Wednesday, 20 October 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲፬)

 Please read in PDF

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ስለ ነገረ ድኅነት ያን ያህል ሰፊ ጽሑፍ ሲጽፍ፣ አንድም ቦታ ከውኃ ጥምቀት በስተቀር ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አለመጻፉ፣ ምን ያህል ከመንፈስ ቅዱስ እውነት፣ ከኢየሱስ ትምህርትና ሕይወት መራቁን፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ኃይል ባለማወቅ እንዴት እንደ ሳተ እንመለከታለን።



መጽሐፍ ቅዱስ ግን፣ በግልጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በሚገባ ያስተምራል፤ ደግሞም ከነገረ ድኅነት ጋር ተያያዥና ቊልፍ ትምህርት መኾኑን በሚገባ እናስተውላለን። የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መመልከት እውነታውን እንድናስተውል ይረዳናል።

እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤” (ማቴ. 3፥11)

ዮሐንስ መልሶ፦ እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤” (ዮሐ. 3፥16)

ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። (ዮሐ. 3፥5)

“አንዲት ጥምቀት” (ኤፌ. 4፥5)

እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤” (ቲቶ 3፥5)

እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ[ክርስቶስ] ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።” (ማር. 1፥8)

ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” (ሐ.ሥ. 1፥5)።

“በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤” (ኤፌ. 1፥13)

እኒህና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በግልጥ ያስተምራሉ፤ ይመሰክራሉ።

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምንድር ነው?

በአዲስ ኪዳን፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጥና በአደባባይ ያስተማረው፣ መጥምቁ ዮሐንስ ነው። እርሱም ከውኃ ጥምቀት ጋር አንድ ያልኾነና ከውኃ ጥምቀት የተለየ መኾኑን፣ የራሱንና የኢየሱስን ጥምቀት መሠረታዊ ልዩነት ባለው መንገድ በማነጻጸር በግልጥ ተናግሮአል።

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማለት፣ አንድ አማኝ ክርስቶስን ሲያምን መንፈስ ቅዱስ አማኙን ወደ ክርስቶስ ኅብረት ወይም አካል ውስጥ የሚጨምርበት እጅግ ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” (ሮሜ 6፥3) ብሎ በመናገሩ፣ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ የምንኾንበት ምስጢር የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መኾኑን ተናገረ።

አንድ ሰው ከአባቱ በመወለዱ የአባቱን ጠባይና ኹኔታ እንደሚወርስ እንዲሁ፣ አንድም አማኝ በክርስቶስ ጌትነትና አዳኝነት በማመኑ የክርስቶስን ጠባይና የጽድቅ ሕይወቱን በመውረስ እርሱን ይመስላል።

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሚኾነው አማኙ በውኃ በመጠመቁ ብቻ ሳይኾን፣ መንፈስ ቅዱስ፣ አማኙ ክርስቶስን ባመነበት እምነቱ የክርስቶስ አካል ውስጥ ሲጨምረው የሚከናወን ነው። ይህም በሌላ ስፍራ፦  እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።” ተብሎ በመጽሐፍ ተጠቅሶአል፤ ከዚህም የተነሣ በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ክንውን አማኙ ኢየሱስን ባመነ ጊዜ የሚፈጸም ነው፤ (1ቆሮ. 12፥13)።

የውኃ ጥምቀት

መጽሐፍ ቅዱስ ውኃን በተመለከተ አያሌ ትርጕሞች አሉት፤ ለምሳሌ፦ ቅዱስ ቃሉን (ኢሳ. 55፥1)፣ መንፈስ ቅዱስን (ዮሐ. 7፥39)፣ የልብ ከኃጢአት የመንጻት ምሳሌ (ሕዝ. 16፥4፡ 9፤ 36፥25፤ ዮሐ. 3፥5)፣ የእግዚአብሔር በረከት (መዝ. 23፥2፤ ኢሳ. 35፥6-7፤ ሕዝ. 47፥1-12፤ ዮሐ. 4፥14፤ ራእ. 22፥1)፣ ፍርድንና አደጋን (መዝ. 18፥16፤ 32፥6፤ 69፥1) ሊያመለክት ይችላል፡፡[1]

ስለዚህም በውኃ ስለ መጠመቅ  የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳቦችን ኹሉ ወስዶ፣ በውኃ መጠመቅ ብቻ ብሎ መወሰን ለመላው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አለመገዛት ነው፡፡ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ የሚተረጐመው በመጽሐፍ ቅዱስ ከኾነ፣ አንዱን ዐሳብ ከሌላው ጋር ማስታረቅ ግድ ይለናል፡፡ እናም በውኃ ጥምቀት ብቻ የዘላለም ድኅነት ይገኛል ብሎ ማመን፣ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት መካድና አለማወቅ ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ማን ያጠምቃል?

ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት የሚያጠምቀው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ኾነ ያስተምረናል፤ (ማቴ. 3፥6፤ ማር. 1፥8)።[2]

ይቀጥላል  

5 comments:

  1. GOD bless you for sharing Abiny. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come, till your last breath.

    ReplyDelete
  2. tebarek Wendemachen, may God bless you more!!!!

    ReplyDelete
  3. በእውነት የገባህ ነህ በቃ እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ ግን አጨብጭቤአለሁ ለአንተ

    ReplyDelete
  4. ስላንተ፡ስጦታ፡እግዚአብሔር፡ይክበር፣እድሜ፡ይስጥልን።

    ReplyDelete