Please read in PDF
የሚጤስ ክር ምኑ ነው የማይጠፋው? ራሱስ ሊጠፋ የሚጤስ አይደለምን? የተቀጠቀጠ ሸንበቆ ምኑ ነው የማይሰበር? ያልጠቀጠቀጠ ሸንበቆ በራሱ ምን አቅም ኖሮት? እልቅ ድቅቅ፣ ስብር እንክትክት ያለውን ደካማ ኀጥዕ፣ መሲሁ እንደሚያቃና፣ እንደሚያበረታታ፣ እንደሚያጸና ነቢዩ ኢሳይያስ የሩቁን እጅግ አቅርቦ አይቷል። ለወደቀው ማኅበረ ሰብ፣ ኢሳይያስ የመጽናናትን ቃል ይናገራል፤ እስራኤል ነጻ ትወጣለች፤ ተበታትናም አትቀርም፣ እንደገናም ትደራጃለች፤ ተስፋ የተቆረጠባት አገር ሆና አትቀርም፤ የዛሉት ምርኮኞቿን የሚያበረታታ ኀይል ይመጣላቸዋል፣ ይሰጣቸዋልም እያለ ነቢዩ ሕዝቡን ያበረታታል። በፍጻሜው ግን ክርስቶስ ሰዎችን ከኅጢአት ነጻ አውጥቶ፣ በታላቅ ትድግናውና ቤዛነቱ ድኅነት እንደሚሰጣቸው የሚያመለክትና፣ ለኀጥዐን ፍጹም ቸርነትና ርኅራኄ እንደሚያደርግላቸው የሚያመለክት ክፍል ነው።
የሚጤስ ክር ምኑ ነው የማይጠፋው? ራሱስ ሊጠፋ የሚጤስ አይደለምን? የተቀጠቀጠ ሸንበቆ ምኑ ነው የማይሰበር? ያልጠቀጠቀጠ ሸንበቆ በራሱ ምን አቅም ኖሮት? እልቅ ድቅቅ፣ ስብር እንክትክት ያለውን ደካማ ኀጥዕ፣ መሲሁ እንደሚያቃና፣ እንደሚያበረታታ፣ እንደሚያጸና ነቢዩ ኢሳይያስ የሩቁን እጅግ አቅርቦ አይቷል። ለወደቀው ማኅበረ ሰብ፣ ኢሳይያስ የመጽናናትን ቃል ይናገራል፤ እስራኤል ነጻ ትወጣለች፤ ተበታትናም አትቀርም፣ እንደገናም ትደራጃለች፤ ተስፋ የተቆረጠባት አገር ሆና አትቀርም፤ የዛሉት ምርኮኞቿን የሚያበረታታ ኀይል ይመጣላቸዋል፣ ይሰጣቸዋልም እያለ ነቢዩ ሕዝቡን ያበረታታል። በፍጻሜው ግን ክርስቶስ ሰዎችን ከኅጢአት ነጻ አውጥቶ፣ በታላቅ ትድግናውና ቤዛነቱ ድኅነት እንደሚሰጣቸው የሚያመለክትና፣ ለኀጥዐን ፍጹም ቸርነትና ርኅራኄ እንደሚያደርግላቸው የሚያመለክት ክፍል ነው።
አዎን!
በሥጋ ሞቱ ሊያድነንና ሊቤዠን ወደዚህ ዓለም የመጣው ቅዱሱ መሲህ፣ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በኀጢአት ለወደቅነው ለእኛ
የሕይወት ትንሣኤያችን ነው። በመምጣቱ ፈጽሞ አድኖናል፣ ተቤዥቶናል፣ አስታርቆናል፣
ከአባቱና ከእርሱ፣ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር እንኖር ዘንድ የጽድቅ ብቃት ኾኖናል፤ እርሱ በበደላችንና በኀጢአታችን ሙታን የነበርነውን
(ኤፌ. 2፥1)፣ እጅግ ሊጠፋ እንደሚጤሰው ክር ልንጠፋ የደረስነውን፣ ደቅቀን እንደ ሸንበቆ ያለነውን፣ አንዳች ጥቅም ያልነበረንን
… የተጠጋጋን ብቸኛ መጠጊያ አምባችን ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችንና መድኀኒታችን።
በዘመነ ሥጋዌው በምድር ይመላለስ በነበረበት ጊዜው፣ በምድሪቱ ላይ ቁንጮ
ከነበሩት ኃጢአተኞች ጋር በአንድነት ተቀምጦ ያወራ፣ “ያወጋ”፣ አብሯቸው ይመገብም ነበር፤ “አንድ ቀን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና “ኀጢአተኞች” ሁሉ ሊሰሙት በዙርያው ተሰበሰቡ። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ይህ ሰው ኀጢአተኞችን
ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል” እያሉ አጉረመረሙ።” (ሉቃ. 15፥1-2) እንዲል፣ ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ በዚያ ዘመን በማኅበረ ሰቡ ዘንድ በግልጥ ከታወቁ ኀጢአተኞች ጋር በአንድነት ተገኝቷል፤ ተመላልሷል። በዚህም ለኀጢአተኞች
ሩህሩኅና አዛኝ ልብ እንዳለው አሳይቶናል።
እርሱ ራሱን ከታወቁ ኀጢአተኞች ጋር አስተባብሮ ነበር፤ ከኀጢአተኞች ጋር
በመኾኑም እርሱ ራሱ እንደ ኀጢአተኛ ተቈጥሯል። ጌታ ኢየሱስ ከኀጢአተኞች ጋር ግልጥ የኾነ ግንኙነትን መስርቷል፤ አላፈረባቸውም፤
አልተጠየፋቸውም፤ አልታዘባቸውም፤ አላሸሞረባቸውም፤ አላንጓንጠጣቸውም፤ አላላገጠባቸውም፤ አልተሳለቀባቸውም። ፊቱ ኀጢአተኞችን የሚጣራ
እንጂ የሚገፋተር አልነበረም፤ ይህ እጅግ ግሩም ድንቅ አምላክ መኾኑን ያሳያል። የሚጤሰውን ክር የማያጠፋ አምላክና መድኀኒት ነውና!
እናም በግልጥ፣ ከእነርሱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ ከብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና
ኀጢአተኞች ጋር እንዲሁም ከፈሪሳውያን ወገን ከነበሩ ጸሐፍት ጋር፣ በአንድነት ሁሉም እያዩት ተቀመጠ፤ በላም። የበሽተኞችና የሕመምተኞች
ጌታ ኀጢአተኞችን ወደ ንስሐ ሊጠራ በኪደተ እግሩ በመካከላቸው ተመላለሰ፤
(ማር. 2፥15-17)። እኒህ ኀጢአተኞች ጌታ በሄደበትም ሁሉ እየተሰበሰቡ ቅዱስ ቃሉን ይሰሙ ነበር። በልባቸው ኀጢአታቸውን አምነው
ለመጡ ሁሉ ጌታችን የሚያንጠበጥብና የሚያረካ የሕይወት ወንዝ ውኃ አለውና።
ጌታ ኢየሱስ
ከኀጢአተኞች ጋር እንዴት ዋለ? በውኑ እንዴትስ ታገሠው? ማኅበረ ሰቡ የተጠየፋቸውን እርሱ ከቶውን አልተጠየፋቸውም፤ ይልቁን ራሱን
ከእነርሱ ጋር ቈጠረ እንጂ። ይህ አስደናቂ የጌታ ኢየሱስ ጠባይ ነው! ቅጥቅጡን ሸንበቆ አይሰብርም፤ ጢያሹን ክር አያጠፋም! ደካማውን
ምልሽ ኀጢአተኞ አይኮንንም፣ አይፈርድበትምም። በእርግጥ ኀያልነቱ በእኛ በደካሞቹ፣ ታጋሽነቱ በእኛ በታካቾቹ፣ ጻድቅነቱ በእኛ በኀጥዐን
ላይ ተገልጧልና፣ ይህ አባት በእውነትም የተዋረደውን ኀጥዕ፣ ደካማውን ሰው አያጠፋም።
አኹን በአገራችን ላይ ያለውን ነገር ስናይ፣ እጅጉን ጆሮ ጭው የሚያደርግ
ነው። ግፍ መውደዳችን፣ ዓመጸኝነትን መጣባታችን፣ የሰውን ስቅየት ማብዛታችን፣ ድህነታችን ሳያንሰን ምድሪቱን የደምና የክፋት እንብርት
ማድረጋችን ጉበት ያፈርሳል፣ ሃሞት ያፈሳል፣ አንጀት ያቃጥላል! ክፋት በጌትነቱ በግልጥ በምድራችን ተገልጧል፤ ብዙዎቻችን መሪዎች
ብቻ እንዳደረጉት እናስባለን እንጂ፣ ዕድሉን ብናገኝ እኛም ከዚህ በማያንስ ነውር ውስጥ የምንዘፈቅ ግብዞች መኾናችንን ዘንግተናል።
እባካችሁ ወደ ብርሃናችን ጌታ እንመለስ!
አዎን! አሁን በአንዳንዶች ላይ በአደባባይ የተገለጠው ክፋት፣ ለብዙዎች
የተግሳጽ ምልክትና የፍርድ ትእርምት ይኾን ዘንድ ተገለጠ እንጂ፣ በምድሪቱ የሚርመሰመሰው አያሌው ሰው በሥራውና በኑሮው እግዚአብሔርን
የማያከብርና ክብሩን የሚቃወም ሥራ በመሥራት የተጠመደ ነው። አንዳንዶቻችን ምንም ብከፋ እንዲህ እንደ እነርሱ አልከፋም እንበል
እንጂ፣ አኹን ባለንበት ሕይወታችን እንኳ የገዛ ወንድማችንን ይቅር ለማለት የሚተናነቀን፣ በዝሙት የተከበብን፣ ሐሜት ጠልፎ የጣለን፣
ክፉ ምኞት ቀስፎ የያዘን፣ ያሻንን ለመፈጸም እንዲያመቸን እንደ ጠፋው ልጅ (ሉቃ. 15፥12) ከእግዚአብሔር ፊት የኮበለልን፣ ከቃለ
እግዚአብሔር ይልቅ ከንቱ ልፍለፋና ተረት የበለጠብን፣ በጭፈራ ቤት ስንከራተት ሌሊቱ አጥሮብን በመንጋቱ የተበሳጨን፣ የሚሊየን ብር
ጉቦና እጅ መንሻ የሚያስቆጣን፣ አንድ መቶና አንድ ሺህ ብር ግን ስንቀበል የሻይ ቡና የሚመስለን፣ የሰው እንጂ የእኛ ኀጢአት የማይታየን
… ግብዝ ፈሪሳውያን ነን።
ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ግብዝነት ፈጽሞ ይጠየፋል፤ አይወድምም። እርሱ
የማያጠፋው ጢያሽ ክር በልባቸው ለማይመኩና ግብዝ ላልኾኑ ኀጢአተኞች ነው። እንደ ጠፋው ልጅ በልባቸው በንስሐ ልብ፣ ምን እንደሚናገሩ
እያሰላሰሉ ወደ እርሱ ለሚመጡት ቅጥቅጥ ሸንበቆዎችና ጢያሽ ክሮች[ኀጥዐን] ክርስቶስ የማያቋርጥ ፍቅርና የማይነጥፍ ምሕረት አለው።
ስለ ኀጥዐተኛ መመለስና መዳን አይደክምም፣ አይታክትም፣ አይዝልምም፣ ፈጽሞ አይሰለችምም። በድቅድቅ ጨለማ ላለ፣ ጧፉ ሊጠፋበት ለሚስለመለም
ኀጢአተኛ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን፣ የሚያድን መድኀኒት ነው። በንስሐ ለሚመለስ ልብ የጌታ እግሮች ሯጮች፣ እጆቹ ተዘርግተው ተቀባዮች
ናቸው።
እውነተኛው ብርሃን ጌታ ኢየሱስ፣ ከእኛ ከልባችን የተሻለ ስጦታ አይፈልግም፤
የፍጡርም መካከለኛነት አይሻም፤ የእኛን በጎነት እንኳ አያሻትትም፣ ከእኛ የሚፈልገው ሊጠፋ ያለውን ተስለምላሚ ጧፋችንን፣ የደቀቀ
ሸንበቆአችንን በተሰበረ ልብ ይዘን እንድንቀርብ ብቻ ነው። እናንተ[እኛ] ደካሞች ኑ ወደ እርሱ ቅረቡ፣ እርሱ ያሳርፋችኋል፤ (ማቴ.
11፥28)፣ በእውነተኛና በተሰበረ የንስሐ ልብ እርሱን ብቻ በመታመን ተመለሱ፤ ያድናችኋል፣ ይታደጋችኋልም፤ አሜን፤ እንዲህ ዐይነት
አምላክ በማምለካችን ደስታችን ወደር የለውም! እርሱ ድካማችንን አይቆጥርም፤ ጢያሽ ጧፋችንን አያጠፋም፣ ቅጥቅጥ ሸንበቆአችንን አይሰብርም፤
በውድቀታችን አይዘብትም፣ ይቀበለናል፣ ይራራልናል፣ አቤቱ ወዳንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፣ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ፤ አሜን።
እግዚአብሔር በልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ እየባረከ ይባርክህ።
ReplyDeleteRealy it's so annoying and amazing message may God bless you
ReplyDeleteወንድሜ ከልቤ የተደሰትኩበት ይህ አስፈላጊ የሆነ ምግብ ብየዋለሁ ተባረክ ፈረሀ እግዛብሔር አይለይህ!
ReplyDeleteስለ የማይነግረው ስጦታ እግዚአብሔር ይመስገን
ReplyDeleteamen
ReplyDelete