Sunday, 25 November 2018

ነገሌ አርሲ ኪዳነ ምሕረት ዛሬም የስብከት ርዕሳቸው እኛ ነን!


   ከነጌሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ባሻገር፣ በኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በግልጽ በከሳሾቻችን “አእላፋት” ክስ ተከሰን የቀረብነው 2005 ዓ.ም ነበር፤ ከዚያኔ ክሶች የማይዘነጋኝ፦ “ኢየሱስን መካከለኛችን ነው” ብሎ ኮርስ ላይ አስተምሯል ብለው፣ ያስተማርኩበትንና ለተማሪዎች የሰጠኹትን የራሴኑ ማስተማርያ አቀረቡ፤ በተመሳሳይ መልኩ ይኸንኑ ትምህርት ያስተማርኳትን “ጓደኛዬን” ምስክር አቁመው አስመሰከሩ፤ ያሳቀኝ ግን ከዚህ በኋላ የተናገሩት ነው፤ “እኛ ጐጃምና ጐንደር ከሚገኙ ከታወቁ ጠንቋዮች ጋር ጥብቅ የትምህርት ቁርኝት እንዳለን በጊዜው የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የስብከተ “ወንጌል” ኀላፊ ተናገረ። እንግዲህ በእነርሱ አመክንዮ “ጐጃምና ጐንደር ውስጥ ʻኢየሱስ መካከለኛዬ ነውʼ የሚል ጠንቋይ አለ ማለት ነው? …”፤ ለምን እንዲህ እንዳሉ ይገባኛል። ክሳችን ከወንጌል ውጪ እንደ ኾነ ሰዎች እንዲያምኑላቸው!!! ዳሩ ከከንቱና ከውሸት ልፍለፋ አይዘልም! ያንን ኹሉ አልፈን ዛሬም በምሕረቱ አለን! ነገንም የምንመካው በጌታችን ኢየሱስ ብቻ ነው! አንዳንዶች አብረውን ጀምረው ዛሬ ስለ ክርስቶስ ጨክነው አብረውን ባይቆሙም!

