Thursday 3 October 2024

“ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” (ፊል. 4፥4)

 Please read in PDF

የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን፣ በኹለተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት የተወለደች ቤተ ክርስቲያን ናት። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ኹለተኛው ሐዋርያዊው ጉዞው፣ ብዙ መከራና እንግልትን ተቀብሎአል። የመጀመሪያው ሐዋርያዊው ጉዞው ብዙ መከራ የሌለበትና ቀለል ያለ ነበር፤ ኹለተኛው ግን ጠንካራና በብዙ መገፋት ውስጥ ያለፈበት ነው።

በርዕሳችን ላይ ያነሳነውን ቃል የተናገረው፣ ሐዋርያው በእስር ቤት ኾኖ ነው። እየተናገረ ያለውም፣ የመልእክቱ መቋጫ ላይ ኾኖ ነው። በክርስቶስ ወንጌል ምክንያት፣ በእስር ላይ ያለ ሰው ምን ሊናገር ይችላል? እኛ በወንጌል ጉዳይ በእስር ውስጥ ብንኾን፣ ምን ልናስብና ምን ልንመክር እንችላለን?

ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር፣ በብዙ አማኞች ዘንድ የተወደደ ነው። የመወደዱን ያህል ግን በብዙዎች ሕይወት ላይ በትክክል የሚንጸባረቅ አይደለም። እንዲህ ያለውን ጥልቅ ደስታ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ አስቸጋሪ በኾነ ኹኔታ በእስር ቤት ሳለ የተናገረው ነው። ይህን ቃል ግን ብዙዎች፣ ቅዱስ ጳውሎስ ባለፈበት መንገድ ውስጥ ኾነው ሲጠቅሱት እምብዛም አይስተዋልም።

መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ።” (ፊል. 4፥12) የሚለው ቅዱስ ጳውሎስ፣ በእነዚህ ኹኔታዎች ውስጥ ኾኖ፣ እጅግ በጌታ ስለ መደሰት ይናገራል። በርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ እኒህን ሃያላን ተግዳሮቶች፣ ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ እንደሚችል እንጂ በራሱ እንደማይችል ያምናል። እናም በክርስቶስ እንዲህ ያሉ ከፍ ያሉ ተግዳሮቶችን እኛም የማለፍ ተስፋ እንዳለን ይነግረናል።

ቅዱስ ጳውሎስ በተደጋጋሚም፣ የፊልጵስዩስ አማኞች፣ ከኹኔታዎች ይልቅ በክርስቶስ ጌታችን ላይ ተስፋ እንዲያደርጉ ያበረታታል። ይህን እያደረገ ያለው፣ እንደ አነቃቂ ተናጋሪዎች ለሌሎች አይደለም፤ በሕይወቱ ኖሮና ተፈትኖ እየኖረና እያለፈ ያለበትን እውነት በመጥቀስና፣ በራሱ ጥንካሬም ሳይኾን በክርስቶስ በመደገፍ ጭምር በመናገር። በብቸኝነት ተከብቦ፣ ወደ ሞት እየሄደ ቢኾንም፣ በክርስቶስ ላይ ያለውን ታማኝነት ፈጽሞ አልጣለም!

“ደስ ይበላችሁ” የሚለው ቃል፣ በመከራ ለተከበበና ላለ ሰው ስላቅ ይመስላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በድካማችን ብርቱ ነው! አነቃቂ ንግግሮች ወይም የራስን ቃል ማወጅ ሰውን ብርቱና ደስተኛ አያደርግም፤ ኃይልም፤ ደስታም፤ ብርታትም ከክርስቶስ ብቻ ነው! በጨለማ ቤት ለታሠረ ሐዋርያ፣ በእግር ብረት ሰውነቱ በቁስል ነፍሮ ለተተወ አገልጋይ፣ በብዙ መከራ ውስጥ እያለፈ ላለ እውነተኛ የኢየሱስ ባሪያ … ደስታና ሰላም ከክርስቶስ ዘንድ አለው! ይኸውም፦

·        አማኝ ለመጪና ሂያጁ፤ ለመውጣትና መውረዱ፤ ለከፍታና ዝቅታው … ለማናቸውም ኹኔታዎች የሚበገር አይደለም፤ ልዑሉ ክርስቶስ ኹኔታዎቻችንን ኹሉ ይቈጣጠራል፤ ደስታችን ከኹኔታዎቻችን ውስጥ የሉም፤ በክርስቶስ ኢየሱስ እንጂ!

·        ክርስቶስ እንጂ ሌላ ነገር የትኵረታችን ማዕከል ሊኾን አይገባውም፤ ክርስቶስ ዋና ትኵረታችን ከኾነ፣ ሌላውን በርሱ ኃይል ድል እንነሣለን። ከክርስቶስ ግን ትኵረታችንን በቀነስን ልክ፣ ኹኔታዎቻችን ገዝፈው ይታዩንና ሊያሸንፉን ይችላሉ።

·        በሰማይም በምድርም ክርስቶስ በቂያችን እንደ ኾነ እናስተውል፤ ክርስቶስ ካለን ኹሉም ነገር አለን! ክርስቶስን አጥተን ኹሉም ነገር ቢኖረን ግን ያለን ነገር ኹሉ፣ የትካዜና ያለ መርካት ምንጭ እንጂ “እምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና ዐሳባችንን ሊወርሰው አይችልም”!

·        ደስታችንን ከራሱ ከደስታ አምላክ፤ ከሐሴት ምንጭ፤ ከእርካታ መገኛ ከክርስቶስ እንጂ ከሌላ አንሻ፤ በዓለም ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ተወዳድሮ የሚበልጥ ደስታ ፈጽሞ የለምና!

እናም እኔም የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እደግመዋለሁ! “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:

Post a Comment