Saturday, 19 May 2018

ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት ለምን ዐረገ? (ክፍል ፪)


2. ምስክርነታችንን እጅግ የታመነ ይኾን ዘንድ፤
   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት ካላረገና ካልሄደ በቀር ምስክርነታችን ምሉዕ አይኾንም፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን ምስክሮች እንደ ሚኾኑ ተናገራቸው፤ (ሐዋ.1፥8)፤ ምስክርነታቸው ከጌታ ኢየሱስ ለሠሙትና ላዩት ነገር ኹሉ ነው፤ (1ዮሐ.1፥1-3)፤ ካዩት ነገር ዋናውና አንዱ ደግሞ ዕርገቱ ነው። ቅዱሳን መላእክት ማረጉን ወዲያው ተናገሩት፣ “ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል” (ሐዋ.1፥11) በማለት። ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት ወደ አባቱ ክብር ይገባ ዘንድ ዐርጓል፤ ስለዚህ “ትኩር ብላችሁ ወደ ሰማያት አትመልከቱ፤ በመመልከትም ጊዜን አታባክኑ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ልታስተምሩ ገና ሰፊ በርና አገልግሎት አላችሁ” አሏቸው፤ አዎን! ሰማይ በዕርገቱ ሲከፈት፣ በምድር ደግሞ የአገልግሎት በር መርቆ ተከፈተ።
  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ብዙ ተጠራጣሪዎችን ወደ እምነት መንገድ መልሷል፤ ቅዱስ ማቴዎስ እንዲህ ይለናል፣ “አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ።” (ማቴ.28፥16-17)፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱ አምልከውታል፤ ስግደትም አቅርበውለታል። በሌላ ሥፍራም ወደ ሰማያት ሲያርግ እንደ ሰገዱለት ተጽፎ እናገኛለን፤ (ሉቃ.24፥52)። የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ስግደትና አምልኮን ይቀበል ዘንድ ይገባዋል።
 ክብር ይግባውና፣ አንዳንዶች ጌታችን ኢየሱስን ሰው ብቻ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ አምላክነቱን በማጉላት ሰውነቱን ይዘነጋሉ፤ በክብር ያረገው ጌታ ግን ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ወይም አምላክና ሰው ነው። ምንም የሰውን ሥጋ ቢለብስ አምልኮ ተቀባይ ነው፤ ምንም አምላክ ቢኾንም ደግሞ በሰውነቱ ያገለገለን፣ በሰማይ ባለችም ቅድስተ ቅዱሳን የሚያገለግለንና የሚታይልን አባትና መድኃኒት፤ አምላክና ቤዛ፤  አዛኝና ፈራጅ፤ ጌታና በከበረ ወርቀ ደሙ የገዛን፤ የዋጀን ትምክህታችንና አምላካችን ነው።
 በብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተዘነጋና የተተወ፣ የተነቀፈም የስብከት ርእስ ቢኖር፣ እንዲህ ያለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኝነት ነው። የክርስቶስን ፍቅር በሚገባ የነገሩን ፍርዱን ለመናገር አንደበታቸው ይተሳሰራል፤ ይንተባተባል፤ ፍርዱን በቁጣና በጩኸት ቃል የሚነግሩን እልፍ አእላፋት ደግሞ፣ አዳኝነቱንና ቤዛነቱን የፍርዱን ያህል ቢናገሩ ጌታ ኢየሱስ የሚያንስባቸው፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አንድነት የሚነጠል እየመሰላቸው ሥጋ ደማዊ ሥጋትን ያቃጭላሉ። ያው አንዱ ጌታ ግን ኹሉ በኹሉ፣ ሲያገለግለንም አምላክ፤ ሲመለክና ሲሰገድለትም ያው አምላክና ፈራጅ የኾነ ነው። በአምላክነቱ በቅዱስ ፍርሃት እንፈራዋለን፤ እንገዛለታለን፤ እኛን ባዳነበት ፍጹም ሰውነቱ ደግሞ ነፍስ እስከ ማይቀርልን ድረስ ፍጹም እንወደዋለን። ፍግም ብለን በፈቃዳችንም ከፍቅሩ የተነሣ ወደን እንሰግድለታለን።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ኹሉ በኹሉነቱ በትክክል አለ ማወቅ ሳያስት አይቀርም፤ በዘመናችን የምናየው ትልቁ ስህተት ይኸው ነውና። ይህ አለ ማስተዋል ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው የነበረ ጊዜም የታየ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ከእናቱ በቀር በዘመዶቹ ዘንድ አንዳች ከበሬታ አልነበረውም፤ “ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና።” (ዮሐ.7፥5) እንዲል፣ ከወንድሞቹ ኹሉም ከዘመዶቹ ብዙዎች አላመኑበትም፤ አልተቀበሉትምም። በአገልግሎት ዓለም ትልቁ ሕመም የቅርብ ሰዎች ማቁሰል ነው፤ ሥራዎቻችንን፣ ጠባያችንን፣ ጥንካሬያችንን፣ ችሎታችንን፣ “ግላዊ ገመናዎቻችንን”፣ ውድቀታችንን፣ ስብራታችንን የሚያውቁ … ሰዎች እጅግ ብዙ ጊዜ ሲያከብሩትና ሲቀበሉት አናስተውልም፤ ይልቁን ብዙ ጊዜ ሕመሞቻችን ናቸው፤ በዓይኖቻቸው መካከል “በሽታ ሆነን በዓለም … ሁሉ ሁከት አስነሺ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆነን” (ሐዋ.24፥5) ነው የምንታያቸው።
ስለዚህም ብዙ ጊዜ ምስክርነታችን ይሰለላል፤ በጥርጥሬ ይታያል፤ ከተሰቀለው ጌታችን ኢየሱስ ጋር ኾነን፣ ለእርሱ ማድላታችንና ለእርሱ ብቻ መቅናታችን “የብዙ ዓመታት ዝምድናና ወዳጅነት” በቅጽበት ለመፍረስ ከበቂ በላይ ዋና ምክንያት ይኾናል። ዘፈንና ዝሙት፣ ዘረኝነትና ጐጠኝነት የሚያወዳጃቸው፣ ዝምድናና ባልንጀርነት … የሚያጋምዳቸው ብዙዎች፣ በተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ መኾን ሲሳናቸው ስናይ ሳንደነቅ አንቀርም፤ ጌታችን ኢየሱስን የገዛ ዘመዶቹ አለማመናቸው እንዳስደነቀው፤ (ማር.6፥6)፤ አማኝ ብቻ አይደለም፤ ብዙ ተደርጐለት ሊያምን ያልወደደ አላማኝም ያስደንቃል!!!
በእርግጥ ዕርገቱን አንዳንዶች መጠራጠራቸውን ማቴዎስ ነግሮናል፤ ከተጠራጠሩት አብዛኛዎች ሲሞትና ሲነሣ ያልተመለከቱቱ ሊኾኑ ይችላሉ፤ ቅዱስ ጳውሎስ “ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤” (1ቆሮ.15፥6) በማለቱ፣ ከእነዚህ አንዳንዶች ሊጠራጠሩ እንደ ሚችሉ ይታመናል፤ ልክ አስቀድመው ደቀ መዛሙርቱ ተጠራጥረው እንደ ነበረው ማለት ነው፤ (ሉቃ.24፥37)። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ግን የቀየረው ታላቅ ታሪክ አለ።
  ቅዱስ ያዕቆብ የጌታ ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ነው፤ (ማቴ.12፥46፤ 13፥55)፤ ጌታን ካላመኑት ወንድሞችም መካከል አንዱም ነበር፤ ከጌታ ዕርገት በኋላ ግን ነገር ተለውጧል፤ “ … እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።” (ሐዋ.1፥14)። ጌታ ኢየሱስ በሕይወት ዘመኑ እያለ ያላመኑበት ወንድሞቹ፣ ከዕርገቱ በኋላ ግን እንዳመኑበትና የእግዚአብሔር ልጅነቱን እንደ ተቀበሉ እናስተውላለን፤ ደግሞም ወደ አባቱ በስሙም እየጸለዩ በጸሎት ይተጉ ነበር።
  ቅዱስ ያዕቆብ ጌታ ከሙታን መካከል ሲነሣ ተገልጦለታል፤ (1ቆሮ.15፥7)፤ ደግሞም ሲያርግ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ በትክክል አምኗል። ማርኰ ካስቀረው ነገር አንዱ በክብር ደመና የክብሩ ጌታ ማረጉን በማመኑ ነው። በምድር ሳለ ምናልባት እንደ እኩያው ወይም አብሮ አደግ ብቻ ዓይቶት አላመነበትም ነበር፤ አኹን ግን ሲያርግ የእግዚአብሔር ልጅነቱን አመነ፤ ጌታችን ኢየሱስ እንዴት አስደናቂ፣ ትዕግስቱ የበዛና የተትረፈረፈ አምላክ ነው፤ ወንድሞቹና ዘመዶቹ ባያምኑበት እንኳ እስኪመለሱ እንዴት እንደ ጠበቀ አስተውሉ! “የሩቆቹ ሲያምኑብኝ እናንተ እንዴት እናንተ አላመናችሁብኝም?” ብሎ አልተቆጣም፤ ኦ! ኢየሱስ አስደናቂና ግሩም አባትና ወዳጅ!
ቅዱስ ያዕቆብ ከተመለሰና ካመነ በኋላ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ አባት ኾነ፤ የመጀመርያው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ሲደረግ እርሱ የኢየሩሳሌምን ጉባኤ የሰበሰበና የቤተ ክርስቲያኒቱም መጋቢ ነበር፤ (ሐዋ.15፥1-35፤ ገላ.1፥19፤ 2፥9)፤ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደ ሚተረከው በጸሎት ሕይወቱ የታወቀ አባትም ነበር፤ የሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ መልእክትንም የጻፈው እርሱ ነው፤ አስተውሉ! ይህ አባት ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በምድር ሲመላለስ ያላመነ ሰው ቢኾንም፣ ከሙታን ትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ ግን በጌታችን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት አመነ።
ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት ማረጉ እንዴት ያሉ ሰዎችን ለምስክርነት እንደ ጠራ እናስተውል፤ ለእኛም ዕርገቱ የምስክርነታችን ዋና ርዕስ ነው፤ የምንመሰክርለት ጌታ የት እንዳለና ወዴት እንደ ሄደ ያወቅነው በዕርገቱ ነውና። አገራችን በሰማይ ነው የምንለውም፣ ሰማይን ቀድሞ ገብቶበት፣ ወደዚያ እንደ ሚወስደን ኪዳን የገባልን አባት ስላለን ነው። እርሱ በክብር እንደ ገባ እኛንም በክብሩ ሊወስደን ይመጣል።
ሲያርግ፣ “በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።” (ሉቃ.24፥47-48) ብሎ የተናገረን እርሱ ነው፤ ምስክርነታችን ሕያውና ኹሉን ወራሽ የኾነው ግን በጌታችን የትንሣኤ ኃይል፣ የዕርገቱ ድል ነሺነት ነው። ቅዱስ ያዕቆብና ብዙዎች እንደ እርሱ ያሉት፣ በኢየሱስ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ የሻሩትና ፍጹም በእርሱ ያመኑት ዕርገቱን ካዩ በኋላ ነው። አብሮ አደግነትና እኩያነት ተኖ የጠፋውና የጌታ ኢየሱስ ጌትነትና የያዕቆብ የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያነትን ያስረገጠው ዕርገቱ ነው፤ በሥጋ በዚህ ምድር ሳለ፣ ኢየሱስን ለማክበር እንኳ ምንም መሻት ያልነበረው ያዕቆብ፣ ራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ (ያዕ.1፥1) ብሎ ያቀረበው የክብሩን ጌታ በክብር ሲያርግ ስላየው ነው።
ያረገው ጌታ መጥቶ እንደ ሚወስደን እናምናለን፤ ስለዚህ ስንመሰክር አናፍርም፤ አንፈራምም። አድራሻችን ሰማይ ነውና ምስክርነታችንም ሰማያዊ ነው። ምስክርነታችንም የተረጋገጠውና ላይናወጥ የጸናው በክርስቶስ የሥጋ ሞት፣ ትንሣኤና ዕርገቱ ነው። ወንጌላችን ወይም ምስክርነታችን የማይበገረው፣ የማይለወጠው፣ የማይፈታው፣ የተደላደለው፣ ሕትመቱ የማይደበዝዘው … ምስክሮቼ ትሆናላችሁ ባለውና በክብር ባረገው ጌታ ምስክሮች ስለኾንን ነው። እውነተኛ ምስክሮች ሆይ! ደስ ይበላችሁ፤ ጌታችን በክብር በሰማይ አለና፣ የክብሩን ጌታ በክብር ዕያያችኹት ደፍራችሁ መስክሩት፤ ተናገሩትም! ጸጋውን መንፈስ ቅዱስ ያብዛላችሁ፤ አሜን።


1 comment:

  1. ያረገው ጌታ መጥቶ እንደ ሚወስደን እናምናለን፤ ስለዚህ ስንመሰክር አናፍርም፤ አንፈራምም። አድራሻችን ሰማይ ነውና ምስክርነታችንም ሰማያዊ ነው። ምስክርነታችንም የተረጋገጠውና ላይናወጥ የጸናው በክርስቶስ የሥጋ ሞት፣ ትንሣኤና ዕርገቱ ነው። ወንጌላችን ወይም ምስክርነታችን የማይበገረው፣ የማይለወጠው፣ የማይፈታው፣ የተደላደለው፣ ሕትመቱ የማይደበዝዘው … ምስክሮቼ ትሆናላችሁ ባለውና በክብር ባረገው ጌታ ምስክሮች ስለኾንን ነው። እውነተኛ ምስክሮች ሆይ! ደስ ይበላችሁ፤ ጌታችን በክብር በሰማይ አለና፣ የክብሩን ጌታ በክብር ዕያያችኹት ደፍራችሁ መስክሩት፤ ተናገሩትም! ጸጋውን መንፈስ ቅዱስ ያብዛላችሁ፤ አሜን። amen amen

    ReplyDelete