  ከሳሾቻችን ከኢየሱስ ውጪ እኛን የሚከሱበት ምክንያት የላቸውም፤ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ሳይቀኑ እንዲያው በከንቱ በሰው ለመደመጥ ውሸት ሊቀላቅሉ ተገደዱ! ከሰባት ዓመት በኋላ ደግሞ፣ በቀን 16/3/2011 ምሽት 12፡00-2፡30 በቆየ ዓውደ ምሕረት ላይ “እኛን በሰበኩበት ግሩም ስብከታቸው” ሌላ አዲስ ውሸት ፈጥረው ደገሙ፤ ከውሸቶቹ ኹሉ ይህችኛዋ ፈገግ አስደርጋኛለች፣ እንዲህ የምትለዋ፦ “የሚንቀሳቀሱት ከጀርመን አገር በሚላክላቸው ልዩ ፈንድ [ትልቅ ብር መኾኑ ነው] ነው፤” የምትለዋ፤ አንዲት “ቤተ ክርስቲያን” ልታፍር ሲገባት፣ ሳታፍር እንዲህ ውሸት ስትናገር መስማት ባለ አእምሮ ሰሚን ያሳፍራል።
  ከጀርመን አገር ላኪው ማነው? ግለሰብ ወይስ ድርጅት? ለማን ወይም ለእነማንስ ይላካል? እስካሁን ቢያንስ ስንቴ ተልኮ ይኾን? … ይህን ማጣራት አያስፈልገውም? ነገር ግን ዝም ብለው ዓውደ ምሕረቱ[መዐቱ] ላይ ቆመው አንድ የአውሮፓ ወይም የአሜሪካ ከተማ ጠርተው፣ “ከዚያ ፈንድ ይላክላቸዋል” ማለት በቂያቸው ነው። ምክንያቱም ጠያቂ የለባቸውማ! የሚታመኑ እነርሱ ብቻ እንደ ኾኑ ያስባሉና! ከኹለት ሰዐት በላይ ይህን አውርተው ወንጌል ሰበክን ሊሉ ነውን? ውሸት መፍጠር ተክነውበታል፤ ሲዋሹ ከራሳቸው ይዋሻሉ፤ አያፍሩም ደፋሮች ናቸው፤ የሚያገለግሉትን ሕዝብ ስለማያከብሩ ውሸት ይግቱታል፣ እርሱም ስለማይመረምር ጭጭ ብሎ ይጋታታል!
  ስለራሴ ግን እርግጠኛ ነኝ፤ ድረ ገጽ በስሜ ከከፈተልኝ የልብ ወዳጄ ሙሌና እስከ አኹን ጽሑፎቼን አልፎ አልፎ ቡስት(Boost) ከሚያደርግልኝ ወንድሜ ቢኒ፣ እንደ ዐይን ብሌን ከሚሳሱልኝ ውድ ቤተሰቦቼ በቀር በአገር ውስጥም ይኹን በውጭ፣ በግለሰብም ይኹን በድርጅት የረዳኝ የለም! ደግሜ እላለሁ ማንም የለም!!! እንደ ቁም ነገርም አልቋምጥለትም! ሌላውን ማየት እስከማልችል ድረስ በጌታዬ ኢየሱስ ረክቻለሁና!
   ቀና ብዬ መሄድ እንድችልም ነው መጽሐፍን ያህል ነገር ብዙ ሺህ ብር ተበድሬ ያሳተምኹት! ያውም ብርቱ ተቃዋሚ ፊት ለፊቴ ቆሞ! እና “ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል” እንዲል አገርኛው ብሒል፣ “አባቶቻችን” ቢያንስ ስለኅሊናችሁ ስትሉ አትዋሹ፣ ለእግዚአብሔር ከቀናችሁ ቅንአታችሁን በወንጌል ምስክርነት ግለጡት፣ ቤተ ክርስቲያንን ከወደዳችኋት ደግሞ በ“ዐውደ ምሕረቷ” እየዋሻችሁ አታርክሷት”፤ በእርግጥ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ብቻ ሳይኾን፣ በጳጳሳቱና በሲኖዶስ ደረጃ፣ “በዐይናቸው ያላዩትን ሰው፣ ጠርተን መክረን ዘክረን፣ ያላናገሩትን ሰው አልመለስ ስላለ …” እያሉ ከእኔው ጀምሮ ሲያወግዙ ማየት ከጀመርን ሰነባበትን፤ ጌታ ዕድሜ ከሰጠን የዛሬ ሰባት ዐመት ደግሞ ምን እንባል ይኾን?
   በሊቀ ካህናቱ ሐናና ቀያፋ ፊት ሙሽራው ኢየሱስ ከተዋረደባት ዓለም፣ እኛስ ሙሽራዪይቶች ምን ክብር አለንና እንጠብቃለን?! ምንም! ፈጽሞ አንዳች!!! ትላንት እኛ ከስድስት ሠዐት ጀምሮ እስከ ማታ ጌታችን ኢየሱስን ከባሕርይ አባቱና ከማኅየዊ መንፈስ ቅዱስ ጋር በደስታ አመለክነው፤ እነርሱ ግን “የተሐድሶና የመናፍቃን መመከቻ ልዩ ጉባኤ” ብለው በኹለት አጥቢያ እኛን ሲሰብኩ አመሹ! እግዚአብሔር ግን በውሸት አይከብርም!
   እኛ ከክርስቶስ ወንጌል በቀር አንዳች ዐላማ የለንም! ሰዎች ፊታቸውን ወደ ጌታ ዘወር ያደርጉ ዘንድ ብቻ ወንጌል እንሰብካለን! ሰዎችን ወደ ሌላ ቤተ እምነት የማፍለስ “የቀደመውን ዘመን ስህተት” የምንደግም አይደለንም! ጌታ በረዳን መጠን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን በ“ልጆቿ” ቅዱሱ ወንጌል እንዲደርሳት የመትጋት ትጋትና ቅንአት ብቻ ነው ያለን! በእርግጥ ይህን ስንል ማንም ከእጅግ ጥቂቶች በቀር፣ ከቤቱ ሊያምነን የሚችል እንደሌለ እናምናለን! ግና ከዚህ የተለየ ዓለማም መሻትም የለንም! ጥሪት ማጋበስ፣ ሃብት ማከማቸት፣ በጐችን ሥጋቸውን ለምግብ፣ ጸጉራቸውን ለልብሳቸው እንደሚሸልት ግብዝ እረኞች አይደለንም! በማጣትና በውርደት ውስጥ እንኳ እያለፍን ወንጌልን ከማወጅና ከመመስከር በቀር አንዳች ዐላማ የለንም!
    “ … አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጐ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ አስበው በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታድያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤” (ፊል. 1፥15-18 ዐመት) እንዲል ሐዋርያው፣ እኛም በከተማይቱ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታችን ርዕስ በመኾኑ ደስ ይለናል፤ ብሎናልም፤ አሜን።


9 comments:

  1. በዚህ አገልግሎት እጅግ ተባርከናል ስለጀመራቹ ደስ ብሎናል

    ReplyDelete
  2. እናንተ መናፍቃን እናውቃችዋለን

    ReplyDelete
  3. አንተን ብሎ ዲያቆን ሃፍረተ ቢስ

    ReplyDelete
  4. አውደልዳይ ሌባ ሲያስጠላኝ። አታፍርም ደነዝ!!!!!!

    ReplyDelete
  5. ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ እሮሜ 1÷22

    ReplyDelete
  6. ተረት ከመስበክ እየሱስን ይሰበክ

    ReplyDelete
  7. “ … አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጐ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ አስበው በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታድያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤” (ፊል. 1፥15-18 ዐመት) tebarek

    ReplyDelete
  8. “ … አንዳንዶች ከቅናትና ከፉክክር የተነሣ፣ ሌሎች ግን ከበጐ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብካሉ። እነዚህ፣ እኔ ለወንጌል ለመሟገት እዚህ እንዳለሁ ስለሚያውቁ፣ በፍቅር ይህን ያደርጋሉ፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ሳለሁ መከራ ሊያጸኑብኝ አስበው በቅንነት ሳይሆን ለግል ምኞታቸው ሲሉ ክርስቶስን ይሰብካሉ። ታድያ ችግሩ ከምኑ ላይ ነው? ቁም ነገሩ በቅንነትም ይሁን በማስመሰል በማንኛውም መንገድ ክርስቶስ መሰበኩ ነው። በዚህም ደስ ይለኛል። አዎን፤ ደስ ይለኛል፤” (ፊል. 1፥15-18 ዐመት) tebarek

    ReplyDelete