Friday, 29 October 2021

በአንድ ቀን የወደቀ የለም!

Please read in PDF

ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። (መዝ. 19፥12)

ሔዋን ከእባብ ጋር በማይጠቅምና በማያንጽ ወሬ መዘግየቷ ዋጋ አስከፍሎአታል (ዘፍ. 3፥1-6)፤ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳዖል ውድቀቱ የጀመረው፣ ትንሽ ከምትመስል ነገር ግን አደገኛ ከኾነ ክፉ የባልንጀርነት ቡድን ውስጥ መሳተፉ ነው (1ሳሙ. 14፥2-3)፤ ጅማሮው መልካም የነበረው ያ ንጉሥ በፍጻሜው፣ ጠንቋይ እንደ ፈለገ፣ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዘ ክፉ ሞት ሞተ፡፡ ሳምሶንን የሚያህል ብርቱ አገልጋይ፣ የመውደቁና የመንኮታኮቱ ጅማሮ፣ ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ። (መሣ. 13፥1) ከምትል ቀላል ሐረግ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ፣ ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። (1ቆሮ. 15፥32) ከሚሉ ሰዎች ጋር መዋል፣ በፍጻሜው የክርስትና ዋና ማዕከልና ተስፋ የኾነውን የትንሣኤ ሙታንን ትምህርት ሊያስክድ እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ እንዲህ አለ፤ አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። (1ቆሮ. 15፥33)፡፡ ስለ መብል፣ ስለ መጠጥ፣ ስለ ዝሙት፣ ስለ ጥላቻ፣ ስለ ፖለቲካ፣ ወንጌልን ከመከራ ጋር ከመመስከር ይልቅ ተደላድሎ ስለ መስበክ ከሚያወሩ ሰዎች ጋር መዋል ፍጻሜው መልካሙ አመላችንን ማጥፋቱ የማታበል ሃቅ ነው፡፡

የትኛውም ብርቱ አማኝ(አገልጋይ)፣ በአንድ ቀን እንዳልተጠራና እንዳልጸና[እግዚአብሔር ተፈጥሮን አይክድምና] እንዲሁ፣ በአንድ ቀን አይወድቅም፤ አይንኮታኮትም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ከመጥራቱ በፊት አስቀድሞ፣ ወደ ከተሞቻቸው ሄዶ ተአምር አድርጎአል፤ ወደ መንደሮቻቸው ሄዶ አስተምሮአል፤ ወደ ሥራ ቦታቸውም ሄዶ ጉብኝት አድርጎአል፤ ሥራውንና ሕይወቱን፤ ትምህርቱንም ጭምር እንዲመለከቱ ደጋግሞ ጋብዞአቸዋል (ዮሐ. 1፥35-51)፡፡ ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ እያንዳንዱን ደቀ መዝሙር፣ ተከተለኝ ብሎ ሲናገረው፣ ምላሹ ፍጹምና አዎንታዊ ነበር፡፡

ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ አማኞች(አገልጋዮች) የሚወድቁበትን መንገድ ስናስተውል፣ በአንድ ቀን ወይም ወዲያው ሲወድቁ አናስተውልም፡፡ በአንድ ቀን ማንም ሊወድቅ አይችልምና፡፡ ዛሬ ላይ ከወንጌል አገልጋይነት ወደ ኋላ የተመለሱ ወይም ለመመለስ እየተዘጋጁ ያሉ ወገኖች፣ መመለስ የጀመሩት ወይም ምልክቱን ማሳየት የጀመሩት ዛሬ አይደለም፡፡ ቀኑ ሩቅ ጊዜውም ከረጅም ጊዜ በፊት ነው፡፡ ዛሬ ያየነው ፍሬው ጎምርቶ፤ ዐሳባቸው ተሳክቶ ነው፡፡ የጀመረው ግን ከትንሽዬና ይኾናል ተብሎ ሊገመት ከማይችል ስፍራ ነው፡፡

የተወደዳችሁ አማኞች(አገልጋዮች) ሆይ፤ ከማን ጋር ነው የምትዘገዩት? የትስ ነው ረጅሙን ጊዜአችሁን የምታሳልፉት? ስለ ምንስ እያወራችሁ ነው የምትቆዩት? ምንስ ረጅሙን ጊዜአችሁን ይወስድባችኋል? ውሎአችሁንና ንግግራችሁን፣ ከማን ጋር እንደምታሳልፉም ለዩ፤ ኢየሱስ ከማይከብርበትና እናንተ ከማትታነጹበት፤ ሌሎችንም ከማታንጹበት ስፍራ ራቁ፤ ተጠንቀቁም፤ ጠላት ሁል ጊዜ በዙሪያችሁ ሊያደባ፣ ስህተትም በጽድቅ መዝገባችሁ ውስጥ ተሸሽጎ ራሱን ሊደብቅ ይችላልና እንግዲህ ንቁ!

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌ. 6፥24)

 

4 comments:

  1. GOD bless you for sharing Abiny. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come, till your last breath.

    ReplyDelete
  2. God bless u brother u have all good teaching

    ReplyDelete
  3. የማይጠገብ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቃል!

    ReplyDelete