Sunday 29 September 2024

ኢየሱስ “ከሃይማኖተኝነት” ይበልጣል!

"... ወደ የትኛውም ሃይማኖት ዛሬ ተነስታችኹ ለመግባት ትችላላችሁ። ጴንጤ ለመኾን ግን መመረጥ ያስፈልጋል" (በጋሻው ደሳለኝ)

“ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” (ኢየሱስ ክርስቶስ - ዮሐ. 10፥16)

ክርስትና የቆመው በእግዚአብሔር ቸርነትና ዘላለማዊ በኾነው ሰውን መውደድ (ቲቶ 3፥4)፣ አድልዎ በሌለበት ፍጹም ምርጫው፣ ኹሉን ወደ ጽድቅ ለማምጣት በሚወቅሰው በመንፈስ ቅዱስ ወቀሳ፣ የሰዎች ወቀሳውን መቀበልና አምኖ በጽድቅ መመላለስ፣ ወደ አካሉ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መጨመር … ላይ ነው።

“እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ … ”

እንዲል፣ ታላቁና ልከኛው ሐዋርያ (ቲቶ 3፥3-5)፤ ይህን ያደረገው ደግሞ በእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እናም፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ጴንጤያዊ ሃይማኖት የክርስትና ውኃ ልክ አይኾንም።

እናም እኔ ግን እላለኹ፦ በክርስቶስ ኾነው ጴንጤ ያልኾኑ ሚሊዮናት አሉና፣ ተመርጦ የሚገኘው ወይም አብ መርጦ የሚመርጠውና የሚወድደው በክርስቶስ የኾኑትን ኹሉ ነውና እባካችሁ "ጴንጤነትን" አታምልኩ! አታስመልኩ!

ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፣

“ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።” (ኤፌ. 1፥4)

“እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።” (ዮሐ. 15፥16)

በርግጥ በጋሻው እኒህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ቢጠቅሳቸውም፣ ያለ ዐውዳቸው “ለጴንጤ” ብቻ መጥቀሱ እንዴት ያሳዝናልም፤ ያስደንቃልም! በትክክል ባንተረጕም፣ ምናለ በትክክል ብናነብብ? በትክክል ከማይተረጕም ሰባኪ እኮ፣ በትክክል የሚያነብብ አማኝ እጅግ የተሻለ ነው!

እኔ እንዲያውም ፍርሃት አለኝ፣ ጴንጤው ማኅበረ ሰብ ከጥቂት ቅሪት በሚያስብል ትሩፋን በቀር እየኾነ ያለውን "የውድቀት ግስጋሴ" ካየን፣ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት የነበረውን የአገልግሎት ጥራትና የቅድስና ጌጥ እየተጣለ "ለቀረጥ ሰብሳቢና ለሸቃጭ ነቢያት" የተገዛውን ትውልድ ብዛት ከተመለከትን … እውን ጴንጤ መኾን መታደል ነው ወይ? የሚያስብል አሰቃቂ ጥያቄ ያጭራል። አገልጋይ ነን የሚሉት፣ እንደ በጋሻው ባሉ ንግግሮች ሲረኩ ሳይ ያሳዝኑኛል!

እንዲኽ ያለ ትምክህት ይመስለኛል ኦርቶዶክስን እዚኹ ምድር ላይ አቀጭጮ ያስቀረው። ኢትዮጵያ የአሥራት አገር፣ የክርስቲያን ደሴት፣ ኢየሱስና እናቱ በኪደተ እግራቸው የባረኳት፣ የተመረጠች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስሟ ተደጋጋሚ የተጠቀሰ ... በሚል አጉል ኩራትና ንቀት ተሞልታ ወንጌልን ለመላው አፍሪካና ለዓለሙ ከማድረስ ያቀባት።

ክርስቶስ ጌታችን ሆይ፤ በአንደበት ከተገለጠ ኩራት፤ በልብ ከተሠወረ ንቀት ጠብቀን፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment