎችን ኹሉ ኃጢአተኝነት አጉልቶ ተናገረ፤ ለሰዎች ኹሉ ንስሐ ያስፈልጋቸዋል
ምክንያቱም ሰዎች ኹሉ ኃጢአተኞች ናቸውና። በሌሎች ላይ በድንገት የኾነው ነገር ኹሉ እኛ ከኃጢአታችን ተጸጽተን እስካልተመለስን
ድረስ እኛንም የማናመልጠውና ከቶ ልንሸሸው የማንችለው ፍርድ ያመጣብናል። ምክንያቱም እኛ አኹን የተረፍነው የተሻልን ስለኾንን አይደለም፤
ይልቁን ስለገዛ ኃጢአታችን ንስሐ እንድንገባ እንጂ።
በሰዎች ላይ
የምናየው ነገር እጅግ የሚያንገበግበንና የሚያስፈራን ከኾነ፣ እኛ እንደዚያ ካለ ነውርና ዕድፈት መራቅ ይገባናል። “እነእገሌ እንዲህ
ያለ መከራና ቅጣት፣ ውርደትና ሞት ያገኛቸው በሥራቸው ነው፤ እሰይ!” ከማለታችን በፊት እኛ እነርሱ ሠርተውታል ከሚባለው ነውርና
ዕድፍ ንጹሐንና የምንነቀፍበት ነገር የማይገኝብን ሊኾን ይገባል። ንስሐን ስናውጅና ስንናገር የሰውን ልጆች ኹሉ ኃጢአተኝነት መናገራችን
ነው። ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነትና አዳኝነት ካላመነ በቀር ሊድንና ምሕረትን ሊያገኝ አይችልም፤ ከዳነም በኋላ ደግሞ መዳኑን
ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ አጽንቶ መያዝና በማናቸውም መንገድ የሞተለትን ጌታ ከማሳዘንና ከማስመረር ሊርቅ ይገባዋል። ደግሜ እላለሁ፤
ይህ ማለት ግን የተገለጠውንና ለብዙዎች መሰናክል የሚኾነውን የኃጢአትን ስልና ፍል ጠባይ በዝምታ መመልከት አለብን የሚል አንድምታ
የለውም።
በዚህ ቅዱስ
ቃል መሠረት አኹን ያለንበትን ወቅት ስንመዝነው ብዙዎቻችን ከመንፈሳዊነት ፈቀቅ ማለታችንን ያሳያል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር
ዓቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት [ሲመጡ የነበረውን የዘረኝነት ዓይን ያወጣ ጽዩፍ ድርጊት በዓይኖቼ ካዩትና ከሰሙት አንዱ ነኝና
ጌታ በዚህች ምድር ላይ ልዩነት እንዲያደርግ ሲያለቅሱና] በአገሪቱ ከታየው “አንጻራዊ ሰላም” አኳያም ለያህዌ ጸባኦት ምስጋና ካቀረቡት
አንዱ ነኝ። አኹንም ይህን “ወጣትና ልበ ሰፊ መሪ” ጌታ ከክፎዎች ሰዎች እንዲጠብቀው ምልጃዬ በፈጣሪዬ ፊት የጸና ነው፤ ቅዱስ
ቃሉ በፍቅር ጠቅጥቆ ያዘኛልና። ዳሩ ግን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ባገኙት አጋጣሚዎች ኹሉ ደጋግመው አንዳንዶችን “የቀን ጅቦች፣ በጫካ
ውስጥ ያሉ ጠማማ ዛፎች፣ በሕዝብ ውስጥ ያሉ ሌቦች…” የሚለው አባባላቸው በአብዛኛው ሰው ዘንድ የተወሰደው ወደ አንድ ብሔር ባንጋደደና
እጅግ ሥር በሰደደ ጥላቻን ባመረቀዘ መንገድ ነው። [መቼም ይህንን ሰው እንጂ ታድያ መሪያችን ምን አጠፉ ብሎ የሚሞግተኝ እንደ
ሚኖር ተስፋ አደርጋለኹ! የዕድገትን ኹለንተናዊነት ካሰብን [ያውም ስመ እግዚአብሔርን እየጠራን!] መንገዱ በትክክል መጽዳት አለበት።]
ይህ ደግሞ ከፖለቲከኞች
እስከ ባለ ሥልጣናት፣ እንዲሁም መንፈሳዊነት ከእኛ በቀር “ላሳር” በሚሉ “አማኞችና አገልጋዮች” ጭምር ሲንጸባረቅ አስተውለናል።
ብዙዎችም ይህን መንገድ ተከትለው ሌብነታቸውና ዘረኝነታቸውን በሌሎች ሰዎች ላይ [ አንዳንዶች ብሔር ጭምር ጠቅሰው ] አላክከው፣
በሚያሳፍር መልኩ ለራሳቸው ንጹሐን እንደ ኾኑ ሊነግሩን ሲቋምጡ ተመልክተናል። ራሳቸውን ከበረዶ ይልቅ አጥርተው፣ ከሐር ይልቅም
አለስልሰው ከዘረኝነት፣ ከሙስና ሌብነት፣ ከስግብግብነት … ንጹሕ መኾናቸውን ለማመረጅ [ማስረጃ ለማድረግ] ማጣፈጫቸውን የሌሎችን
ክፋት በማስፋትና በማጥለቅ ሲተነትኑ አስተውለናል።
ክፉነት የአንድ ወገን አይደለም፤ በክርስቶስ ያልኾነው ወይም ከክርስቶ ፊቱን
ዘወር ካደረገው አሮጌው ሰው ማንነት የሚመነጭ ነው፤ ከእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ፊቱን ዘወር ያደረገ ኹሉ በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር
ነውና፣ ለኃጢአት ከመገዛት አያመልጥም። ማንም እገሌን እንዲህ ያለ ነውር አለብህ ከማለቱ በፊት፣ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ከተባለው
ነውር ጽዱ መኾን አለበት። ዛሬ ግን “እገሌ የተባለ ሰው ወይም ብሔር ዘረኛ ነው፣ ሌባ ነው” የሚለው ኹሉ፣ ራሱ በዘረኛና በከፋፋይ
ክፉ መንገድ ላይ ቆሟልና፣ የሚናገረው ተቃርኖውን እንጂ ትክክሉን አይደለም።
ትላንት መሪዎቻችን
የከፉብን በእኛ ኃጢአት ምክንያትና በመሪዎቻችን እጅግ ራስ ወዳድነት ምክንያት መኾኑን ለመቀበል ፈጽሞ ዝግጁዎች የኾንን አይመስልም።
ለኢትዮጵያ “አለማደግና አለመሰልጠን” የኾነ ብሔርና የኾኑ ሰዎች የከፋ ክፋት እንጂ፣ “የእኔም ስንፍና፣ ሥራ አለመውደድ፣ ዘረኛ፣
ብሔርተኛ መኾንም … ጭምር አለበት የሚል፣ በዚህች ምድር ላይ ፈልጐ ማግኘት ጭንቅ ነው። ክፉነትና የኃጢአት ስልነት ከላይ እስከ
ታች ተጠናውቶናል፤ እገሌን ዘረኛ ስንል፣ እኛ ራሳችን ዘረኞች መኾናችንን ዘንግተናል፤ ሰውን መግደል ብንጠላም ለመግደል የምናደባ
“ወፈፌዎች” ብዙ ነን።
ለመግደላችን፣
ዘረኛ ለመኾናችን፣ ደም ለማፍሰሳችን፣ ጉበኛና ሌቦች ለመኾናችን … የሌሎችን ስህተት የምናነሣ ከኾንን የአሮጌው ሰው ጠባይ በትክክል
ተጣብቶናል እንጂ፣ በትክክል ከኃጢአት ኹሉ በሚያነጻውና በሚዋጀው (1ዮሐ. 1፥7) በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም አልተዋጀንም።
ትላንትም ኾነ ዛሬ [ክፉና ደግ ከምንላቸው መሪዎች] ጐን የምንቆመውና የምንማልድላቸው፣ የምንጸልይላቸው፣ አስተዋይ የጥበብ መንገድ
እንዲከተሉና የሚመሩትን ሕዝብ በፍትሕ እንዲያሳርፉ፣ ክፋታቸውን ተጠይፈን ያህዌ ኤሎሂምን ደጅ የምንጠናው የኾኑ አካላትን ወይም
ብሔሮችን ወይም ግለሰቦችን አምርሮ በመጠየፍ መንፈስ ውስጥ ኾነን አይደለም። ይልቁን እየወደድንና እየማለድንላቸው እንጂ። አልያ
መንፈሳዊነታችን “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤” (ማቴ. 6፥12) ማለት የማይችል ልምሾ ይኾናል፤
ደግሞም ሕግ ተላለፉ ያልናቸውን በሕግ ጥላ ሥር እንዲያርፉ ከማድረግ፣ እኛው በገዛ እጃችን በአደባባይ የምንደበድብ፣ እንደ እባብ
የምንቀጠቅጥ፣ የምንገድል፣ የምናዋርድ፣ የምንሳደብ … ከኾንን ከምንጠላቸው ሰዎች የባስን ክፉዎች እንጂ፣ ከእነርሱ ስህተት የተማርን
ወይም የእነርሱን ክፋት ከልባችን የተጠየፍን አይደለንም።
እንግዲያስ፣
ኹላችን ንስሐ ባንገባ ድንገት የማናመልጠው ፍርድ እንደ ሚያገኘን ማሰብ አለብን። መሪዎቻችንን እንውደድ፤ እንታዘዛቸውም፤ ስንወድና
ስንታዘዛቸው ግን ሌላውን በሚጠላና በሚያናንቅ መሠረት ላይ ቆመን መኾን የለበትም። በትክክል ስንመለስም ከሌሎች እንደ ተሻልን በማሰብም
አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድን ያለው እንደዚያ ነውና፤ የሌሎች ክፋት አብዝቶ የተገለጠውና የታየው እኛው ንስሐ እንድንገባ
መንፈስ ቅዱስ ሊወቅሰን አስቦ ቢኾንስ? ምናልባት እኛም ልክ እነርሱ በተያዙበት ኃጢአት ተይዘን ቢኾንስ? እኛ ራሳችንን ማየት እንደ
ተሳነንና መንፈሳዊ ፊታችን እንደ ተጨማደደ ለማሳየት ቢኾንስ? እንኪያስ፦ “ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።”
ጌታችን ኢየሱስን
መስቀሉንና ሞቱን፣ የትንሣኤውን ኃይል ብቻ ትኵር ብለን ባለመመልከት የተሰቀለውን ጌታ ከበደልንበትና ካሳዘንንበት ወራት እንመለስ፤
ደግሞም፣ በወደቁት ከመሳለቅና በጥላቻ ኅሊናችንንና ዓይናችንን ከማሳወርና ከማቅላት፣ ከቻልን መንገዱን በትክክል እናሳያቸው፤ እኛም
እነርሱ በተያዙበት ነውር እንዳንያዝ እንጠንቀቅ፤ ጌታችን መንፈስ ቅዱስ ወደ ልባችን ይመልሰን፤ በትክክል ራሳችንን ማየት እንድንችል
ይርዳን፤ አሜን።
አሜን አሜን አሜን
ReplyDeleteጌታ ይባርክህ ወዳጄ በርታ
ReplyDeleteamen yenisiha lb ysten
ReplyDelete