Saturday, 14 September 2024

ዘነበ ወላ(ጋሽ)ና ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ!

Please read in PDF

ዘነበ ወላ፣ ሰሞኑን ሥራና ምናኔን አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት በብዙ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ጥርስ አስነክሶበታል። ብዙ ኦርቶዶክሳውያን የሰላ ትችት ሲሰነዘርባቸው፣ ችግሮቻቸውንና ስህተቶቻቸውን ከማረቅ ይልቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማዋረድ የሚነገር አድርጎ ማሰብ፣ “ልጅ እናቷን ምጥ አታስተምርም” የሚል አጉል ፈሊጥ መጥቀስ፣ ዛሬ መጥታችኹ ቤተ ክርስቲያንን ወንጌል ልትሰብኳት፣ ችግሯን ልታመለክቱ አትችሉም … የሚሉ አያሌ አሉታዊ ምላሾች ይቀርባሉ። ይህን ስንል ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዋረድ የሚሠሩ የሉም ማለት አልችልም። ይኹንና ደግመን ደጋግመን መናገር የምንፈልገው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ እውነተኛ የወንጌል ጐዳና እስክትመለስና በመካከልዋ ያለውን “ዕድፍና ጉድፍ” እስክታስወግድ ድረስ “የተሐድሶ ድምጽ” ማሰማታችንን አናቆምም!

በርግጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን በመላው ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ የሥራ ባህል እጅግ በጣም ደካማ ነው። እንዲያው የእኛን አገር የሥራ ባህል በሚገባ ያስተዋሉት ከንቲባ ገብሩ ደስታ እንዲህ ገልጠዋል፤

“ኢየሩሳሌም ትምህርት ቤት እንደ ገባሁ ሰሞን ከተማሪዎች ጋር የደረቀ ፍግ በአካፋ እየዛቅን በሚገፋ ጋሪ ወደየአትክልቱ እንድናፈስስ ታዘዝን። ተማሪዎቹ የለመዱት ሥራ ስለ ነበር እየተዝናኑ እየተጫወቱ ይሠራሉ። የክፍል አለቃዬ መጣና ‘ጎባው አትሠራም እንዴ?' ቢለኝ ‘እኔ ፍግ ለመዛቅ አልመጣሁም ለመማር እንጂ!’ ብዬ መለስኹለት። የክፍል አለቃዬ ይህንኑ ሄዶ ለዋናው አስተዳደር ነገራቸው። እሳቸውም ‘ተዉት ግድ የለም እሱ ሥራ መሥራት ካልለመደ ሀገር ስለ ኾነ እስኪለምድ ድረስ አትንኩት’ ብለው ሲናገሩ ሰማሁ። እኔም ጥቂት ደቂቃዎች ከቆየሁ በኋላ ቆጨኝና የሚገፋውን ጋሪና አካፋዬን ይዤ እንደ ጓደኞቼ እየተሻማሁ መሥራት ጀመርሁ። ከዚያ በኋላ ሥራ ሕይወት መኾኑን ተማርሁና ኑሮዬን ማቅናት ቻልሁ።” (ከንቲባ ገብሩ ደስታ በኢየሩሳሌም ለትምህርት ሄደው የገጠማቸውን ኮሎኔል ዳዊት ገብሩ እንደ ዘገቡት)[1] 

የአገራችን የሥራ ባህል ምንም እንኳ ከመላው የአገራችን ሕዝብ ጋር የሚገናኝ ቢኾንም፣ በአላትን አስታክኮ የማይሠራው፤ በምናኔ፣ በምንኵስና፣ በፍሬ ሰሞን፣ በብህትውና ሰበብ ሥራን እርግፍ አድርጐ የተወ ኦርቶዶክሳዊ ቊጥሩ ትንሽ አይደለም። ለዚህ ኹለት ምሳሌዎችን ልጥቀስ፦

1.   የማርያምን 33 የግዝት በአላት፣ በየወሩ (12፣ 21 እና 29) ግዴታ የሚከበሩ 36 የግዝት በአላት … እያልን በጠቅላላ የዓመቱን በአላት በወራት አስልተን ብናስቀምጥ፣

“ከ12 ወራት ውስጥ 4 ወር ከ18 ቀናት የሥራ ቀናት ሲኾኑ፣ ሕዝባችን ሰባት ወር ከዐሥራ ኹለት ቀናት እጅ እግሩን አጣጥፎ ይቀመጣል ማለት ነው።”[2]

2.   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሚያገለግሉ አገልጋዮች ቀሳውስትና ዲያቆናት ቊጥራቸው በግምት ወደ ኹለት ሚሊየን ገደማ ይጠጋል፤ በገጠርና እጅግ ራቅ ወዳለው ገጠር ከሚያገለግሉት በቀር አብዛኛዎቹ በወረዳ ከተሞችና በከተሞች የሚያገለግሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት ምድብ ወጥቶላቸው በፍሬ ሰሞን ነው የሚያገለግሉት።

ለምሳሌ፦ የአዲስ አበባ አድባራትና ካቴድራሎች መነሻ መደባቸው(በፍሬ ሰሞን) አራት ነው፤ ትልቁ ደግሞ ሰባት መደብ ነው፤ ይህ ማለት አንድ ሰው በአገልግሎት ላይ ቢመደብ፣ ከአራት ሳምንት በኋላ ወይም ከሰባት ሳምንታት በኋላ ነው የሚያገለግለው ማለት ነው። በዚያ ላይ ተጋባዥ እንግዶች ከነበጀታቸው መኖራቸው ሳይዘነጋ። በአዲስ አበባ ያለ አንድ አድባር፣ ቢያንስ 15 ቀዳሽ ቀሳውስት፣ 13 ዲያቆናት፣ 16 መዘምራን ወይም መሪጌቶች፣ ከ10 የማያንሱ “ሰባኬ ወንጌል” አሉአቸው፤ ይህ አማካዩ እንጂ አንዳንድ ቦታዎች በነጠላ ብቻ እስከ 25 አገልጋዮች ያላቸው አሉ። እንግዲህ እኒህን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ደመወዝ ከመክፈል በዘለለ፣ በየትኛው ሥራ ላይ እንዳሰማራችና የሥራ ባህልን እያበረታታች እንደ ኾነ፣ ያረጋል አበጋዝ ቢያቀርብልን መልካም ነበር።

ከዚኹ ጋር በተያያዘ፣ የመናንያንንም እውነታ በዚኹ መንገድ ማስተዋል እንችላለን፤ መናንያንና መነኰሳት ያሉባቸው አብዛኛዎቹ የሰሜን ክፍሎችና ከፊል ሸዋው ገዳማቱ በዙሪያቸው ካለ ገበሬና ነዋሪ መቁነንና የከርሞ ምግብ ከመለመንና በልመና ከማሰባሰብ ባሻገር፣ ለማኅበረ ሰቡ ያላቸውን የሥራ ባህል ሲያካፍሉ አይስተዋልም። በተጨማሪም ጋብቻ በቤተ ክርስቲያቱ ውስጥ ኹለተኛ ደረጃ እንዲይዝና ምንኵስናና ምናኔ ለአገልግሎት ከፍ ያለ “ቦታ” እንዲሰጠው የተደረገው በተመሳሳይ መንገድ በተፈጠረ ስህተት ይመስለኛል።

ዛሬም ድረስ የእኛ አገር የሥራ ባህል ደካማ ስለ መኾኑ ያፈጠጠ፤ ያገጠጠ እውነታ ነው። ያረጋል አበጋዝ፣ ይህን እውነት ወደ ጎን በመተው፣ እጅግ በሚያስደንቅና በሚያስቅ መንገድ፤ ምናኔንና በመናንያን ዘንድ ያለውን የሥራ ባህል ለማስረዳት ተሻግሮ ወደ አውሮፓ መሄዱ ነው። እንዲህ ይላል ለዘነበ ወላ በመለሰው መልሱ፣

“በአውሮፓ የውኃ ኃይልን ለወፍጮና ለቆዳ ሥራ መጠቀምንና ማዕድናትን ማውጣትንና መጠቀምን በስፋት ያስተዋወቁት ገዳማውያን ናቸው። የአውሮፓን የእርሻ መሬት፣ ሥነ ጥበብና እውቀት ከጥፋት በመጠበቅና በማበልጸግ ረገድ ገዳማት የተጫወቱት ሚና ምትክ አልባ ነው። … በዚህ መንገድ ሥልጣኔ በመላው አውሮፓ እንዲስፋፋ የራሳቸውን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል።”

