“ማራናታ” የሚለውን ቃል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማኹት፣ በ20/7/1995 ዓ.ም በከሰዓት መርሐ ግብር፣ በሻሸመኔ
ከተማ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተደረገ ጉባኤ ላይ [ያኔ ይህን ጉባኤ ለመታደም ከአርሲ ነጌሌ፣ ሻሸመኔ ድረስ በእግራችን
ነበር የምንሄደው] ከመምህር ይልማ ቸርነት አንደበት ነው። በዕለቱ መምህሩ፣ በዘፍጥ. 3፥10 ላይ ያለውን ኃይለ ቃል አንስቶ አስተምሮ፣
ትምህርቱን ሲያሳርግ፣ “ማራናታ” የሚለውን ቃል ሲናገር፣ ትርጉሙ ባይገባኝም፣ ቃሉ በልቤ መካከል ተሰንቅሮ ከብዙ ጥያቄዎች ጋር
በውስጤ ቀረ። በጊዜው መምህሩን አጊኝቼ ትርጕሙን ለመጠየቅ ዕድል ባላገኝም፣ በተደጋጋሚ ብዙ ሰዎችን ጠይቄ የመለሰልኝ ሰው ግን
አልነበረም።
ትርጕሙን የሰማኹ ዕለት እጅግ በጣም ፈንድቄአለሁ፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና መናፈቅ የሚያውጅ
ቃል ነውና። ቃል በቃል በመጽሐፍ ቅዱስ፣ “ጌታችን ሆይ፥ ና።” (1ቆሮ. 16፥22) ተብሎ ከአራማይክ ቋንቋ ተተርጕሞአል። ዐሳቡም የተወሰደው ከጥንት ክርስቲያኖች
የናፍቆት ብርቱ ጩኸት ነው። የጥንት ክርስቲያኖች ጌታችን ኢየሱስ ቶሎ እንዲመጣ የማያባራ የናፍቆት ጥሪ ነበራቸው። ይህንም የሚያደርጉት
በመልእክቶቻቸው ብቻ ሳይኾን፣ በጸሎታቸው መጨረሻም፣ ጌታ ፈጥኖ እንዲመጣ አብዝተው ያውጁ ነበር።
የጌታችን ኢየሱስ መምጣት፣ ሙሽራዋን በጽናትና በቅድስና ታምና ለምትጠብቀው ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ የምሥራችና
ናፍቆት ነው። ምክንያቱም እርሱ ሲመጣ፣ “በሰማያት ባለው በአባቱ ፊት ይመሰክርላታልና፤” (ማቴ. 10፥32) ዘወትር መምጣቱን ተግታ በመናፈቅ ትጠብቃለች። የምትጠብቀው እንዲያው ዝም
ብላ አይደለም፤ መጽሐፍ እንደሚል፣ “… የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ኹሉ ይቃጠላል። እንግዲህ
ኹሉም ነገር በዚህ ኹኔታ የሚጠፋ ከኾነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልኾኑ ይገባችኋል? አዎን፤ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት
ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ [የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት ልትጠብቁ]
ይገባል።” (2ጴጥ. 3፥10-12)።
እውነተኛ መንፈሳዊነት ወይም ቅድስና፣ ከኀጢአት ተለይቶ ለእግዚአብሔር መኖርና እግዚአብሔርን በማምለክና በማክበር
አብዝቶ መትጋት ነው። ቤተ ክርስቲያን ይህን ዘወትር የምታደርግ ከኾነ፣ የመሲሑን መምጣት እጅግ ታስቸኩላለች። ምክንያቱም የምድሩንና
ማናቸውንም ነገር ተስፋ ማድረግ አትችልም፤ በምድርና በሰማይ ያሉት ኹላቸውም፣ በእሳት ይወድማሉ፤ ተቃጥለው ይጠፋሉ። ስለዚህ የቤተ
ክርስቲያን ተስፋና አለኝታዋ ከሰማይ የኾነውና ዘላለማዊው መሲሕ ብቻ ነው፤ ለዚህ ነው ሳትታክት ማራን አታ ማለት የሚገባት!
ማራን አታ የምንለው ተናፋቂው መሲሕ፣ በሩን ለኹሉም የከፈተና እንዲገቡም ግብዣ ያቀረበላቸው ናቸው። “እንዴት
ኾነ?” ብለን ለመጠየቅ እስከማንደፍርበት ድረስ፣ አምስት ባል የነበራት ሳምራዊት ሴት፣ በመላው ሕዝብ የታወቀውና ከጌታ ጋር የተሰቀለው
ወንበዴ፣ ሰው ኹሉ ይጠየፋትና አሥራ ኹለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት፣ ብዙ አጋንንት (ሌጌዎን) ገብተውበት የነበረው ሰው፣
በጌርጌሴኖን ዕብድና በመቃብር ስፍራ ይኖር የነበረው ሰው፣ ሰባት አጋንንት የወጡላትና ሌሎችም ወደ መንግሥቱ የተጋበዙ ውድና ክቡር
እንግዶች ነበሩ። የመጣችውና በመካከላችን ያለችው መንግሥቱ፣ በምልአት ትገለጥ ዘንድ፣ መንግሥትህ ትምጣ ወይም ኢየሱስ ሆይ ቶሎ
ና በማለት አማኞች ይቃትታሉ። ቅዱስ ቃሉ፦ “… የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን
ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።” (ሮሜ 8፥23)
እንዲል።
በዚህም ምድር ክርስቶስን የምናምን ኹላችን ማራን አታ እንላለን፤ የመዋጀታችንን ሙሉነት ፈጽመን እንራባለን፤
እንጠማለን። ልጅነታችን አኹን በመከራና በሕማም፣ በጉድለትና በሐዘን እንደ ተከበበው ያይደለ፣ መንፈሳዊ አካል በመልበስና በምልአት፣
በፍጹም ደስታና በበዛ ሐሴት እንዲፈጸም መሲሑን ማራን አታ እንላለን፤ አዎን፤ ማራን አታ፤ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!
No comments:
Post a Comment