Wednesday, 16 March 2022

“የሎጥን ሚስት አስታውሱ” (ሉቃ. 17፥32)

 Please read in PDF

ስለ ኢየሱስ ብዙ ተናግሬአለሁ፤ ከእንግዲህ ስለ ማርያም በመናገር ዘመኔን አሳልፋለሁ” (ወደ ኦርቶዶክስ ከተመለሱት አንዱ የተናገረው)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ወደ ኋላ ስለ መመለስ ጠቅሶ ከተናገራቸው ምሳሌዎች አንዱ፣ ወደ ኋላ በመመለስዋ ምክንያት፣ የጨው ሃውልት የኾነችውን የሎጥን ሚስት በመጥቀስ ነው። የሎጥን ሚስት በምሳሌነት ከማንሳቱ ጋር አያይዞ፣ እንዲህ የሚል ምሳሌም አብሮ ተናግሮአል፤ “በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በእርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ።” ይላል። ጌታችን ይህን ምሳሌ ጠቅሶ ባስተማረበት ቦታ የነበሩ ሰዎች፣ በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በመኾናቸው፣ የቤቶቻቸው ጣራ ክፍትና ለመዝናናት ምቹ እንዲኾን ተደርጎ የተሠራ ነበር።

በመጨረሻው ዘመን ወይም ጥፋት በቤቱ ላይ የሚደርስበት ሰው ግን፣ ንብረቱን ከጥፋት ለማዳን ወደ ታች መውረድ ወይም ወደ ቤቱ ለመመለስ ማሰብ አይኖርበትም። ምክንያቱም ንብረቱን ስለ ማዳን ሲያስብ፣ ልትተካ የማይቻላት ነፍሱን ሊያጣትና ሊሞት ይችላልና። ጌታም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ “ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ኹሉ ያጣታል። ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል” ይላል፤ በሌላም ስፍራ ጌታችን እንዲህ ብሎአል፤ “ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” (ዮሐ. 12፥25) ይላል።

የአማኞች ወይም ኢየሱስን እንከተላለን ለሚሉ ትልቁ ፈተና፣ ከኢየሱስ ይልቅ የሚያስበልጧቸው ነገሮች መብዛት ነው። ብዙዎች ኢየሱስን እንደሚከተሉ ቢናገሩም፣ ከኢየሱስ ይልቅ አስበልጠው የሚያዩአቸው ነገሮች አሉአቸው። ጌታችን ኢየሱስ እኒህን በብዙ መንገድ ገልጦአል፤ ለአንዳንዶች ከኢየሱስ ይልቅ ቤተሰብ (ማቴ. 10፥37)፣ ገንዘብ (ማቴ. 6፥24) ይበልጥባቸዋል። ለዚህ ነው ኢየሱስ ሕይወቱን እንኳ ሊጠላ ወይም ሊንቅ የማይወድድ ቢኖር፣ ለእርሱ እንደማይኾን በግልጥ የተናገረው።

የዘላለም መዳናችን ወይም ልጅነታችን እንኳ ከኢየሱስ በታች ነው፤ ቅዱሳን መላእክት፣ ቅድስት ማርያም፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰማይና ምድር ኹሉ ከኢየሱስ በታች ናቸው። ኢየሱስን እንከተላለን ለሚሉ ዛሬም፣ የማርያም ጸሎት ሰሚነትና አማላጅነት አልቆረጠላቸውም፤ ዛሬም ማርያም ጸሎትን አትሰማም ብለን ስንናገር፣ የሚከፋቸውና እንደ ናቅናትና እንደማናከብራት አድርገው የሚናገሩ፣ “ወንጌል ገባን ባይ ተላላዎች” ዙሪያችንን ከብበዋል። ይህ ብቻ አይደለም፣ በቀደመ የኦርቶዶክስ ዘመን አገልግሎታቸው፣ ማርያምንና ሌሎችን ፍጡራንን ያመለኩበትንና ያስመለኩበትን አልፎም ዛሬም ድረስ እያሳተ ያለ መዝሙራቸውን፣ ስብከታቸውን  … በአደባባይ ሳይናዘዙና ስህተት መኾኑን ገልጠው ንስሐ ሳይገቡ ተቀላቅለውን፣ ብቅ ጥልቅ የሚሉ “ዘማርያንና ሰባክያን” በዙሪያችን አሉ። የተሐድሶ አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ በአስመሳዮችና ወንጌል አልባ በኾኑ ሰዎች መከበቡ ልብ ይሰብራል!



