አንድ የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባባል አለ፤ “በምድር ላይ ፍጽምት ቤተ ክርስቲያን የለችም፤ ምናልባት ካለች፣ አንተ የገባህባት ቀን ፍጽምናዋን ታጣለች” ይላል። ሙሉ ለሙሉ ባልተዋጀው ዓለም ስንመላለስ ፈተናና ውጊያ፤ መሰናክልና ወጥመድ፣ መከራና ተግዳሮት አለብን፤ ጌታችን ኢየሱስ ራሱ፣ “እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤” (ማቴ. 10፥16) ብሎ ተናገረን እንጂ፣ ወደ ሰላማውያንና ፍጹማን አማኞች ወይም ማኅበረ ሰቦች ዘንድ እልካችኋለሁ አላለንም። እናም ውጊያችን ፈርጀ ብዙና በዚህች ምድር ላይ እስካለንም ድረስ የማያቋርጥም ነው።
ጌታ እንዲህ ወዳለ
ሕዝብና ትውልድ የላከን፣ “በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ኾነን፤ … በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር
ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ የተመላለስን”፣ ደካሞች፣ ኃጢአተኞች፣ ጠላቶች፣ እጅግ ዓመጸኞች፤ (ኤፌ. 2፥1፤ ሮሜ 5፥7፤
2ጴጥ. 1፥12) የነበርነውን ሲኾን፣ እግዚአብሔር እንዲህ ያለነውን እኛን የመምረጡ መንገድ፣ የሞኝነት፣ የድካም፣ የተናቀና ያልኾነ
መንገድ ተብሎ ተጠቅሶአል፤ (1ቆሮ. 1፥27-28)።
ክፉ ከሆነ ከአሁኑ
ዓለም ያዳነን ጌታ (ገላ. 1፥4)፣ ዋጅቶና ቀድሶ የሚልከን ወደዚያው ክፉ ዓለም ነው፤ የመሲሑ ፈቃድ ከክፉ እንድንጠበቅ እንጂ
ከዓለሙ እንድንወጣ አልተባለልንምና (ዮሐ. 17፥15)፤ ከዓለሙ የማንወጣው ለተልዕኮ ነው፤ ተልዕኮውም ጨውና ብርሃን (ማቴ. 5፥13-16)
መኾንን አጥብቆ የሚሻ እንጂ፣ መመሳሰል ወይም ግብዝነትን አይሻም።
አዎን፤ የእግዚአብሔርን
ክብር ያጎደልን እጅግ ኃጢአተኞች እንደ ነበርን አንክድም፤ ነገር ግን በኃጢአት አንጸናም፤ እንሳሳታለን ነገር ግን ስህተታችንን
ተናዝዘን እንተወዋለን እንጂ፣ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ብለን በስህተታችን ሙጥኝ፤ ጥብቅ፤ ሙጭጭ አንልም! ውድቀታችንን በምድር ሸንጎ
ለማጸደቅ በብዙ አንጥርም!
ዛሬስ
ዛሬ አንድና ፍጹም
ነገር እናውቃለን፤ ኢየሱስ እንዳዳነን፤ እንደሚያድነን፤ ፍጹምም ደግሞ እንደሚያድነን። መጽሐፍ፣ “ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር
ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።”
(1ዮሐ. 3፥2) እንደሚል፣ አኹን እርግጠኞች የኾንንበት እውነት አለ፤ እግዚአብሔር እንዲያው ልጆቹ አድርጎናል፤ እኛም እርሱ ከሰጠን
እምነት የተነሣ አምነን ተቀብለናል። ነገ የጌታ ብድራት እንዳለን እንጂ በከንቱ አንመላለስም።
ይህን ስንል፣
አንፈተንም፣ አንዝልም፤ አንታክትም፣ አናዝንም፣ አንሳሳትም አላልንም፤ አዎን፤ በድንግዝግዝ የምንኾንበት፣ በድካም የምናልፍበት፤
የምንሳሳትበት … ጊዜ አለ፤ ነገር ግን ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ እንደወደቅን እንዳንቀር የማይሻ፣ የጻድቅ ጌታን ምሕረትና ቸርነት
ታምነን እንነሣለን፤ እንቆማለንም።
ታድያ ምን እናድርግ?
ዛሬ የእግዚአብሔር
ልጆች ነን፤ ይህን ማመናችን በቂያችን ነው፤ ይህንም ንቀን፣ ፈጽሞ ወደ ተውነው ቤትና የፍጡራንን መካከለኝነት ወደ ሰበክንበት ኅብረት
መመለስን አናስብም። ወደኋላ መመለስንም፣ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን ድካም አንቆጥርም። አዎን፤ ክርስቶስ ቤዛ የኾነላትና ይህን
ብቻ ያመነች ቤተ ክርስቲያን ትዝላለች፣ ትደክማለች ማለት፣ ዝለት፣ ድካም፤ አምልኮ መቀላቀል፣ ወንጌል መበረዝ፣ አማኞችን ከክርስቶስ
ውጭ ባሉ ሌሎች የተሸቀጡ ትምህርቶችና አምልኮአዊ ልምምዶች በአደባባይ በማወጅና እንደ አንድ አስተምህሮ በመቀበል አይደለም።
ደግሜ እላለሁ፤
ድካም አለብን የምንለው፣ ሙሉ ለሙሉ ባልተዋጀው ዓለም እንደሚመላለስ ሰው እንጂ፣ ወደ ኋላ ለመመለስ፣ አምልኮ ለመቀላቀል፣ ክፉ
ምሳሌ ለመኾን፣ አምልኮተ ማርያምና አምልኮተ ቊሳትን ለማስረጽና እንደ ገና ሕይወት እንዲዘራ ባለ ነውር ውስጥ ለመመላለስ አይደለም!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ
ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)
GOD bless you for sharing Abiny. May the LORD be your guide until your last breath.
ReplyDelete