Friday 4 October 2024

“አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ማቴ. 16፥16)

Please read in PDF

ጌታችን ኢየሱስ፣ በምድርም ኾነ በሰማይ ካለ ከየትኛውም ፍጡር፣ ባህልና ልምምድ፤ ከየትኛውም የዓለም ሥርዓትና አስተዳደር ጋር አይወዳደርም! ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን በማስተዋል ነው፣ የተገለጠለትን እውነት የመሰከረው። ይህ ቅዱስ ምስክርነት፣ ክርስትና ተንጣልሎ የተመሠረተበት ሕያውና ዘላለማዊ መሠረት ነው። የቤተ ክርስቲያን ሕይወት፣ ተልእኮ፣ ታላቅ ተስፋና ዘላለማዊነት የተወሰነውና የሚጸናው፣ ይህን ታላቅ ምስክርነት በመቀበልና በማመን ብቻ ነው።

ይህን ምስክርነት የሰጠው፣ በሰማይ አምላክ በእግዚአብሔር አብ ገላጭነት ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፤ ታላቁ መጽሐፍ፣ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” እንዲል (ማቴ. 16፥17)። ያለ አብ ገላጭነት ይህን እውነት መመስከር የሚቻለው ማንም የለም።

እግዚአብሔር አብ፣ ዛሬም ስለ ልጁ ጮኸን እንድንመሰክርለት ይሻል፤ መንፈስ ቅዱስም እንኳ፣ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐ. 14፥26) ብሎ እንደ ተናገረ፣ ርሱም የሚመሰክረው ስለ ብላቴናው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።

አብም፤ መንፈስ ቅዱስም የሚመሰክሩለትን ይህን ጻድቅ ብላቴና፣ ቤተ ክርስቲያንም ትመሰክለት ዘንድ ተጠርታለች። በተለይም በቅዱስ ጴጥሮስ አንደበት፤ በአብ አባታችን ገላጭነት የተገለጠውን እውነት፣ ቤተ ክርስቲያን ድምጽዋን አሰምታ መመስከር ከተሳናትና ለዚህ እውነት ያላትን ታማኝነት ካጎደለች፣ ተልእኮዋን መፈጸም የተሳናት፤ ደካማ፤ በአቅራቢያዋ ካሉ ዓለማዊና ብሔር ተኰር ባህላት ጋር በቅይጥነት ለመኖር የምትጎመጅ ልትኾን ትችላለች።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሕያው ምስክር ናት፤ ለመሲሑና ለሥራዎቹ፤ ላዘዛትም ተልእኮው በትክክል ካልታዘዘች፣ ፍጻሜዋ አስፈሪና  የተጠራችለትን ሕያው ምስክርነት በዓለሙ ፊት የምትጥል ተላላ ያደርጋታል። በተለይም ልክ በአገራችን እየተመለከትን እንዳለነው፣ ለባህል እምነቶችና ለፖለቲካ እሴቶች “እጅ ሰጥታ” ወደ መማረክ ከሄደች፣ ጨለማውን ታበረታለች፤ አልጫውንም ይበልጥ አልጫ ታደርገዋለች።

ቅዱስ ጴጥሮስ ከመሰከረው ውጭ ያለው የትኛውም አስተምኅሮ ወይም ቅዱስ ጴጥሮስ የመሰከረውን እውነት የማይመሰክር የትኛውም ባህለ ትምህርት፣ የገሃነም ደጅ ነው። ጌታችን ኢየሱ ደግሞ እንዲህ ብሎአል፤ “በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”። ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ለኢየሱስ ቃሎች ከታመነች፣ “የገሃነም ደጆች” በማይችሉት መንፈሳዊ ትጥቅ ተውባ፣ በልዩነት ብቻዋን መቆም ትችላለች።

ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል ምስክርነት ደፋር መኾን መቻል አለባት፤ ይህን ድፍረት ደግሞ የምታገኘው፣ እውነትን በሚገፋው፤ ነገር ግን እውነት አጥብቆ በሚያስፈልገው ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ብቻ ወክላ የቆመች እንደ ኾን ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት ከየትኛውም ባህላዊ ትምህርትና ልምምድ ይበልጣል፤ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ በገለጠው ሕያው እውነት ላይ ጸንታ በመቆም፣ በምድራችን ባሉ ባህሎችና ልምምዶቻቸው ፊት በድፍረት የወንጌልን ኃይል ልትገልጥ፣ ይህን በማድረግ ውስጥ የሚያስፈሩ የሚመስሉትን “የገሃነምን ደጆች” ኹሉ ሳትፈራ ልትቆም ይገባታል። 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ ለወንጌልህ ታማኞች አድርገን፤ ለእውነትህ በፍጹም መገዛትን ስጠን፤ መንግሥትህን ያለፍርሃት እንመሰክር ዘንድ ድፍረትን እንደ ሐዋርያት ስጠን፤ አሜን!

No comments:

Post a Comment