በአጭር ቃል፣ በ58 ዓ.ም አከባቢ ነግሦ የነበረው የሮም ቄሣር ኔሮን፣ የሮምን ከተማ ከግማሽ በላይ በእሳት አነደዳት። ያነደበበት ምክንያቱ ከተማይቱ ስለ ደበረችው፣ ሌላ አዲስ ከተማ መገንባት ያመቸው ዘንድና ቃጠሎውን በክርስቲያኖች በማላከክ በኋላ በዚህ ሰበብ፣ ክርስቲያኖችን ለማሳደድና ለመግደል ይመቸው ዘንድ ነው። አባ ጎርጎርዮስ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፣
“ … ብዙ ወንጌል መልእክተኞችን የፈጀው ኔሮን ቄሳር ነው።ለነገሩ መነሻ ያደረገው የሮምን መቃጠል ነው። ርግጥ በዘመነ መንግሥቱ አጋማሽ ላይ የሮም ከተማ በእሳት ጋይታለች። ያቃጠለው ማን እደ ኾነ አልታወቀም። ክርስቲያኖችን አሳጥ ለማጥፋት ኔሮን ራሱ ነው ያደረገው የሚሉ አሉ።”
ይህን ለማድረግ አንድ መንገድን ተከትሎአል፤ ክርስቲያኖች በአብዛኛው የሚኖሩበትን ስፍራ እንዲቃጠል አላደረገም። የከተማይቱን አብላጫ ክፍል ተኩሶ ግን አነደዳት፤ አጋይቶ አመድ አደረጋት። ኮሪደሮችዋን ለማሳመርና በአዲስ ውበት ሊሠራት የከተማይቱን ሰዎች ከምንም ሳይቈጥራቸው ከተማይቱን ከጥቅም ውጭ አደረጋት። ከታሪክ ጸሐፊዎች አንዱ፣ ኔሮን ከተማዪቱ ስትቃጠል ዋሽንት እየነፋ ይጫወት ነበር ብሎአል።
በኋላ ላይ የከተማዪቱ ሰዎች በቊጣ በተነሱበት ጊዜ፣ “አማልክት በክርስቲያኖች ተቆጥተው ነውና ክርስቲያኖች ሊገደሉ ይገባል” ቢልም፣ ክርስቲያኖች ይህን እንዳላደረጉ ሕዝቡ በተረዳ ጊዜ ከዙፋኑ ተሰድዶ በፍጻሜው በገዛ ባሪያው እጅ በሰይፍ ተገደለ።
ያለመውንና ያሰበውን የሮምን ከተማ ኮሪደር እንኳን ሊሠራው፣ ሕይወቱ በስደትና በሰይፍ ቅላት ተቋጨ። ምድራችን ጭካኔያቸው ለምድር የከበዱ መሪዎችን በየዘመናቱ ተፈራርቀውባት አስተናግዳለች። ሃያላኑ ደክመውና ዝለው፣ አስፈሪዎቹ ተርበትበትውና ተንቀጥቅጠው፣ አፈር አይንካን ያሉት አሟሟታቸው እንኳ "ሳያምር"፣ በጭካኔያቸው ልክ ፍትሕ ፊት ነሥታቸው በነርሱም ተጨክኖባቸው አልፈዋል። አስፈሪነታቸው ተሽሮ በፍርሃት በወየበ ፊት ብዙዎች ተሸማቅቀው አልፈዋል። ማንም የማይነካቸው የተባሉት የማንም መጫወቻ ኾነው ታይተዋል።
እንዲህ ያሉ ነገሥታት የከተማ ውበትና ድምቀት የሚያስጨንቃቸውን ያህል፣ ሰውና ሰውነት አያስጨንቃቸውም። የሰው ከቀዬው መነቀል ቁብ አይሰጣቸውም። የማኅበራዊ ሕይወቱ ቢመሰቃቀል ግድ የላቸውም። ራሳቸውን ንጹሕና ንዑድ አድርገው እያቀረቡ፣ ስህተትና ጥፋትን በሌላው እያላከኩ መኖርን፣ የዕድሜያቸው ማራዘሚያ አድርገው መጠቀም የተካኑበት የክፋት ጥበባቸው ነው።
የአገራችንም መሪዎች በንግግራቸው፣ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ” ቢሉንም፣ ለኢትዮጵያ እንጂ ኢትዮጵያዊ ኾነን እንድንኖር ሲተጉልን አንመለከትም። “ሐገር ማለት ሰው ነው” ቢሉንም፣ ለአገር መሬቱ እንጂ፣ ለአገር ልጅ ሰውነት ከቁም ነገር አልተጣፈም። ቊስና ብልጭልጭ ነገር ደርቶአል፤ ሰውና ሰውነት ግን ረክሶአል። አስታዋሽም ያለው አይመስልም።
እግዚአብሔር አምላክ፣ ቊስን ለሰው እንጂ ሰውን ለቊስ አልፈጠረም። ኤፊቆሮሳዊ ቊስ አምላኪነት ሰውን ውስብስብና ሴረኛ አድርጎታል። እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ክፋት በምድር ላይ አልፈጠረም። በሰዎችም ልብ አላኖረም። ሰው ግን ውስብስቡን መንገድ መረጠ። መጽሐፍ፣ “ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤ እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ።” (መክ. 7፥29) እንዲል።
ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ይብዛ! አሜን።
እጅግ በጣም እናመስግናለን
ReplyDeleteለፀጋው ክብር ይሁን
ReplyDelete