ካለፈው የቀጠለ …
ሥራ
የክርስትና
ትምህርት ጤናማና መዳን የሚገኝበት ቃል ወይም ትምህርት ተብሎ ተነግሮአል (ሐዋ. 13፥26፤ 1ጢሞ. 6፥3፤ 2ጢሞ. 1፥13፤
2ጢሞ. 3፥15)፤ ትምህርቱ ጤናማ ከኾነ የኑሮ ዘይቤና ጠባዩም ፍጹም ጤናማ መኾኑ አያጠራጥርም። ጤናማው ትምህርት ለእግዚአብሔር
ክብር (Orthopraxy) በሚያመጣ እውነተኛ ሕይወት እንድንመላለስ ያደርገናል፤ ይህ ጤናማ ትምህርት ደግሞ ርትዕት ከኾነች እምነት
(Orthodoxy) ጋር ፈጽሞ ሊነጣጠል የሚቻለው አይደለም። ሕይወት የሚቀዳውና የሚመነጨውም ከእውነተኛ ትምህርትና ከእውነተኛ ፍቅር
(Orthopathy) ነውና።
በሕይወት
ለመተከልና ፍሬ ለማፍራት፣ በእውነተኛ እምነትና ትምህርት መተከል ግድ ነው፤ በእውነተኛ ትምህርትና እምነት ያልተተከለ፣ እውነተኛ
የኑሮ ምልልስና እውነተኛ ክብርን ሊያመጣ በሚችል የምግባር ምስክርነት አይመላለስም። የእስራኤል ትልቁ ውድቀት፣ የተሰጣትን ሕግ
በራስዋ ሥራና በዘልማድ ለመፈጸም መሞከርዋ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሕጉን የሰጣት በእምነትና በእውነተኛ መታዘዝ እንድትፈጽመው
ነበር። ዛሬም የእግዚአብሔር መሻትና ፈቃድ ነው!
እግዚአብሔር፣
እንዲሁ በነጻ የዘላለም ሕይወትን በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑት ኹሉ እንደ ሰጠ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይመሰክራሉ። “በእርሱ
የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐ. 3፥16)፣ “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር
ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።”
(ሮሜ 5፥8)፣ “ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ኾነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ[1]
በበደላችን ሙታን እንኳ በኾንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥” (ኤፌ. 2፥4-5) … እኒህና አያሌ የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍሎች ሰው በሥራው ጨርሶ እንዳልዳነ የሚመሰክሩ ናቸው።
በባለፉት
ክፍሎች ደጋግመን እንዳነሣነውም፣ ሰው መዳን የሚችለው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሠራለት ሥራ ሲያምን ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን
መዳን ወይም ነገረ ድኅነትን የሚያስቀምጠው፣ በሦስት መንገድ ነው፤ ይኸውም፦ አንድ አማኝ በትክክል በክርስቶስ
ኢየሱስ ጌትነትና አዳኝነት ካመነ በኋላ፣ የማይቋረጥ፣ የሚቀጥል፣ የሚያድግ፣ የሚጐለብት፣ የሚበዛ፣ የሚታይ ቅዱስ ሕይወት ወይም
የቅድስና ሕይወት ይካፈላል። ይህንም እንዲህ ማለት እንችላለን፤ ልክ እንዳለፈና እንደ ተከናወነ ኹኔታ ብንወስደው፣ የመዳን
እምነት አንድ ጊዜ የምናምነውና ልጅነትና የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት ሲኾን፣ “እንደ ምሕረቱ
መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን” (ቲቶ 3፥5) ብለን የምንመሰክርበት
ነው።
ወንጌልም የሚሰበክበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት፣ “በእርሱ
የሚያምኑ ኹሉ በስሙ የኃጢአታቸውን ስርየት እንዲቀበሉ” (ሐ.ሥ. 10፥43)፣ “የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት
መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ” (ሐ.ሥ. 28፥17-18)
ነውና፡፡ በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምሥራች ብሎ የሚያበሥረው፣ “እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቆጥርለት” ሰው ነውና (ሮሜ
4፥6)።
ኹለተኛው፣ አኹን በዚህ ምድር ላይ ሳለን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ
የምንኖረውና የምንለመማደው ሕይወት ነው። “እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ ሳይኾን”
(ቲቶ 3፥5)፣ የክርስቶስን ሥራ በማመን ካገኘነው እምነት የተነሣ፣ በመታዘዝና እግዚአብሔርን በመምሰል ወደ ልጁ መልክ
የምናድግበት ታላቅና ክቡር ሕይወት ነው። አማኞች በዚህ ሕይወት ሲመላለሱ ሊያስተውሉ የሚገባቸው እውነታዎች አሉ፤ እኒህም፦
1.
አማኞች መዳናቸውን ተግተው መጠበቅ ይገባቸዋል፤ በቅዱስ ቃሉ፣
በመንፈስ ቅዱስና በጸሎት በመበርታት ከኀጢአት ሊርቁ፣ ከኀጢአት ጋር ሊጋደሉና “የእምነታቸውን
ፍፃሜ እርሱም የነፍሳቸውን መዳን እየተቀበሉ፥” (1ጴጥ. 1፥9)፣ “ከኃጢአት ጋር
እየተጋደሉ”
(ዕብ. 12፥4) የቅድስናን መንገድ ሊለማመዱና ሊያድጉበት ይገባል። በግልጥም፣ ከዲያብሎስና ከመንግሥቱ ጋር በተለይም፣ “የሰውንም
አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ ለማፍረስ፣ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ ለመማረክ”
(2ቆሮ. 10፥4) ብርቱ ጦርነትን ይገጥሙ ዘንድ አማኞች ጥሪን ተጠርተዋል፤
2.
ክርስቲያኖች ከዳኑ በኋላ በዚህ ምድር ይኖሩ ዘንድ የተጠሩት ኑሮ፣
“ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፤” (ቈላ. 3፥3) እንዲል፣ ፍጹም
ለክርስቶስ ክብር ብቻ መኾን እንዳለበት ነው፤ ምክንያቱም፣ “ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት በእርሱ[በኀጢአት] አንኖርምና” (ሮሜ
6፥2፡ 6፡ 10፡ 18፡ 8፥13፤ 1ጴጥ. 2፥24))፣
3.
ዘወትር ቅዱስ ቃሉን በመታዘዝ ልንኖር ወይም ልንመላለስበት ይገባናል።
እንዲሁም፣ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤” (ዮሐ. 8፥30) እንዲል፣
መዳናችንን ከሚገልጡትና ከሚመሰክሩት እውነታዎች አንዱ፣ ክርስቶስን መውደዳችን በሕይወታችን ልክ ፍጹም መታየቱ ነው፤ “ትእዛዜ በእርሱ
ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው” (ዮሐ. 14፥21)፣
4.
ዘወትር መንፈስ ቅዱስን በመሞላት በምሪቱ መመላለስም
ይገባናል፤ “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ” (ኤፌ. 5፥18) ሲል፣ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን አማኞች መተግበር
ያለባቸው ትእዛዛዊ ድርጊት መኾኑን ይገልጥልናል። ይህም ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ ቊጥጥር ሥር መኾኑን የሚያመለክት ታላቅ ዐሳብ ነው።
5.
የምድር ምልልሳችን የአማኞች የመጨረሻ ግብ ወደ ኾነው፣ እግዚአብሔርን
በሚመስል ሕይወት እንመላለስ ዘንድ ተጠርተናል፤ “አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና
እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።” (1ጢሞ. 6፥11) እንዲል፣ አማኝ የተጠራለት እውነተኛው፣
የመጨረሻው መዳረሻ እግዚአብሔርን መምሰል ነው፤ (1ጢሞ. 2፥1-2፤ 4፥7-8፤ 5፥4፤ ቲቶ 2፥12-13፤ 2ጴጥ. 1፥2-3፡
6፡ 7፤ 3፥11) እውነተኛ አማኝ፣ “ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጤናማ ቃልና እውነተኛ መንፈሳዊነትን ከሚያጐለብት ትምህርት ጋር
ሊስማማ” (1ጢሞ. 6፥3) እንጂ፣ ከዚህ ከማይስማማ ትምህርት ፈጽሞ ሊርቅ ይገባዋል።
ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ፣ መዳናችን ወደፊት ገና ፍጽምናን
የሚጠብቅና በክርስቶስ
መምጣት የሚጠናቀቅ ነው። “የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት
እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።” (ሮሜ 8፥23)። አማኞች ፍጹም የሚድኑበትና
መንፈሳዊ አካልን በመልበስ፣ እግዚአብሔርን በመምሰል ወይም የልጁን መልክ በመያዝ ፍጹም የምንኾንበትና መንፈሳዊ አካልን የምንለብስበት
አስደናቂ ቀን አለን! መጽሐፍ እንዲህ እንዲል፣ “እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።” (1ተሰ. 5፥9)።
እንግዲህ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ እኒህን ሦስቱን የመዳን ሂደቶች
እንደ ቅዱስ ቃሉ አጥርቶ ከማቅረብ ይልቅ፣ ደባልቆና አንዱን ለሌላው ሰጥቶ ሲያቀርብና የአደባባይ ስህተቱን በሌላው ሲያላክክ
እንመለከተዋለን። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንደሚል፣ እኛ የዳንነው በሥራችን ወይም በገዛ ጽድቃችን ወይም በመልካምነታችን
አይደለም (ሐ.ሥ. 15፥11፤ ሮሜ 3፥24፤ 9፥30፤ ኤፌ. 2፥5፡ 8)።
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment