Please read in PDF
3.ሌላው አጽናኝ ወደ እኛ ይመጣ ዘንድ፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መስቀል
ነፍሱን ስለ ሰው ልጆች አሳልፎ ሊሰጥ እጅግ በቀረበበት ሰዓት፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ማዘን ጀምረው ነበር፤ ተላልፎ እስከ
ተሰጠባትና መስቀል ላይ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ መከራው በሙሉ ያነጣጠረው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው። ነቀፌታውም፣
ስድቡም፣ ትችቱም፣ ጥላቻውም፣ መገለሉም፣ መሰደዱም፣ በመጨረሻም በመስቀል ከባድ መከራንም የተቀበለው ጌታችን ኢየሱስ ነው።
ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን መከራው እነርሱንም እንደ ሚያገኛቸው አስቀድሞ አልነገራቸውም፤ ምክንያቱም በእርሱ ሕይወት ሲያልፍና
ሲኾን የነበረውን ኹሉ ሲመለከቱ ነበርና። ከንግግር ይልቅ ሕይወት የማስተማር አቅሙ እጅግ ታላቅ ነውና!
ነገር ግን ወደ ሰማያት ወደ አባቱ ሊሄድ ሰዓቲቱ
እንደ ደረሰች ሲያውቅ፣ “እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ
እግዚአብሔርን እንደ ሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል።” (ዮሐ.16፥1-2) በማለት፣ መከራው ለእነርሱም እንደ ማይቀር
ነገራቸው። በጌታችን ኢየሱስ ላይ የወረደው የዓለሙ ኹሉ ጥላቻ በእነርሱም ይፈስሳል፤ የተገለጠ ንቀትም ፊት ለፊት ያገኛቸዋል፤
በዓለሙ ኹሉ ፊት እንደ ጉድፍ ይቆጠራሉ፤ ጌታቸው ባለፈባት የምጥ መንገድ እነርሱም ያልፉ ዘንድ አይቀርላቸውም። የመከራው ጫፍ
ሰዎች እነርሱን ሲጠሉ፣ ሲያሳድዱ፣ ሲገድሉ … ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን የማቅረብ ያህል በጭካኔ ያደርጉባቸዋል። በዛሬ ዘመን
ምን እየኾነ ይኾን? ሰዎች የእግዚአብሔር ሰዎች ነን እያሉ፣ በሃይማኖት ሽፋን ሰዎችን ለምን ይገድላሉ? ይጠላሉ? ያሳድዳሉ?
የሰዎችን ስምስ በመረረ ጥላቻ ለምን ያጠፋሉ? …።
ነገር ግን መደናገጥና መሰናከል
አይገባም። ደቀ መዛሙርቱንም ኾነ እኛን የሚኾንብንና የሚያገኘን ኹሉ በክበበና በምክረ ሥላሴ አስቀድሞ የተወሰነ ነው።
የሚገጥመን መከራና ሕማም ኹሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይታወቅ አይደለም። አጋጣሚ ወይም ዕጣ ፈንታም አይደለም፤ ፈጽሞ “የአርባ
ወይም የሰማንያ ቀን” ዕድልም አይደለም። መከራው የምስክርነት ውጤት፣ ጌጥ፣ መሠሪያ፣ መታነጺያ፣ መንጫና መጥሪያ፣ መገረዢያ፣
መስተካከያ መኾኑን እንጂ ከእግዚአብሔር ስለተተውን የሚያገኘን አይደለም። በጌታችን ኢየሱስ ስም ካመንን ቀጣዩ ጽዋችን መከራውን
አብረን መካፈል ነው፤ “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ
አይደለም፤” እንዲል፤ (ፊል.1፥29)።
መከራው የማይቀርልን እውነት ነው፤ ነገር ግን መከራውን ኹሉ
የምናልፍበት አቅም፣ ችሎታ፣ ጉልበት፣ ኃይል … እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። መከራው ለጊዜው ጥቂት ነገራችንን
ይነካው፣ ያምመን፣ ስሜታችንን ይሰብረው ይኾናል፤ ነገር ግን “ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ
መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።” (1ቆሮ.4፥17-18)፤ ይህን ዘላለማዊ
የማይሻር እውነት ከልባችንና ከሕይወታችን አድምቆ የሚጽፈው አጽናኙ ጰራቅሊጦስ ነው፤ (ዮሐ.14፥15፤ 26፤ 15፥26)።
አጽናኙ በሕይወታችን ይህን
ሊያደርግ ግን ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት ማረግና መሄድ አለበት። ጌታችን ኢየሱስ ካላረገና ካልሄደ በቀር ፈጽሞ መንፈስ
ቅዱስ፤ ሌላው አጽናኝ ወደ እኛ አይመጣም፤ “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ
ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” (ዮሐ.16፥7) እንዲል፣ በአንድ ጊዜ በመላው ዓለም
በመገኘት አማኞችንና አገልጋዮችን ኹሉ፣ ይመራል፣ የክርስቶስን ትምህርት ኹሉ ያስታውሳቸዋል።
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት
ማረግ፣ የመንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ መምጣት ዋና ምክንያት ነው። የእርሱ ወደ አባቱ ክብር መግባት ለቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን
እጅግ መቅረቡን ማብሠሪያ እውነት ነው። ደቀ መዛሙርቱ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሄዱ ጥቅማቸው፣ ማረጉ ዘላለማዊ ክብራቸው
እንደ ኾነ አሁን አያስተውሉም። እናም አጽናኙን በልባቸው፤ በኹለንተናቸውም ለማክበርና እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስን በልባችን
እንዲያከብረው የእርሱ ወደ እነርሱ መምጣት እጅግ አስፈላጊ እንደ ኾነ በማመን፣ ክርስቶስን የሚያከብሩትና የሚያመልኩት አኹን
አይደለም፤ አኹን የሚያደርገውንም ነገር በትክክል አያስተውሉም፤ ነገር ግን በሄደ ጊዜና መንፈስ ቅዱስ በመጣ ጊዜ ኹሉን
ያስታውሳሉ።
ክርስቶስን ለመመስከር የመንፈስ ቅዱስ
መሞላት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ያለ መንፈስ ቅዱስ መሞላት ክርስቶስን መመስከር እጅግ ከባድ ነው። መንፈስ ቅዱስን ተቀብያለኹ
የሚሉ ነገር ግን ክርስቶስን የማይመሰክሩ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ፤ አንድ ሰው በመንፈስ በመቃጠልና በትክክል ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስን የማይመሰክር ከኾነ መንፈስ ቅዱስን አልተቀበለም ብለን ደፍረን መናገር እንችላለን። ምክንያቱም ሰይጣን የሚያፍርበትና
ድል የሚነሣበት ስም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ነውና።
ደግሞም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም
መከራን መቀበል ትልቅ መታደልና ልዩ ሥጦታ ነው። በስሙ በሚያገኘን መከራም ፊታችን ለቅጽበት እንኳ መጥቆር የለበትም፤ ይልቁን
“ስለ ስሙ እንናቅ ዘንድ የተገባን ኾነን ስለ ተቈጠርን በሸንጐው፣ በሚያሳድዱንና በሚጠሉን ፊት ደስ ሊለን” ይገባል፤
(ሐዋ.5፥41)፣ “ዋጋችን በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበለን፥ ሐሴትም እናድርግ፤ ከእኛ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ
አሳድደዋቸዋልና፤” (ማቴ.5፥12)። የታመነውን ስም በሐሰተኛውና የሐሰት አባት በኾነው ሰይጣን ፊትና በከሃዲው ዓለም ፊት
ስንናገረው ማንስ በበራ ፊት ሊቀበለን!?
አዎን! በመከራችን ኹሉ የማናፍረውና የማንፈራው
መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ነው፤ ዛሬ በክርስቶስ የምናፍረው መንፈስ ቅዱስን ስላልተሞላን ነው፤ ብዙዎችም ክርስቶስ ሲሰበክ ከመደሰት
ይልቅ “ቅዱሳን ተረሱ” በሚል ኢ መንፈስ ቅዱሳዊ ቅንአት ውስጥ የሚገቡት፣ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ምን እንደ ሚሠራ ስላላስተዋሉ
ወይም ማስተዋል ስላልወደዱ ነው። “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም
የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል፤” (ዮሐ.14፥26) እንዲል፣ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ የጌታችንን ኢየሱስ ትምህርቶች፣ የቃሉንና
የሥራዎቹን ትርጉም ኹሉ አብራርቶላቸዋል፤ ለልባቸውም አስታውሷቸዋል። ለእኛም እንዲኹ ያደርጋል። ክብር ይኹንለት፤ አሜን።
መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ የሚነግረን ያንኑ
የጌታችን ኢየሱስ ትምህርቶችን ነው። በሌላ ንግግር ወንጌል የክርስቶስና የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ነው። መንፈስ ቅዱስን
የተቀበለ ኹሉ ከዚህ ትምህርት ውጪ ሌላ ትምህርት የለውም። ይህንን ትምህርትም ስናስተምር በሚያገኘን ማናቸውም መከራና ችግር
በደስታና በተስፋ የምንቀበል ነን። እናም መከራችንን ልናረክሰው አይገባም፤ በእውነትና በትክክል በጌታችን ኢየሱስ ስም መከራ
ልንቀበል ይገባናል፤ ስንቀበልም ልናጉረመርም፣ እልሃዊ ማናቸውም ምላሽ፣ ቁጣ፣ አሽሙር … መመለስ አይገባንም፤ ምክንያቱም
እንዲህ ያሉ ተግባራት መከራችንን የሚያጠለሹ፤ የሚያበላሹም ናቸው። መከራችንን በመታገስ (ሮሜ.12፥12)፣ እጅግ ደስተኞች፣
እግዚአብሔርን በሚፈራ ቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ኾነን መንፈሳዊ ምላሻችንን ልንገልጥ ብቻ ይገባናል፤ (ፊል.2፥17፤ ቈላ.1፥24)።
ቅዱስ ጳውሎስ እኒህን
መልእክቶች የሚጽፋቸው በሮም በእስር ላይ ሳለ ነው፤ በዚያ ኾኖ በመከራዎቹ ኹሉ ደስተኛና ባለ ሙሉ ተስፋ፣ የማያንጐራጉርም
ነው። ባለበት በማናቸውም እስር ቤቶችም ውስጥ ትጋቱና ጥማቱ ክርስቶስን መስበክና እርሱን መመስከር ብቻ ነበር። ይህም የኾነው
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት በማረጉና መንፈስ ቅዱስም በመምጣቱ ምክንያት ነው። ስለዚህም የጌታችን ኢየሱስ ማረግ
እጅግ የሚናፈቅ፣ በመሄዱም የምናዝንበት ጉዳይ አይደለም፤ ካልሄደ አጽናኙ አይመጣም፤ ሲሄድ በውስጣችን ኾኖ የሚያጽናናን
ይመጣል፤ ደግሞም ካልሄደ ሊወስደን ዳግመኛ አይመጣም፤ እናም ጌታችን ኢየሱስ ማረግህ እጅግ ታላቅ ደስታችን ነው፤ በማረግህ ደስ
ብሎናል፤ ዳግመኛ እንደ ምትመጣም እናምናለን፤ በተስፋ እንጠባበቃለን፤ አሜን፤ ማራናታ!
ተፈጸመ።
amen amen
ReplyDeleteamen amen amen kal hiwet ysmalna
ReplyDelete