Sunday, 15 August 2021

ዕረፉ[አድቡ]! (መዝ. 46፥10) - ክፍል ፩

Please read in PDF

መግቢያ

በዚህ ምዕራፍ፣ መዝሙረኛው የሚዘምረው መዝሙር፣ የቆሬ ልጆችን መዝሙር ነው። የቆሬ ልጆች ከቆሬ ወገን የኾኑ ሌዋዊ መዘምራን ናቸው። በንጉሥ ዳዊት የተሾሙና በዳዊትም ዘመን የቆሬ መዘምራን አለቃ ኤማን የተባለ ሰው ያገለግል የነበረ (1ዜና. 6፥31-47) ሲኾን፣ በቅዳሴ ሥርዓት እግዚአብሔርን በአንድነት ያገለግላሉ። በዳዊት መዝሙር ውስጥ፣ በቆሬ ልጆች ከተሰየሙት ሰባት[1] መዝሙሮች መካከል፣ አንደኛው ዝማሬ ይህ ዝማሬ ነው። ዝማሬው የጽዮን ዝማሬ ነው፣ ዝማሬውን የሚዘምሩትም ደናግላን በደናግል የዜማ ስልት ነው። መዝሙሩ የሚዘመረው በኅብረት፣ የመዘምራን አለቆችም እየመሩት ነው።

መዘምራኑ እየዘመሩ በሰልፍ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲሄዱ፣ ደናግላኑ ከበሮ እየመቱ በማጀብ ይከተሉአቸዋል። እጅግ ውብና እግዚአብሔርን በሕዝብ ኹሉ ፊት ከፍ የሚያደርጉበት፣ በእርሱ መታመናቸውንም በአደባባይ የሚገልጡበት ዝማሬ ነው።

መዝሙሩ በትክክል የሚታወቅ ታሪካዊ መቼት ባይኖረውም፣ የመዝሙሩ ክፍል ግን መዝሙር ብቻ አይደለም፤ ይልቁን ትንቢታዊ ይዘትም አለው። በእግዚአብሔር ላይ የመታመንን ዝማሬ እየዘመረ፣ ትንቢትን ወደ መተንበይ ቅርጽም የሚሸጋገር መዝሙር ነው። መዝሙሩ በተለያዩ መተርጉማንና አገልጋዮች አያሌ ርዕሶችም ተሰጥተውታል፤ ለምሳሌም፣ “ብርቱ ምሽግ ነው አምላካችን”፣ “እግዚአብሔር የሕዝቡ መጠጊያ”፣ “እግዚአብሔር የሕዝቡ መጠጊያና የአሕዛብ ድል አድራጊ”፣ “የጽዮን መዝሙር የአምላክን አጠቃላይ ድል በአሕዛብ ላይ ስለ ማክበር”፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” … የሚሉና ሌሎችም ርዕሶች ለዝማሬው ተሰጥተዋል።

“ቋሚ” ነገሮች ኹሉ ይናወጣሉ!

መዝሙረኛው በሚዘምረው መዝሙር ውስጥ፣ የማይለወጥና ቋሚ ደግሞም የማይናወጥ እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን ሲናገር፣ ሌሎች ከእግዚአብሔር ውጭ ያሉ ነገሮች ኹሉ የሚናወጡትና የሚወድሙ መኾናቸውን በዝማሬ አሰምቶ ይዘምራል። ሰዎች የተደገፉባቸው ነገሮች ኹሉ አይጸኑም፤

1.   ምድር ትነዋወጣለች፦ ሰው ለመውደቅ ቢያስብ፣ ምድርን ይዞ ከመውደቅ፣ ከሚደርስበትም ታላቅ ጉዳት ሊተርፍ ይችላል። ነገር ግን ምድር ለኹልጊዜ ብርቱና ጽኑ የማትፈርስና የማትወድቅም አይደለችም፤ ይልቁን ትነዋወጣለች። ምድር መነዋወጥ ብቻ ሳይኾን፣ ትቀልጣለች (ቊ. 6)፣ ባድማ ትኾናለች (ቊ. 8)፤ ምናልባትም ልትንኰታኰትና ያልተፈጠረች ያህል ልትኾን ትችላለች።