ይላል። 

ያረጋል አበጋዝ፣ አውሮፓ ሳይሄድ እንዲህ ያለ ምሳሌነት ያላቸው መናንያንና መነኮሳት በኢትዮጵያ ምድር ነበሩ፤ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን።

1.     እስጢፋኖሳውያን በወንጌል የበረቱ ነበሩ፣ ለጳጳሱ አባ በርተሎሜዎስም ከብሉይና ከሐዲስ ቅዱሳት መጻሕፍት አስማምተው መመሥከራቸውንና በአደባባይ ማሰማታቸውን በታሪክ ተዘግቦአል።[3] ከዚያ ባሻገር ዋና ሥራቸውም ወንጌል መመስከር፣ ጸሎትና ሥራ ነበር።

2.     ከአውሮፓ አስቀድሞ ሥልጣኔውን ያመጡት እኒኹ መነኮሳት መኾናቸውንና በሥራው ትጉሃን የነበሩ መኾናቸውን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ትዝብታቸውን አስቀምጠዋል፤

“ከሰዎች በፊት ከሥልጣኔ በራፍ ላይ ደርሰን ከኋላችን የመጡ አልፈውን በአዳራሹ ሲገቡ፣ እኛ አኹንም ከውጭ ቆመን መቅረታችንና በልመና የምንኖር መኾናችን የገዢዎቻችን የዐፈና ተግባር የማይቀር ውጤት ኾኖ ነው። በታሪካችን ኹሌም በሕገ አራዊት እየተመራን፣ የሰውነት ሐብታችንን፣ አዕምሮአችንና መንፈሳችንን ታፍነን ኑሮአችንን የምናሻሽልበት ዘዴ ለመፍጠር አልቻልንም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ መንፈሳዊ ወኔ የነበራቸውና ሐሳባቸውንና እምነታቸውን ማንንም ሳይፈሩ በአደባባይ ለማውጣት የቻሉ እንደነደቂቀ እስጢፋኖስ የመሳሰሉ መገኘታቸው ከአፈናው ባሻገር ጭራሽ ባዶ አለመሆናችንን ያሳየናል”[4]

ያረጋል አበጋዝ፣ ይህን እውነትና ምስክርነት መቀበል አይሻም፤ ምክንያቱም እስጢፋኖሳውያን ለርሱና ለማኅበረ ቅዱሳን መናፍቃን ናቸውና። ምናኔ ወይም በገዳም መወሰን ከሐዋርያዊ ተልእኮና ጌታ፣ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” (ማቴ. 28፥19-20) ብሎ ካዘዘው ከተፋታ፣ ከንቱ ትምክህት እንጂ እውነታ የለውም! እንዲያውም ከምናኔና ምንኩስና ጋር ተያይዞ በገዳማት ዙሪያ ያሉትን የነውር ሐሜቶችን ቢያስወግዱና ገዳማት በትክክል የጽሙና ማዕከላትና ከዚያም የሐዋርያዊ ተልእኮ ማሰማሪያ ቢኾኑ ምንኛ በወደድን ነበር!

እንደነ ፓትርያርክ አባ ማትያስና ያረጋል አበጋዝ በጽሑፉ እንደ ጠቀሳቸው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ “የአባቶች አለቆች” ከፍ ያለ የተሐድሶና የእንታደስ ድምጽ ሲያሰሙ፣ “አንታደስም፤ እንዲኹ ብንቀር ይሻለናል” የሚሉ ሰዎች በነያረጋል ተርታ ያሉ ናቸው። አንዳንዶች እንደውም ላለመመለስና በዚያው “በእርጅናና በብልየት” መንገድ ለመጽናት፣ “ነገረ በትን፤ መስተባርር” አለን ብለው ሲገበዙ እንሰማቸዋለን፤ እኛ ግን እንላለን፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚበጃት ወደ ወንጌልና ወደ እውነተኛው ስቁል መሲሕ መመለስ ብቻ ነው!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።



[1] ከንቲባ ገብሩ ደስታ የኢትዮጲያ ቅርስ፤ 1985 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፣ ቦሌ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ 22

 

[2]ብሩክ ገብረ ሊባኖስ ተስፋዬ፤ የሰው ያለህ፤ 2013 ዓ.ም፤ ሜልቦርን አውስተራሊያ፤ ገጽ 185

[3] ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር)፤ በሕግ አምላክ፤ 2002 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አአዩ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 71

[4] ዝኒ ከማኹ

1 comment: