Friday, 6 August 2021

የክርስቶስ ትንሣኤና የማርያም “ትንሳኤ”

 Please read in PDF

የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የማርያምን፣ “በሦስተኛው ቀን” ሳይኾን፣ በጥር ሞታ ነሐሴ “መነሣቷን” ከዶግማ ትምህርቶቻቸው አንዱ አድርገው ይቀበላሉ። ማርያምን “ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች”ና ፍጹም መካከለኛ አድርገው ለመቀበላቸውም ከሚያቀርቡት ማስረጃዎች አንዱ ይህን፣ “ከሞት ተነሥታለች” የሚለውን ትምህርት በዋቢነት በመጥቀስ ነው።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ስለ “ክርስቶስ ትንሣኤ”ና ስለ ማርያም “ትንሳኤ” ምን ይላል?” የሚለውን ማየት ነገሩን በሚገባ እንድናስተውል ይረዳናል።

1.   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ስለ ሞቱና ከሙታን መካከል ስለ መነሣቱ እጅግ ደጋግሞ አስተማረ፤ (ማቴ. 16፥21፤ ማር. 8፥31፤ ሉቃ. 9፥21-22፤ ዮሐ. 12፥32)፣ ድንግል ማርያም እንደምትሞት ሊነገርላት አይገባም፤ ምክንያቱም ሰው ብቻ ናትና ከሞት ለመነሣት ሰው ኹሉ የሚጠባበቀውን ተስፋ እርሷም ትጠባበቃለችና፣

2.   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተናገረ በገዛ ፈቃዱ ሞቶአል፤ ደግሞም ከሙታን መካከል ተነሥቶአል፤ ይህም በአእላፍ ምስክሮች ተመስክሮለታል፤ (ማቴ. 26፥67፤ 27፥59፤ 28፥6፡ 9፤ ማር. 15፥37፤ 16፥6፤ ሉቃ. 23፥46፤ 24፥5፡ 33-35፡ 46፤ ዮሐ. 19፥30፤ 20፥8፡ 18፡ 21፡ 29፤ 21፥14፤ 1ቆሮ. 15፥4-9) ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በአንድም ቦታ ማርያም ከሙታን መካከል መነሣትዋን የሚያመለክት ክፍል የለም።

3.   የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ የክርስትና ማዕከልና የዘላለም ትምክህት ነው። እርሱ ከሙታን ባይነሣ ኖሮ፣ ክርስትና ከተረት ተረት የዘለለ እውነት አይኖረውም ነበር። እርሱ ከሙታን መካከል በመነሣቱ ግን መዳናችን፣ የዘላለም ተስፋችን ጸንቶአል (1ተሰ. 4፥13)፤ መጽሐፍ፣ “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ … ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። … ”  (1ቆሮ. 15፥14፡ 17-18)፣ እርሱ ከሙታን በመነሣቱ ሞት ተዋጠ፣ ሲዖልም ድል ተነሣ (1ቆሮ. 15፥54-55)፣ ምክንያቱም ሕያውና ፍጹሙ ትንሣኤያችን ነውና (ዮሐ. 11፥25-26)፤ እርሱ ከሙታን መካከል በመነሣቱ ከኀጢአታችንም ጸድቀናል (ሮሜ 6፥6)። ነገር ግን የማርያም ከሙታን መካከል “መነሳት”[የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ የለም እንጂ] ለክርስትና አንዳች የሚጠቅመው ነገር የለም፤ ባትነሣ በክርስትና ላይ የሚያመጣው አንዳች ተጽዕኖ የለም!

4.   የክርስቶስ ትንሣኤ በአእላፍ ሐዋርያትና በቅዱሳን ትምህርቶችና መልእክቶች ጭምር የተንጸባረቀ ነው (ሐዋ. 2፥24፡ 31-32፡ 36፤ 3፥15፤ ገላ. 1፥1፤ ዕብ. 6፥1-2፤ 9፥14) ሰማዕታት በሕይወታቸው ተወራርደው ክርስቶስን ያከበሩትና እስከ ሞት ድረስ የታመኑለት፣ እርሱ ከሙታን መካከል በመነሣቱና ፍጹም ሕይወት ስለ ኾነላቸው ነው።

ከዚህ ባሻገር የእውነተኛ አባቶችም ትምህርት ከክርስቶስ በቀር ከሙታን መካከል የተነሣ እንደሌለና ክርስቶስም በግልጥ ይነግረናል።

“ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” (ዮሐ. 3፥13)

“ስለዚህም ጌታ … በፈቃዱ ሞተ፤ ከተነሣም በኋላ ዳግመኛ አይሞትም፤ ከትንሣኤው በኋላ ግን ጌታ ይህን አልተናገረም፤ ከሰውም ወገን ማንንም ተነሥ፤ ከመቃብር ውጣ አላለም፤ ዳግመኛ እስከሚመጣባት ቀን ድረስ ለሰዎች ኹሉ አንድ ኾነው በሚነሡበት ቀን ሙታን ይነሣሉ አላቸው።”[1]

 “ … ከሙታን ተለይቶ እርሱ ብቻ ስለ ተነሣ ነው እንጂ ሥጋውን ብቻ ሕያው አድርጎ ከኹሉ አስቀድሞ በአስነሣ ጊዜ፤ በተዋሐደው ሥጋ በሞተው ሞትም የሞትን ሥልጣን በአጠፋ ጊዜ ለባሕርያችን ወደ ትንሣኤ የሚያደርስ መንገድ እንደ ኾነ ነገሩ የተገለጠ ነው፤ …”[2]

እናም፣ የ“ማርያምን ትንሳኤ” ማዕከል ያደረገ የትኛውም ጾምና ጸሎት፣ ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከመኾኑም ባሻገር፣ የክርስቶስ ኢየሱስን ትንሣኤ የሚያክፋፋና የሚነቅፍ ነው። ወደ ቃሉ እንመለስና እንደ ቅዱስ ቃሉ የኾነ እውነተኛ ምልሰት እናድርግ ስንል፣ እንዲህ ያሉ ስህተቶችን እናርም፤ ቃሉን በትክክል እንመንና እንታዘዝ ማለታችን ነው! መንፈስ ቅዱስ በነገር ኹሉ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን።



[1] ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ፤ 1988 ዓ.ም፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ምዕ. 59 ክፍል 13 ቊ. 49 ገጽ 209

[2] ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ፤  1988 ዓ.ም፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤  ምዕ. 79 ክፍል 50 ቊ. 51 ገጽ 326

1 comment:

  1. ስለዚህ ማርያም ሞታ ቀርታለች ነው ምትለው

    ReplyDelete