Monday, 30 December 2024

በተሰቀለው ክርስቶስ ወንጌል አናፍርም!

 Please read in PDF

እናውቃለን፤ ዕርቃንና ወንጀለኛ በሚሰቀልበት መስቀል ላይ መሰቀል፣ ልዕለ ኃያል አምላክ ሲኾን በፍጡራን እጅ መያዙና ፍጹም መከራን ፈቅዶና ወድዶ በ“ሽንፈት” መቀበሉ ውርደት ነው፤ በሰው ዓይንም ሲታይ፣ የሚያሳፍር እንጂ የሚያኰራ አይደለም። እንዲህ ያለውንም ነገር “የምሥራች!” ብሎ መናገር ተቀባይነትና ተከታይን የሚያስገኝ ነገር አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በሕዝብ ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት የሌለውን ወንጌል በይፋ፤ በድፍረት ሰበከ!

ስለ መከራ ተቀባዩ ክርስቶስ ሲናገርም፣ “… የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥” (ፊል. 2፥7-8)፤ አለ፤ አምላክና ጌታ ሲኾን በዚህ መንገድ ማለፉ እጅግ የሚደንቅ ነው። በገዛ ፈቃዱ መለኮታዊ መብቱንና ጥቅሙን በመተው፣ ጌታችን ክርስቶስ ስለ እኛ ይህን በማድረጉ ፈጽሞ አላፈረም!

ቅዱስ ጳውሎስ ጌታ በርሱ አላፈረምና፣ ቆፍጠን ብሎ “እኔም አላፍርበትም” ይላል። ይህ በፍጡር አቅም የሚቻል አይደለም።መንገዱም ሰው የሚወድደውና ቢያደርገው ደስ የሚያሰኘው አይደለም። “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል” (ማር. 1፥1) የምናምንበት ብቻ ያይደለ፣ መከራ ልንቀበልበትና በወንጌሉ ስም ልንጎሰምበትም ነው፤ በወንጌሉ ክብርን የምንሸለውን ያህል፣ መከራና መስቀልም እንጌጥበት ዘንድ ተብሎልናል፤ በመሲሑ መንገድ መሄድና ማለፍ ልጁን መምሰያ ዘላለማዊ ጥበብ አለበት።

ማፈር፣ መሸማቀቅ፣ ውርደትን መፍራት፣ ነቀፋን መሸሽ፣ በስሙ መጠላትንና ስለ ወንጌል መዋረድን መተው ወይም ለመቀበል ባለመፈለግ ማፈግፈግ የእውነተኛ የወንጌል አማኝ መገለጫ አይደለም። በወንጌል አለማፈር በክርስቶስ መመካት ነው፤ ርሱ ባለፈበት የመስቀል መንገድ ለማለፍ መጨከን ፍጹም መታደልና ታላቅ ክብርም ያለው ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ስቁልና መከራ ተቀባይ ጌታ አላፈረም፤ በርሱ በመታወቁ ፍጹም አልተሸማቀቀም፤ በአንድ ወቅት ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አፍሮበት ክዶት ነበር፤ ነገር ግን በኋላ መንፈስ ቅዱስ ጠቅልሎ በወረሰው ጊዜ፣ በገደሉት ፊት ቆሞ እንዲህ አለ፤ “በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። … እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤” በማለት ደጋግሞ ተናገረ (ሐ.ሥ. 2፥23፤ 3፥14-15)። ቅዱስ ጴጥሮስ አላፈረበትም፤ እና ደፍሮ መከራ ተቀባዩን መሲሕ በአደባባይ ሰበከው!

ቅዱስ ጳውሎስ በአንድ ወቅት በሰው ዘንድ ስለሚያስመካው ነገር በዝርዝር ተናግሮ ነበር፤ ብዙ ከዘረዘረም በኋላ እንዲህ አለ፤ “… በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤” (ፊል. 3፥9)፤ በሰው ፊት ድል ነሺና አሸናፊ ኾኖ መታየት ሊያኮራ ይችላል። ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ከመዋረድ አይበልጥም! የምንሰብከው ወንጌል የተሰቀለውንና መከራ ተቀባዩን መሲሕ ማዕከል ያደረገ ነውና። በሰው ፊት ደግሞ ስቁዩ መሲሕን መመስከር አያኮራም፤ ኢየሱስ ግን እኛን ስለ ማዳን መከራንና መስቀልን ታግሦ በማዳን ድልን ተቀዳጅቶአል፤ “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብ. 12፥2) እንዲል፣ ጌታችን ዛሬ በሰማያት በድል አለ፤ እኛም በወንጌሉ ስም የሚመጣውን ውርደትና በተሰቀለው ክርስቶስ ባለማፈር በመንጓደድ ልንኖር ተጠርተናል!

እናም አላፈረብንም አንፈርበት!

No comments:

Post a Comment