Thursday, 10 March 2022

ጾም ለአዲሱ ሰው

 Please read in PDF

በድጋሚ፣ በቅድስና እየጾማችሁ ላላችሁ፣ እንኳን ለዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ!!! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ እየተመላለሰ በሚያስተምርበት ወቅት፣ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ቀርበው፦ “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት” (ማቴ. 9፥14)፡፡ እነዚህ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት፣ መጾማቸው መልካም ነበር። በጾማቸው ውስጥ ግን የሚያዩት እግዚአብሔርን ሳይኾን፣ የሌሎችን አለመጾም ነበር። ስለዚህ ጾማቸው፣ “በክስ የተሞላ ሥነ ሥርዓትን” ብቻ ያሟላ እንጂ የልብ መሠበር፣ የንስሐ መንፈስ፣ ፍቅር የነበረው አልነበረም። ጾማቸውን ለሃይማኖታዊ ውድድር ወይም ውርርድ አውለውታል። ስለዚህ መልስና እርካታ ያለው አልነበረም። ጾም ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መንፈሳዊ መስመር፤ ቅዱስም ተግባር ነው።



ቅዱስ ተግባር የኾነው፣ ጾም ዋጋውን ከሚያጣባቸው ነገሮች በጥቂቱ ብንጠቅስ፦ 

1. ጾማችን ትዕቢትን ሲወልድ፣

2. ጾማችን የሌሎችን አለመጾም ሲያይ፣

3. ፈተናው የራቀልን ጸጋ የበዛልን በቸርነቱ መኾኑ ቀርቶ በጾማችን ሲመስለን፣

4. በግድ፤ ያለ ፈቃዳችን ስንጾም ዋጋ እናጣለን።

   የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ብዙ ቢጾሙም፣ መጾማቸው ግን የሐዋርያትን አለመጾም ያሳያቸው ነበር። ራሳቸውንም የጾም ፖሊስ አድርገው፣ አቁመው ነበር። በሌላ ሥፍራ ላይም፣ አንድ ፈሪሳዊ እርሱ በሳምንት ኹለት ቀን እንደሚጾም፣ ቀራጩ ግን ያልተገራ ሕይወት እንደሚኖር ለእግዚአብሔር ተናግሮል። በዚህ መመጻደቁ ግን ተዋርዶ ተመልሶአል። ጽድቅ አለኝ ያለው ፈሪሳዊ ባዶ እጁን፣ ምንም ጽድቅ የለኝም ያለው ቀራጭ ግን በጽድቅ ተመልሰዋል (ሉቃ. 18፥9-14)፡፡ የሚጾም ሰው፣ የማይጾሙ ሰዎችን በጸሎት የሚያስባቸው እንጂ የሚከሳቸው አይደለም። ጾም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ጉዳይ የምንፈጽምበት እንጂ እየተያየን፣ በመፈራራት የምንጾመው መኾን የለበትም። በጾም ውስጥ ራሳችንን ማየት ይገባናል እንጂ፣ ከኋላችን የቆሙ የሚመስሉንን ሰዎች ማየት አይገባንም። ከምግብ ብቻ ሳይኾን፣ ከኃጢአትም ካልተከለከልን ጾም እውነተኛ አይደለም።

   በነቢዩ ኢሳይያስ፦

“ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?

 እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህን ስለ ተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?

 የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ” (ኢሳ. 58፥3-11)።

በእግዚአብሔር ፊት ተወዳጅ ጾምና ጸሎት ለማቅረብ፣ አስቀድሞ ርእስ መያዝ፣ ንስሐ መግባትና ይቅር መባባል ይገባል። ከጾሙ ቀጥሎ ደግሞ ረሀብተኞችን ማጥገብ፣ የታረዙትን ማልበስ ይገባል። እነዚህ ነገሮች በሌሉበት የሚደረግ ጾም ዋጋው ያነሰ ነው። ጌታችን፣ የራሳቸውን መጾም ተናግረው የሌሎችን አለመጾም ክስ አድርገው ላቀረቡት የጾም ፖሊሶች “ሚዜዎች ሙሽራው ከነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉ ነገር ግን ሙሽራው ከነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ” አላቸው (ማቴ. 9፥5)፡፡

በእሥራኤል ባሕል፣ ሙሽራና ሚዜዎች እንዲጦሙ አይፈቅድም። ጾም በሀዘን በለቅሶ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት በመሆኑ ሙሽሮች እንዲጦሙ አይፈቀድም ነበር። በእኛም ሀገር መንገደኛ፣ የታመመ፣ አራስ ሴት፣ ወታደር፣ መጾም እንደሌለባቸው ይታወቃል። ጌታችን፣ በእስራኤል ባህል መልሱን ሰጣቸው። እርሱ ሙሽራ እንደ ኾነ እንደሚሄድም አብሮ ተናገረ።