ከሰሞኑ ከተለቀቁት የ“ወደ ኋላ ተመልሰናል” ከሚሉ አታካች ንግግሮች መካከል፣ አንዱ ወደ ኋላ ተመላሽ እንዲህ ይላል፤ “እንዴት ሃይማኖቴን እንደ ቀየርኹ በማላውቀው መንገድ፣ ለሠላሳ ስድስት ዓመታት ከእናት ቤተ ክርስቲያን ወጥቼ በሌላ ቤት አገልግያለሁ። … እስከ ዛሬ ድረስ በማገልገሌም እጸጸታለሁም” ይላል። እንግዲህ እጅግ አስደናቂ በሚኾን መንገድ መለወጡን ሳያውቅ፣ ሠላሳ ስድስት ዓመታት እንዳገለገለ ይነግረናል። የብዙዎች ከተሐድሶነት ተመልሰናል የሚሉት ንግግር፣ ከዚህ እምብዛም የተለየ አይደለም። እንዴት እንደ ተለወጠ ያላወቀ፣ እንዴት ኢየሱስን ሳገለግል ኖሬአለሁ ሊል ይችላል?!

እውነት ነው፤ ኢየሱስን ብቻ ማክበር ዋጋ ያስከፍላል፤ ኢየሱስን ብቻ ማምለክ ወዳጅ አያበዛም፤ ኢየሱስን ብቻ ማወጅ እንጀራ ያሳጣል፤ ኢየሱስ፤ ኢየሱስ ብቻ ማለት አጀብ አያስከትልም፤ ኢየሱስን ብቻ መናገር ተከታይ አያስገኝም። እናውቃለን፣ ከኢየሱስ ጋር ማርያምን አዳብሎ መስበክ ብዙ ብር ያስገኛል፤ እናውቃለን ኢየሱስን ሸቃቅጦ መስበክ “አቡነ፤ አባ” ያስብላል። ለዚህም ነው ተመላሾቹ ሳያፍሩ፣ ስለ ኢየሱስ በቃን! ቀጣይዋ የዕድሜያችን ስብከት ማርያም ናት ለማለት ምላሳቸው ያልተንተባተበው!

በእርግጥ እኒህ ሰዎች፣ ሰማይ ሙሉ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም፤ በቀንና በሌሊት ሳያርፍ የሚዘምርለትን ኢየሱስን አያውቁትም፤ ታርዶ የቆመው መሲሕ ኢየሱስ፣ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። … ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።” (ራእ. 4፥8፡ 10-11) ተብሎ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንደሚዘመርለት ጨርሶ አያውቁትም።

እኛ ስለ ኢየሱስ ስንዘምር፣ ስንሰብክ፣ ስናውጅ፣ ስንለፍፍ፣ ስንናገር … ጨርሶ አንታክትም፤ አንሰለችም፤ ስለ ኢየሱስ ስንዘምር ኹለንተናችን በእርሱ ፍቅር ተነድፎ፤ ፍጹም ተማርኰ ነው። እርሱ ሲወድደን ነፍስ እንዳላስቀረልን ኹሉ፣ እኛም ስንወደው ነፍስ አናስቀርለትም፤ እርሱን ስናስብ፣ ስንወድድ፣ ስናመልክ፣ ስንጠራው፣ ስንወድሰው፣ ስንቀድሰው፣ ስናሞጋግሰው … ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ በቀር ከፍጡርም ይኹን ከሌላ ልዩ ፍጥረት አንዳች ትዝ የሚለን የለም፤ እናንተ የኢየሱስ ነገር የሰለቻችሁ ሆይ፤ የሎጥን ሚስት አስቡአት፤ ተሐድሶ ነበርን ማለት ቁም ነገር አይደለም፤ እውነታው ግን በኢየሱስ ማፈራችሁንና በኢየሱስ ለመሸቀጥ መመለሳችሁን ደፍረን እንናገራለን፤ ስለዚህ ተግባራችሁም፣ መጽሐፍ ቅዱስ፦ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአድራጎታችሁ ዕፈሩ፤ ተሸማቀቁ” (ሕዝ. 36፥32) እናንተንም፤ በኢየሱስ ያፈራችሁትን ዕፈሩ፤ ተሸማቀቁ እንላለን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

4 comments:

  1. This is a good piece; perhaps the best of all I have seen on this site.

    ReplyDelete
  2. ይህን የምትሰራውን አይቶ ሀሳብህን ያሳካልህ።

    ReplyDelete
  3. Very interesting article. May God bless your work.

    ReplyDelete
  4. እግዚአብሔር ቃለ ሕይወት ያሰማችሁ !!! ይህን ሐሰተኛ ነፍሰ ገዳይ ከንቱ ማኅበር ራቁቱን አውጡት ማንነቱ እነዲህ ይታወቅ እንጂ

    ReplyDelete