መጽሐፍ ቅዱስ ወንድ አባ ወራ እንደ ኾነ ይነግረናል፤ “ባል
የሚስት ራስ ነውና።” (ኤፌ.5፥23፤ 1ቆሮ.11፥3)፣ እንዲል። እናም ወራውን(ቤተሰቡን) በአግባቡ ማስተዳደር አለበት፤ “ልጆቹን
በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ
ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?” (1ጢሞ.3፥4-5)። አባ ወራነት አስቀድሞ የወራ[በኦሮሚኛ ቤተሰብ ማለት ይኾንን?] ምስክርነት
ያሻዋል፤ ቤተሰቡን የማይወድና ለቤተሰቡ ምንም ከበሬታ የሌለው አማኝም ኾነ አገልጋይ በውጭ ያለውን ዓለም በመላው እንደ ሚወድ ቢናገር
ወይም ቢያሳይ ግብዝ ወይም አርቲስት እንጂ ሌላ ምንም ሊኾን አይችልም።
የባል አባወራነቱ አስተዳደራዊ ነውና፣ ትልቅ ፍቅር የሚጠይቅ ነው። በትልቁም
በትንሹም ውድ የኾነውን የባሎቻቸውን ፍቅር ያዩ ሚስቶች፣ ለባሎቻቸው እስከ ሞት በሚያደርስ ፍቅር እንደ ሚታመኑ ጥርጥር የለውም።
ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ፍቅር ዓይታ ለነፍሷ እንደ ማትሳሳ እንዲሁ፣ ሚስቶችም የአባ ወራቸውን “ደማቅ” ፍቅር ዓይተው ለባሎቻቸው
የማይታመኑበት፣ ልጆችም አባታቸውን እንደ “ንጉሥ” የማያዩበትና የማያከብሩበት አንዳች ምክንያት አይኖርም።
የአባ ወራነትን ድርሻ በአግባቡ ተፈትኖ የወጣ፣ ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ
መምራት ይቻለዋል። እግዚአብሔር አባ ወራነትን የመሰለ “አነስተኛ” ኅላፊነት በመስጠት ይፈትናል፤ በዚህ “አነስተኛ” በሚመስል ኅላፊነት
እግዚአብሔር ይፈትናል፤ በዚህ ያልታመኑትን ለቤተ ክርስቲያን ኅላፊነት አያጭም። በአብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ላይ ምን እየተተገበረ
ይኾን? የኃላፊነቱን ሥራ የያዙት እነማን ይኾኑ? በእውኑ ቤተሰብና ቤተ ክርስቲያን የመሰከሩላቸው ናቸውን?
በኢትዮጲያ የሥነ
ማኅበረሰብ ዘይቤ አባ ወራ የወራውን(የቤተሰቡን) የቀዳሚነትና የመሪነቱን ሥፍራ ይይዛል። የሚይዘውን ቦታ ያህል ሳይኾን ግን በአብዛኛው
የኢትዮጲያ አባ ወራ ለሚስትና ለልጆቹ ፍቅርና ክብር ባለመስጠት በጥብቅ ይታማል[ሉ]! እናም ብዙ ኃላፊነት በመዘንጋትና ባለመወጣት
የታወቅን ይመስላል።
ዋና ሃሳቤ ግን ወዲህ ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን አባ ወራዋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ነው፤ (ኤፌ.4፥15፤ 5፥23፤ ቈላ.1፥18፤ 2፥10፤ 19፤ ዕብ.12፥1)፤ እርሱ ለቤተ ክርስቲያን ክቡር ሙሽራዋ ነው፤ (ኤፌ.5፥23፤
ዮሐ.3፥29፤ ራእ.21፥9)፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እንደ ክርስቶስ ሌላ አጽናኝ ኾኖ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ማጫ ነው፤ (ዮሐ.14፥15)፤
ደግሞም ቤተ ክርስቲያን አብ የሰጠውን ተስፋ እርሱም መንፈስ ቅዱስን እንድትለብሰው የተሰጣት ኃይሏ ነው፤ (ሉቃ.24፥49)፤ ደግሞም
ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳፈሰሰው ቅዱስ ጴጥሮስ፦
“ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ
ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።” (ሐዋ.2፥33)
በማለት ገልጦታል፤ ጌታ እግዚአብሔር
አብ መንፈስ ቅዱስን ለክርስቶስ ሰጠው፤ ደግሞም ወልድ ተቀብሎ በሐዋርያቱ ላይ በአደባባይ አፈሰሰው፤ በክበበ ሥላሴ የተመከረውና
የታቀደው የመዳናችን ጉዳይ በአንድ ልብ በሥላሴ ዘንድ እንዲህ ተከወነ፤ ሥላሴ በመካከላቸው አንዳች መበላለጥ የለም፤ ስለእኛ መዳን
በሠሩት ሥራ ግን በአንዲት ፈቃዳቸው አንዱ ለሌላው ይታዘዛሉ፤ ደግሞም እያንዳንዳቸው በፍቅር ባሕርያቸው ያደርጉታል። ሥላሴ አንዲት
ሕብረትና ፈቃድ ብቻ ነው ያለው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን በሌላ ሥፍራ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው
አጽናኝ” (ዮሐ.14፥26) በማለት ገልጦታል።
መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት በአደባባይ ከፈሰሰበት ቀን ጀምሮ የአባ ወራነት
ኃላፊነት ከወልድ “ወስዷል”። ቤተ ክርስቲያንን በሥጋ ሞቱ የመሠረታት፣ በደሙም የገዛት፣ የራሱ ገንዘብም ያደረጋት እግዚአብሔር
ወልድ ነው፤ (ሐዋ.20፥28፤ 1ቆሮ.5፥7፤ 6፥19)፤ ከመሠረታት በኋላም ደግሞ አብሯት ለዘላለም ኗሪ ዘላለማዊውን አምላክ መንፈስ
ቅዱስን የላከው እርሱ ነው፤ ከመሄዱ በፊትም ለደቀ መዛሙርቱ፣ “እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው
የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐ.14፥17) በማለት፣
ልክ እንደ ክርስቶስ እውነት የኾነው የእውነት መንፈስ፤ መንፈስ ቅዱስ ለዘወትር ከቤተ ክርስቲያን የማይለይና ዘወትር ከእርሷ ጋር
ኗሪ እንደ ኾነ ተናግሯል።
ዓለም ዓያየውም፤ አያውቀውምም
(1ቆሮ.2፥14)፤ ሊቀበለውም አይችልም። የክርስቶስ የኾኑት ግን እርሱን ያውቁታል፤ ክርስቶስን የማይቀበሉ የእርሱን መንፈስ አይቀበሉትም፤
ክርስቶስን ለተቀበሉት እርሱ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ኗሪ ነው። አብሮ ኗሪ ብቻም አይደል፤ በውስጣችንም የሚኖር ነው፤ ስለኾነም
በድካማችን ጊዜ ኹሉ አብሮን አጋዥ፣ ቃታች፣ ማላጅም ነው፤ “ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደ ሚገባን
አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤” (ሮሜ.8፥26)፣ “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦
ና ይበል።” (ራእ.22፥17) እንዲል።
ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን አባ
ወራ፤ የቤተ ክርስቲያን ዋና መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን በየትኛውም ጉዞዋ መሪዋና አደራጅዋ እርሱ ነው፤ (ሐዋ.13፥2-3)፤
ያለ እርሱ ጥሪና ምሪት ምንም ምን ማድረግ አይቻላትም፤ ጌታችን ኢየሱስ እርሱን ካልለበሱ በቀር ደቀ መዛሙርቱ ወደ የትም እንዳይወጡ
የተናገራቸው ለዚህ ነው፤ (ሐዋ.1፥8)፤ እርሱ ምሪታቸውና መንገዳቸው ነው። እርሱ ወደ ሚመራቸው ወደ የትኛውም ሥፍራ ለመሔድ፣
የሚያዛቸውን የትኛውንም ሥራ ሊሠሩ ይወዳሉ፤ ይገደዳሉም፤ ምክንያቱም እርሱ የቤተ ክርስቲያን አባ ወራ፤ የቤተ ክርስቲያን ዋና መሪ
ነውና።
ይህ አባ ዋራ ግን ዛሬ በቤቱ የተዘነጋ፤
የተረሳ ይመስላል፤ በቤቱ ያልተደመጠ አባ ወራ መንፈስ ቅዱስ ነው። ብዙ አገልጋዮችና አማኞች ምሪት ፍለጋ፣ እንቅቅልሻቸውን ጥየቃ፣
ችግራቸውን ማወያያ፣ ሃሳባቸውን አጋሪ፣ ጭንቀታቸውን ተካፋይ፣ ምጣቸውን ማጭ፣ ሃዘናቸውን ተቋዳሽ፣ እንባቸውን አባሽ … ፍለጋ ከገዳም
ገዳም፣ ከነቢይ ነቢይ፣ ከሐዋርያ ሐዋርያ፣ ከጸበል ጸበል፣ ከቄስ ቄስ፣ ከአጥቢያ ከአጥቢያ … ሲንከራተቱ ማየት በዚህ ዘመን እንግዳ
አይደለም። አማንያንና አገልጋዮች በክርስቶስ ያመኑና በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁ ቀን የተቀበሉትን የልጅነት መንፈስ፣ አብሯቸውና በውስጣቸው
ያለውን የእውነት መንፈስ ከማድመጥ ይልቅ ዙርያቸው ያለውን ጩኸትና ግርግርታ በማድመጥ የተጠመዱ ኾነዋል።
መንፈስ ቅዱስ ምን ብሎ ተናገረኝ?
በቅዱስ ቃሉስ ምን አለኝ? ሳይኾን፣ አባ እገሌ ምን አለ? ፈዋሹ ጸበል፣ ፈዋሹ ነቢይ፣ ፈዋሹ ሐዋርያ፣ .. የት ነው? እገሌስ
በምኑ ነው የሚፈውሰው? በጸበል፣ በመሐረብ፣ በሶፍት፣ በንግርት፣ በመቁጠሪያው፣ … በምኑ ነው? በሚል መቅበዝበዝ ተጠምደናል። ዋናውን
አባ ወራ ንቀን የሚያንሰውንና የማያሳርፈውን በመከተል ባክነናል። “ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ
ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።” (መዝ.46፥10) ተብለን፣ እኛ ግን መቅበዝበዝን መርጠናል።
ብዙ የሚያስጨንቁ፣ የሚያስተክዙ፣
የሚያስለቅሱ፣ … ነገሮች በዙርያችን አሉ፤ ግን ማደንዘዣውን እንጂ መድኃኒቱን ከልብ አልፈለግንም፤ መምህራንን፣ አገልጋዮችን፣ መንፈሳውያን
ወንድሞችን፣ እህቶችን ማማከር መልካም ነው፤ ያ ግን የመጨረሻ አይደለም፤ እነርሱም እንኳ ወደ ዋናው እኛን የማይመሩበት ጊዜ ብዙ
ነውና ዋናችንን ፊቱን እንፈልገው፤ አባ ወራችንን በንስሐ እንታረቀው፤ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ነው፤ እርሱ ክርስቶስን ለሚያምኑ አብሯቸው
ለዘላለም ሊኖር በአዲሱ ኪዳን፤ ኪዳን ገብቷልና ፊታችንን ወደ እርሱ እናቅና።
ዛሬ መንፈስ ቅዱስ በብዙ አብያተ
ክርስቲያናቱ[በቤቱ] የአንድ አገልጋይ፣ ጳጳስ፣ ነቢይ፣ ቄስ፣ ሐዋርያ፣ መጋቢ፣ ዘማሪ … ያህል እንኳ አልተፈራም፤ አልተከበረም፤
አልተደመጠምም፤ ይህንን ብዙ አገልግለን ጥቂት እንኳ ማረፍና ማሳረፍ ካለመቻላችን መረዳትና መመልከት እንችላለን። እንዲሁም አገልጋዮች
ገንነው እግዚአብሔርን መፍራት ግን ከሰዎች ልብ መሸሹን በማየት ማስተዋል እንችላለን። አባ ወራውን አለመመልከትና አለማክበር በመጨረሻ
ሳያዋርድና ሳያስቀጣ አይቀርም፤ መመለስና ማረፍ እንዲኾንልን ከአባ ወራችን ጋር ፈጥነን እንታረቅ፤ ዘመን ዘለቅ ሕይወትና አገልግሎት
እንዲኖረን አባ ወራውን በማክበርና በመፍራት እንጠመድ፤ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋሉን ያብዛልን፤ አሜን።
ewnet blehal kal!hiwot yasemaln
ReplyDeleteመንፈስ ቅዱስ ምን ብሎ ተናገረኝ? በቅዱስ ቃሉስ ምን አለኝ? ሳይኾን፣ አባ እገሌ ምን አለ? ፈዋሹ ጸበል፣ ፈዋሹ ነቢይ፣ ፈዋሹ ሐዋርያ፣ .. የት ነው? እገሌስ በምኑ ነው የሚፈውሰው? በጸበል፣ በመሐረብ፣ በሶፍት፣ በንግርት፣ በመቁጠሪያው፣ … በምኑ ነው? በሚል መቅበዝበዝ ተጠምደናል። best article
ReplyDeleteያበርታልን
ReplyDelete