ጌታችን ሙሽራ ነው። ሙሽራ ለአንድ ቀን ሙሽራ ይኾንና፣ ከዚያ ቀጥሎ የኑሮ ታጋይ ይኾናል። ጌታችን ግን ኹለት ሺህ ዓመት ሙሽራ ነው። ሙሽራ የማይጠገብ፣ የደስታ ምንጭ፣ የኹሉ ዓይን የሚያየው፣ በምስጋና የሚከብር፣ ነው። ጌታችንም ሙሽራ ነውና አይጠገብም። ኹሉም ነገር ገና በአፍ ውስጥ ይሰለቻል፣ እንደ ጨበጡት ያረጃል፣ የዚህ ዓለም ነገር በምኞት ትልቅ፣ ሲይዙት ትንሽ ነው። ሙሽራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የደስታ መፍለቂያ፣ የተድላ አገሯ የሕይወት ወደቧ ነው።

ጌታችን፣ የኹሉ ዓይን የሚያየው የልብ ሁሉ ናፍቆት፣ የአገልግሎትም ማዕከል ነው። ነቢያት ስለ እርሱ ትንቢት ተናገሩ ስለዚህ ነቢያት ተባሉ፣ ሐዋርያት ስለ እርሱ ሰበኩ፤ ስለዚህ ሐዋርያት ተባሉ። እግዚአብሔር አብ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” አለ፤ (ማቴ. 17፥5)። ቅድስት እናቱ ድንግል ማርያምም፣ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት፣ ወደ ልጇ አመለከተች (ዮሐ. 2፥5)፡፡ ቀስት ኹሉ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያመለክታል። እርሱ ሙሽራ ነውና፣ በምስጋና እና በምሥክርነትም ይከብራል። ሙሽራ በሌለበት ሚዜዎች የሉም። ሚዜዎች ለሙሽራው ክብር ይቆማሉ። ክብራቸው እርሱ ነውና። ኢየሱስ ክርስቶስም የመላእክት ማዕረጋቸው፣ የቅዱሳን ጌታቸው ለኃጢአተኞች ቤዛቸው ነው። እርሱ ስለ እራሱ ይከብራል፣ እነርሱ ግን በእርሱ ይከብራሉ። ዛሬ ግን፣ ወገናችን ሙሽራውን አባሮ ሚዜዎችን የያዘ ይመስላል። የሙሽራው ስም ሲጠራ ይከፋልና። “ኢየሱስ” የሚለውን ስም ሳይቀር፣ ለሌሎች ሰጥቶ ባዶ እጁን የኾነ ትውልድ እንዳናተርፍ መምህራን ተግተን ልናስተምር ይገባናል። ያለ ክርስቶስ ክርስትና ሊኖር አይችልምና። ሰባክያን ሳይቀር ይህን ስም ደጋግማችሁ ጠራችሁ እየተባሉ፣ ክፉ ስም ሲሰጣቸው እናያለን። በሚያሸልመው ነገር መካሰስ ከጀመሩ ቆይተዋል። ትልቁ ትክክለኛነት የኾነው፣ የጌታችን ስም የክስ አንቀጽ ተደርጎ መወሰዱ፣ ትልቅ ኃጢአት ደግሞም ክህደት ነው። ከእኛ ክርስትና በቀርም፣ በስሙ የሚያፍር የየትም አገር ክርስትና እምነት የለም።

ጌታችን፣ ለዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ አላቸው፣ “በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጥጅ የሚያኖር የለም። ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁም ይፈሳል፣ አቁማዳውም ይጠፋል፣ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ” (ማቴ. 9፥16-17)፡፡ የደቀ መዛሙርቱ ሕይወት አሮጌና በመንፈስ ቅዱስ መታደስን ያላገኘ ነበር። በዚህ አሮጌ ማንነት ላይ ጾም ቢታዘዝ ይከብደዋል። ደግሞም ያብሰዋል። ብዙዎች ሕይወታቸው ሳይለወጥ፣ ጾም ሲመጣ ጾመኛ ይሆናሉ። ጾም ሲፈታ በበለጠ፣ ኃጢአት ውስጥ ይወድቃሉ። መጠጥና ዝሙትን በጾም ወራት ያቆማሉ እንጂ አይተዉትም። ኃጢአትን አዳፍነው እንጂ አጥፍተው አልመጡም። ጾም ለነርሱ ለኃጢአት የዓመት ፈቃድ መውሰጃ ነው። ያለ ማቋረጥ ከጠጡ ጉበታቸው ይፈርሳልና፣ ብዙ ዘመን ለመጠጣት ጾምን ይጠቀማሉ። “የቀበሮ ባሕታዊ” ማለት እንዲህ ነው። ኃጢአት ግን ቅበላና ፋሲካ የሌለው፣ ኹልጊዜ ልንርቀው የሚገባ ነው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር የሚኖሩ እንደሚያውቁት ከጾም በኋላ አመጻቸውና ባሕርያቸው እየከፋ፣ አብረዋቸው የሚኖሩትን ያስመርራሉ። ላልተለወጠ ሰው፣ የሚያስፈልገው የክርስትና ሙሉ ትምህርት ንስሐና እምነት ነው። ለብዙዎች ግን ጾም፣ ራሳቸውን የሚያታልሉበት፣ መንፈሳዊ ድራማ የሚሠሩበት ነው። በጾማቸው ሰዓት ሃይማኖተኝነት ይታይባቸዋል። ለሃይማኖታቸውም ይሳደቡላታል። ሃይማኖት ግን የሚኖርላት እንጂ የሚሳደብላት አትፈልግም። ሃይማኖት በራሳችን ላይ ድልን ታቀዳጀናለች እንጂ፣ በሌሎች ላይ ሥጋዊ ድልን አትሰጥም።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለሚያምኑና አዲስ ሰው ለሆኑ ጾም ከጸሎት ጋር አስፈላጊ ነው። ለልማድ ክርስቲያን ግን አስፈላጊ አይደለም። አስቀድመን እንደ ተናገርን፣ ጾም ርእስ፣ ይቅርታና ንስሐ ያስፈልገዋል። ጾም በአዋጅ ሲደረግ፣ ቤተ ክርስቲያን ርእስ መስጥት ይገባታል። በግላችን ስንጾምም ርእስ መያዝ አለብን። አሊያ እግዚአብሔርን ባስቸኳይ እፈልግሃለሁ ብሎ፣ ዝም እንደ ማለት ነው። በውነት ለአዲሱ ሰው ጾም አስፈላጊ መኾኑን ጌታችን ተናግሮአል፤ (ማቴ 9፥16-17)። “ጌታችንን ኢሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

5 comments:

  1. This is a good piece; perhaps the best of all I have seen on this site.

    ReplyDelete
  2. እስኪ እናንት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጾሞችዋ ይታደስ (ተሃድሶ ያስፈልጋታል) የምትሉ ሰዎች ከየትኞቹ ቅዱሳን በልጣችሁ ነው ለማደስ የተነሳችሁ፡ የናንት እናትና አባቶች አልጾሙትም እንዴ? የቀደመችውን ስርአት ማሰቡ ላይ ልብ አላላችሁም? የጾመ ምን ተጎዳ? እስኪ ቀን ይምጣ ለሁላችንም የስራችን ይከፈለናል፤ ቸር ይግጠመን፤
    አንድ ሃሳብ አንድ ልብ ያድርገን!

    ReplyDelete
  3. It is surprising you quote a book that the penetes wrote to attack and undermine the EOTC. Again, the quote is deceptive. Did you hear from anyone or read in any book of the church that purports that Christ is replaced by anyone else? Why do you quote few phrases out of context? The reason probably is that you are doing the work that you have seen from your father,

    ReplyDelete
  4. የኢኦተቤክ ከሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ልዩ ሆና የተገኘችበትና እምነትና ሥርዓቷ ዕድሳት እንደሚያስፈልገው የሚመከርባት ምክንያቱ አልገባህ ይለኛል።
    - እስላም ወንድሞች ከነቢዩ መሃመድ ጀምሮ የወጣ የጾም ሥርዓትን ተከትለው እያከበሩ ስለሆነ፣ የርዕስ ጾም እንዲጀምሩ እስቲ እነሱንም ምከራቸው፤

    ታድያ የአንተ ከየት የመጣ፣ማንን የተከተለ ነው ይባላል? ትግልህ አዲስ የሃይማኖት ሥርዓት ለመዘርጋት ወይስ የኘሮቴስታንት ትምህርትን ወደ ቤተክርስቲያናችን ለማስገባት ይሆን? የትናንቱ ወቀሳ ከሌሎች በተለየንበት ጉዳይ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ሌሎችን በምንመስልበትና የክርስትናችን መሠረታዊ ሥርዓት በሆነው ሁሉ ላይ መጣ።


    ይቺ ጨዋታ እየደመቀች መጣች።

    ReplyDelete
  5. እስኪ ንገረኝ፣ በየዋህነት የጾመው የኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ሲጎዳና ሲጎድልበት አየህ፡ እስኪ አንተ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጾሞችዋ ይታደስ (ተሃድሶ ያስፈልጋታል) የምትል ከየትኞቹ ቅዱሳን በልጠህ ነው ለማደስ የተነሳኸው፡፡ የአንተ እናትና አባት አልጾሙትም እንዴ? የቀደመችውን ስርአት ማሰቡ ላይ ልብ አላልክም? ነው ወይስ ሰው በህገ ልቦና(በየዋህነት) ሲጾም አይዋጥልህም / ቅር ይልሃል እንዴ? ለመሆኑ እራስህን አይተሃል? የጾመ ምን ተጎዳ?

    ReplyDelete