2.   ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ይሰጥማሉ፦ በጦርነት ወቅት ተራሮች ከጠላት መሰወሪያና ማምለጫ ምሽጎች ናቸው። ተዋጊዎች ከጠላቶቻቸው ለማምለጥ በመጠጊያነት ይጠለሉበታል፤ ይሰወሩበታል። ነገር ግን ተራሮች ልክ ቀድሞ በፍጥረት ወቅት በባሕር ልብ እንደ ነበሩት (ዘፍ. 1፥9፤ መዝ. 104፥6) ኅልውናቸው ጨርሶ እስከማይታወቅ ድረስ ሊዋጡና በባሕር ልብ ሊሰወሩ ይችላሉ።

3.   አሕዛብ፣ መንግሥታት ይናወጣሉ፦ ለአሕዛብ ትልቁ ጉልበታቸው በጦር ኀይልና በሃብት የሚመኩ መንግሥታቶቻቸው ናቸው። ከፈርዖን እስከ ናቡከደነጾር፣ ከቂሮስ እስከ ሜዶን ያሉት ነገሥታት ብርታትና አቅማቸው ብርቱ መንግሥትን መጨበጣቸው ነው። መንግሥታት ለሕዝቦች ታላቅ ትምክህትና መተማመኛ ናቸው።

የእስራኤል ጠላቶች የማስፈራታቸው አቅም እጅግ ጠንካራ ነው። ነውጡ ጠንካራ፣ ጨርሶ ኅልውናን የሚፈታተን፣ በብርቱ ነፋስ እንደ ተናወጠ ባሕር የመኖርን ኹኔታ የሚገዳደርና እስካለመኖር የሚያስቆጥር ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በእርሱ ለሚታመኑ የኪዳን ሕዝቡ እንዲህ ነው፤ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (ቊ. 1)። እግዚአብሔር ለእስራኤል ብርቱ መጠጊያ ኃይል፤ በመከራዋም ኹሉ ረዳትዋ ነው። አሜን።

ምድር፣ ባሕር፣ ተራሮች፣ መንግሥታት … ጽኑዓን ይመስላሉ፤ ግን አይደሉም ይነዋወጣሉ፤ ይወድቃሉ፤ ይንኰታኰታሉ። ነገር ግን ቋሚ ነገሮች ኹሉ ቢነዋወጡ፣ ቢንኰታኰቱ አብሮ የማይናወጥና የማይንኰታኰት ብቻውን የጸና አንድ ብርቱ አለ፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው። በእርሱ ዘንድ ፈጽሞ መለወጥ የለም፤ እርሱ ለዘላለም ያው ነውና። ኹሉም ስፍራውን ቢለቅ እርሱ ስፍራውን አይለቅም፤ ያው ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተነገረለት፤ “አንተ ግን ትኖራለህ፤ ኹላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤” (መዝ. 102፥26) በሌላም ስፍራ እንዲህ ተብሎ እንደ ተነገረለት፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።” (ዕብ. 13፥8)

አሜን፤ አምላካችን ዛሬም ለታመኑበቱ፣ ብርቱ መጠጊያ ነው (መዝ. 71፥7)።

ይቀጥላል …



[1] መዝ. 42፣ 84-85፤ 87-88

3 comments:

  1. አንተ ምኑን አውቀኸው ነው? እንደው ብልግና ስድ አደግነት እንጂ ይህን ለመረዳት አቅምህ አይደለም። ብቻ ምን ያደርጋል እንደ አንተ አይነቱን መረን በደህና ጉማሬ አለንጋ ነበር ሁለተኛ አይለምደኝም ማስባል። ደህና አድርጎ ቢሞሸልቁህ ሁለተኛ አይለምደኝም ብለህ በኦርቶዶክስ ላይ አፍህን አትከፍትም ከእምነትም አትወጣም ነበር!

    ReplyDelete
  2. መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው እያሉ ሌላውን ማጣጣል እምነት አይደለም ክህደት እንጂ። በጌታችን ይደረግ የነበረ በሀዋርያትም ከእነሱም በኋላ እንዲሁ። ጌታችን አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኔም በላይ ታደርጋላችሁ በማለት የሚያስደንቁ ነገሮች ሊከወኑ እንደሚችሉ ነግሮናልና

    ReplyDelete
  3. መቼም የናንተ አጋንንት የሚነሣው በግንቦት ልደታ በታህሣሥ ገብርኤል በመጋቢት መድኃኔዓለም በጥር ስላሴ ..... ምን ይሻላችኋል ??? መቼም ከመቃብር ሬሣ እያወጡ ከማሽተት በካራቴ እየተወራጩ ወንጌል ነው በቃሉ ከማሾፍ ሣይሻል አይቀርም።

    ReplyDelete