Saturday, 7 August 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲፫)

Please read in PDF

ሥራ

ካለፈው የቀጠለ …

ሰዎች ኹሉ ሊድኑ የተጠሩት በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሥራ ብቻ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ግልጥና የማያወለዳ ትምህርቶቹን እንዲህ ያስተምራል፤

ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።” (ኤፌ. 2፥8-9)

ኹሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በኾነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።” (ሮሜ 3፥23-24)

እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤” (ሮሜ 9፥30)


ከዚህ አንድ በኾነ መንገድ፣ የሰው ሥራ ሰውን ያድን ዘንድ አይችልም። የሰው ሥራ (ጽድቅ) በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ጥዩፍና ርኩስ ነው። “ኹላችን እንደ ርኩስ ሰው ኾነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ኹላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።” (ኢሳ. 64፥6)፣ ቅዱስ ጳውሎስም በግልጥ ቃል፣ “አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። … ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤” (ሮሜ 3፥19-20፡ 22)። በሌላ ንግግሩም ሐዋርያው ሲናገር፣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ያላወቁ አይሁድ፣ የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ሲሹ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አለመገዛታቸውን ይገልጣል፤ (ሮሜ 10፥3)።

ከዚህም የተነሣ ለእኛ ሲል በሞተውና በሥራው ባጸደቀን፣ በጌታችን ኢየሱስ ላይ ብርቱ እምነትና ትምክህት አለን (ሮሜ 4፥25፤ 5፥1-3፤ 8፥32፤ 1ተሰ. 5፥9-10)፤ ይህ እምነታችን ግን ሙሉ ለሙሉ ባልተዋጀው ዓለም ላይ ስንመላለስ የሚያድግና ከተቀበልነው መዳን የተነሣ መጋደልና መትጋትን የሚሻ ነው። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ “… “በጸጋው ድነናል” እያሉ የሰው ልጅ ለመዳኑ ምንም እንደማይጠበቅበት በማስመሰል ሰዎችን ወደ ሞት ጎዳና የሚመሩ የጥፋት መንገድ ሰባኪዎች ናቸው።”[1] በማለት በአእላፍ የጥላቻ ቃላት ማንን በግልጽ እንደ ተናገረ ባይታወቅም፣ ከእምነት እንቅስቃሴ መምህራን በቀር፣ ጤናማ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ፣ የያረጋል አበጋዝን ንግግር እንደማይናገር፣ እንደማያስተምር፣ እንደማያምን እሙን ነው።

ከዚህ ባሻገር፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ኹለተኛውን የመዳን ሂደት ለአንደኛው የመዳን ሒደት ሰጥቶ ሲያቀርብ እንመለከተዋለን። ሰው በሥራው እንደሚጸድቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይናገር እያወቀ፣ አማኝ ከዳነ በኋላ መልካም ሥራ መሥራት ይገባዋል ከሚለው ዐሳብ ጋር ኾን ብሎ ሲያምታታ ይስተዋላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ግልጽ ነው፤ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ከሰው ምንም አልፈለገም፤ እንዲኹ ወደደው (ዮሐ. 3፥16)፤ ኀጢአተኛና ደካማ ሳለ አፈቀረው፤ በልጁ ሞትም ታረቀው (ሮሜ 5፥6፡ 8፡ 10)፤ ከአማኙ ለመዳን የተጠበቀው እምነት ብቻ ነው። በእምነት የዳነው ሰው ደግሞ ከእርሱ ምስክርነትና የሕይወት ፍሬ ይጠበቅበታል፤ በክርስቶስ ስለዳንን፣ “ሕግን በእምነት አንሽርም፤ ይልቁን ሕግን እናጸናለን እንጂ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኹለቱ ሥራዎች ግልጥ አስተምህሮ አለው። አንደኛው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች መዳን የሠራው ምትክና ወደር የሌለው ሥራ ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ አማኞች በክርስቶስ ሥራ ካመኑና ከዳኑ በኋላ፣ “እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርበት” (ኤፌ. 2፥10) ታላቅ ሥራ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይ በአዲስ ኪዳን “ከሕግ በታች” የሚለው ሐረግ የሕግ ትእዛዛትን በመፈጸም ሊድኑ ተስፋ የሚያደርጉትን ሊያመለክት ይችላል። በዚህ አጠቃቀም “ከሕግ በታች” ያሉት ገና ከኀጢአት በደል፣ ብክለትና ኀይል በታች ናቸው፤ ሮሜ 6፥14-15፤ ገላ. 5፥18። “ከሕግ”፣ “በሕግ” ወይም “የሕግ ሥራ” ደግሞ ይህን ዐሳብ ሊያመለክቱ ይችላሉ (ሮሜ 3፥20፤ 4፥14፤ ገላ. 2፥16፤ 3፥2፡ 5፡ 18)፤ ጸጋ እንጂ ሕግ ሰውን የማጽደቅ ኀይል የለውምና፤ ሮሜ 3፥21-24።[2]

ያመኑት የዘወትር ሥራቸው ይህ ነው፤ “በየቀኑም በአንድ ልብ ኾነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤” (ሐ.ሥ. 2፥46) ለእውነተኛ አማኞች ይህ የዘወትር ትክክለኛ አምልኮአቸው ነው!

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ስለ ሥራ ብቻ ብርቱ ስህተት

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ስለ ሥራ ኹለት ነገሮችን እጅግ አምታትቶ ያቀርባል፤ በአንደኛው ዐሳቡ፣ መዳን በሥራችን፤ በጽድቃችን ነው ይልና መልሶ ደግሞ፣ “ድኅነትና ዘላለማዊ ሕይወት በሰው ጥረትና ዓቅም የተገኘና የሚገኝ ሳይኾን በእግዚአብሔር ቸርነት የተሰጠ”[3] ነው ይላል። በሌላ ንግግሩ መልሶ፣ “መልካም ሥራ በእምነት ላይ ተመሥርቶ የሚያድግ መኾኑን እናምናለንና”[4] ይላል። ሲቀጥልም፣ እንዲህም በማለት በግልጥ ይናገራል፤ “እኛን ለማዳን በእግዚአብሔር በኩል ያስፈልገው የነበረው ነገር ኹሉ የተፈጸመ ቢኾንም በእኛ በኩል ያለው ግን የተጀመረ እንጂ ገና ያልተቋጨ[ገና ብዙ ሂደቶችን ማለፍ የሚገባው][5] ነው።”[6]

ሥራ ለመዳን ወይስ ሥራ የዳንን መኾችንን የሕይወት ፍሬ መገለጫ ነው? የሚለውን  የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ኹለቱን ደባልቆና አጨማልቆ ያቀርባል። በግልጥም እንዲህ ይላል፣ “ለመዳን ከእምነትና ምሥጢራት ጋር መንፈሳዊ ተጋድሎና በመልካም ሥራ መጋደልና እስከ መጨረሻው መጽናት ይገባል”[7] ለዚህም ዐሳቡ ማጽኛ በተደጋጋሚ ምጽዋትን የኀጢአት ማስተስረያ አድርጎ ያቀርባል፤[8] ደግሞም፣ ምጽዋት በፍርድ ቀን ይቅርታ ያስገኛል፤[9] ምግባርና ተጋድሎ ወደ ሰማይ የሚያወጣ መድኀኒት ነው፤[10] ጾም አጋንንትን ያባርራል፣ ክፉ ዐሳቦችን ያስወግዳል፣ ልብን ንጹሕ ያደርጋል፤[11] አዳም ባለመጾሙ ምክንያት ድል ኾነ፤[12] እናም ለመዳን ከእግዚአብሔር ጸጋና ቸርነት ባሻገር ምሥጢራትንና ተጋድሎን እንዲሁም የራሱም ሥራ እጅግ አስፈላጊ እንደ ኾነ ሲናገር እሰማዋለን።[13]

እንዲያውም በግልጥ፣ ከጥምቀት በኋላ የሚሠራን ኀጢአት ማስወገጃና ማጠቢያ መንገድ ምጽዋት እንደ ኾነ ስለ ኀጢአት ኹሉ የፈሰሰውን (1ዮሐ. 1፥7፤ 2፥1-3) በድፍረት ክዶ ያስተምራል።[14] ያረጋል አበጋዝ፣ እጅግ የሚያስደንቀው ነገሩ፣ ስለ ምስጢራት፣ ስለ ውኃ ጥምቀት፣ ስለ ምጽዋት፣ ስለ ጾም … ብዙ ተናግሮ፣ ልጅነት ስለሚገኝበት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ግን አንድም ቃል አለመናገሩ፣ ምን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያልተረዳ አሳዛኝ ሰው እንደ ኾነ ማስተዋል አያዳግትም! በርግጥም ስለ ውኃ ጥምቀት እንጂ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምንነት ፈጽሞ የተረዳም አይደለም አልያም አፍቃሬ ምስጢራት በመኾኑ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ጨርሶ አያምንበትም!

በግልጥ ቃል፣ አስቀድመን እንደ ተናገርን ሰው በክርስቶስ ሥራ በማመን ብቻ ይድናል፤ ከዳነ በኋላ ደግሞ የሕይወት ፍሬ ከመዳኑ ወይም ከመጽደቁ የተነሣ በሕይወቱ ይታያል፤ ይህም ታላቁ የመንፈስ ቅዱስ ሥራና ሂደታዊ የመታዘዝ ሕይወት ነው! ነገር ግን ስለ ዳነ ይሠራል እንጂ ለመዳን አይሠራም፤ ሲድንም በእግዚአብሔር ጸጋ ይድናል፤ ከዳነ በኋላም በእግዚአብሔር ጸጋ ይሠራል! ሰው ያለ እግዚአብሔር ምሕረትና ጸጋ ባዶ ነውና፤ መጽሐፍ እንደሚል፤ የኾንነውን ኹሉ የኾንነው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው!

ይቀጥላል …

 



[1] ገጽ 203

[2] ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርተ ክርስቶስ፤ ገጽ 117

[3] ገጽ 191

[4] ገጽ 192

[5] ገጽ 201

[6] ገጽ 199

[7] ገጽ 202

[8] ገጽ 207፤ 236፤ 238-239

[9] ገጽ 240

[10] ገጽ 214

[11] ገጽ 226

[12] ገጽ 230

[13] ገጽ 215

[14] ገጽ 236

1 comment:

  1. አንተን ብሎ ሰባኪ አሁን እኮ አሜን የሚል አይጠፋም አይ መናፍቅ ያንተን መጨረሻ ያሳየኝ።666 የእናንተ ሚስጥ እኮ ዘማሪ ሙሉ ቀን ዘማሪ አዱኛ ተናግሯል እናም ብዙ አውቃለሁ አትበል

    ReplyDelete