የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ
ከቅድስት ድንግል መወለድ፣ ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ ያልተሰማ እጅግ አስደናቂ ምስጢር ነው። ንጉሠ ሰማይ ወምድር ክርስቶስ ኢየሱስ
ሲወለድ፣ ሊቀራረቡ የማይችሉ አካላት በአንድነት ተገናኝተዋል። ኀጢአት በሰዎች መካከል ልዩነትን አድርጎአል፤ ባለጠጋና ድኃ፤
ታላቅና ታናሽ፤ አዋቂና መሃይም፤ አለቃና ምንዝር፤ ጌታና ሎሌ፤ ጥቁርና ነጭ፤ ገዢና ተገዥ … በሚል።
“ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ
አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ” (ሐ.ሥ. 17፥24) በመግቦቱ፣ ምግብን ለሚሹና ተስፋ ለሚያደርጉት ለሥጋ ኹሉ (መዝ.
104፥21፤ 136፥25) በየጊዜው እኩል ይመግባል፤ ሳያዳላ ያደላድላል። ኀጢአት በአድልዎ ያበላሸውን መንገድ፣ ኢየሱስ
ክርስቶስ በመጋቢነቱ አደላደለው፤ ደግሞም ፍጹም አስተካከለው።
በዚህ ምድር ላይ ጠቢባንና እረኞች ወይም
ነገሥታትና እረኞች በአንድነት ፈጽሞ ሊገኙ አይችሉም፤ ጌታ ግን በፍጹም ታማኝነትና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ፣ መንጎቻቸውን
በሌሊት ለሚጠብቁ እረኞች በክብሩ ብርሃን (ሉቃ. 2፥9)፤ ጠቢባንና ነገሥታት ለነበሩት ሰብዓ ሰገል ደግሞ በምሥራቅ በሚያበራ
ኮከቡ (ማቴ. 2፥2) አማካኝነት ያለማዳላት በርቶላቸዋል። በኹለት የተለያየ መንገድና ኑሮ ላሉ መሲሑ እኩል ተገለጠላቸው። ጌታ
ለማንም ፊት አይቶ አያዳላምና፤ (ሐ.ሥ. 10፥34፤ ሮሜ 2፥11)።
በግርግም የተኛው ትሁት ጌታ (ማቴ.
11፥28) በኑሮአቸውና በማኅበረ ሰቡ ዘንድ እጅግ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው እረኞች በርሱ ዘንድ ተገኙ፤ ሰዎች ለማይቀበሉአቸው
ሰዎች፣ መሲሑ ተቀባይና ረዳት ኾኖ መጣ፤ ነገሥታት አያዩንም ለሚሉ ንጉሠ ነገሥት የኹሉ ተመልካች ኾኖ መጣ። ኢየሱስ በግርግም
መወለዱ ለዝቅተኛ ማኅበረ ሰቦች ተስፋና ቤዛ ኾኖ መምጣቱን ይገልጣል፤ ለዝቅተኛ ማኅበረ ሰብ ብቻ አይደለም፤ “ቀራጮችና ጋለሞቶች” (ማቴ. 21፥31) እንኳ ተስፋና አለኝታ
አገኙ። እረኝነት በየትኛውም ማኅበረ ሰብ ውስጥ የተናቀና እጅግ ዝቅ ያለ ሥፍራ ነው፤ መሲሑ ለነዚህ እረኞች ኹሉ መታመኛና ወደ
እግዚአብሔር መቅረቢያ ኾኖ መጣ።
በጌታ መወለድ ወደ ጌታ ከመጡት መካከል፣
ሰብዓ ሰገል ይገኙበታል፤ ሰብዓ ሰገል ጠቢባንም ነገሥታትም እንደ ኾኑ ይታመናል፤ ወደ መሲሑ በሰው ዘንድ እንደ ታላቅ የሚታዩ
ሰዎችም መጥተዋል፤ መሲሑ የኹሉም አምላካቸው፤ በሥጋ የተገለጠ መድኃኒታቸውም ነው። ብዙ ጊዜ ጠቢባንና ባለጠጎች የእግዚአብሔርን ሥራ እንደ ሞኝነትና አላዋቂነት ይቈጥራሉ፤ “ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች” እንዲል፣ ይህ የዓለም ጥበብ እግዚአብሔርን
ወዳለማወቅ ጥበብ የሚነዳቸው ናቸው (1ቆሮ. 1፥21)።
አማናዊው የእግዚአብሔር ጥበብ ግን፣ እረኞችንና
ሰብዓ ሰገልን በአንድነት በግርግሙ ስፍራ አገናኝቶአል፤ ለሰው ፊት የማያደላው እግዚአብሔር በዓለም ፊት ታላላቅም፤ ታናናሽም የተባሉትን
በአንድነት ሰብስቦአል፤ የዓለም ጥበብ ጥቂቶችንና በሰው ፊት የተወደዱትን ብቻ በመሰብሰብ ይሞኛል፤ የእግዚአብሔር ጥበብ ክርስቶስ
ኢየሱስ ግን ኹሉን በመሰብሰብና ባለማዳላት የፍጥረተ ዓለሙ አለኝታ ኾኖ በግርግም ተገልጦአል፤ ትሁቱ ጌታ በድንግሊቱ ክንድ የታቀፈ
ቢኾንም፣ ፍጥረተ ዓለሙን ደግፎ በመያዝና ያለአድልዎ እየመገበ፤ በማዳንም አቻ የሌለው ነው፤ ስሙ ይባረክ፤ አሜን።
No comments:
Post a Comment