Monday, 23 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (የመጨረሻው ክፍል)


4.   “የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መካድ፣ በመጽሐፉ ቃል ላይ “የራስን ሃሳብ” መጨመር፤ የቃል ትእዛዝና፣ የገዢነት ሥልጣን”
     “ … ፊተኛው አዳም “lose” ያደረውን ነገር ሁሉ ኋለኛው አዳም መልሷል፤ ፊተኛው አዳም ምንድርነው lose ያደረገው? የተፈጠረበት “purpose” ምን የሚል ነበረ? ምድርን ግዛ፣ ባሕርን ግዛ፣ የሰማይ አእዋፍን ግዛ የሚል ነው፤ ያን ገዢነት ለእኛ መልሷል፤ ሁለተኛው አዳም በዚህ ማንነት ነው የተገለጠው … እያንዳንዱን ነገር አስተካክሏል፤ ለምሳሌ ባሕርን ግዟት አለ፤ በባሕር ውስጥ ያሉት ዓሦች አሉ፤ ኢየሱስ በአንድ ወቅት ግብር ክፈሉ ሲባል፣ ከዛ ጴጥሮስን ምን አለው? ወደባሕር ሂድ፣ ከዛ ዓሳ ታገኛለህ፣ ዓሣ ውስጥ ምን አለ ዲናር አለ፤ እርሱን አንዱን ለእኔ፣ አንዱን ላንተ ትከፍላለህ አለው፤ … ኢየሱስ ለማስደነቅ ምናምን ተአምር ያደረገ ይመስላችኋል? ዓሣ ውስጥ ያ ዲናር ከየት መጣ? …
    ኢየሱስ ሲናገር ዓሳ ውስጥ ዲናር ሲሠራ ነበር፤ በዚህ ቃል ነው ዓለምን የፈጠረው፤ … ምድርን ሲፈጥር እኮ ከነዳይመንዷ ነው የፈጠረው፤ አሁን አይግረምህ … ዓሳው የሆነ ቦታ ዲናር ውጦ አይደለም፤ ይኼ አንተ ያለህ ቃል የሚሠራ ነው፤ የሌለውን እንዳለው አድርጎ የሚጠራ፤ የሚያመጣ ነው፤ አዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ይህ ነው፤ ምንም ነገር በቃሉ … [የበለሲቱን ምሳሌ አንስቶ]… የማትፈልገውን ትናገራለህ ይደርቃል፤ የምትፈልገውን ትናገራለህ ይለመልማል፤ የአዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ነው ይኼ፡፡
     አዲሱ ፍጥረት ዓሣን ብቻ ማዘዝ እንዳይመስልህ ወዳጄ፤ ባሕሩ ላይ መራመድ ካስፈለገህ ትራመዳለህ፤ ይኼ [ኢየሱስ]አምላክ ስለኾነ አይደለም ያደረገው፤ ገና born again ያላደረገው ጴጥሮስን ተናገር ብሎታል፤ “born again” ያልተወለደው ከተራመደ አንተ እንዴት?[አትችልም?] ያኔ ጀልባ ስላለ ላያስፈልግ ይችላል፤ ጭንቅ ቢኾን ትሞታለህ እንዴ? [ሰሚዎቹ በጣም በሚጮኽ ድምጽ አልሞትም ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማል፤] ትራመድበታለህ፤ በባህር ላይ እንድትራመድ የሚያደርግህ “Divine thecnology” ባንተ ላይ ይገጠማል፤ እምነት ይባላል፤ … ”
     በጋሻው በዚህ ትምህርቱ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ይስታል፤
1.     በጋሻው፣ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕር የተራመደው አምላክ ስለኾነ አይደለም” ይለናል፡፡ እንዲህ በማለት፦ “... ባሕሩ ላይ መራመድ ካስፈለገህ ትራመዳለህ፤ ይኼ [ኢየሱስ]አምላክ ስለኾነ አይደለም ያደረገው፤ ገና “born again” ያላደረገው ጴጥሮስን ተናገር ብሎታል፤ “born again” ያልተወለደው ከተራመደ አንተ እንዴት?[አትችልም?] ያኔ ጀልባ ስላለ ላያስፈልግ ይችላል፤ ጭንቅ ቢኾን ትሞታለህ እንዴ? [ሰሚዎቹ በጣም በሚጮኽ ድምጽ አልሞትም ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማል፤] ትራመድበታለህ፤ በባህር ላይ እንድትራመድ የሚያደርግህ “Divine thecnology” ባንተ ላይ ይገጠማል፤ እምነት ይባላል፤ … ”

Monday, 16 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (ክፍል 4)

Please read in PDF

3.  በጋሻው “ሰው መንፈስ  ነው” ይለናል፤ ከየት ይኾን የቀዳው?
    በጋሻው የሰውን ሰውነት አያምንም፡፡ ሰው ሥጋና ነፍስ ወይም ሥጋና መንፈስ ነው፤ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በጋሻው፣ “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል፡፡” በሚለው ፍጹም ክህደት ደምድሞታል፡፡ የዚህ ኑፋቄ ትምህርቱንም ሲያብራራ እንዲህ ይላል፦
   “ ... በእግዚአብሔር የተፈጠረው መንፈስ የሆነው ሰው ከምድር አፈር አዘጋጀው፡፡ ... ያበጀውን፣ የፈጠረውን ያበጀው ውስጥ ጨመረው፤ መንፈስ ሥጋ ውስጥ ገባ ማለት ነው፡፡ ... ነፍስ ማለት ሦስተኛ አካል ምናምን አይደለችም … ነፍስ የተባለው ነገር ዕውቀት ስሜት ፈቃድ ናት፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ዕውቀት ወይም ትምህርት ... ለምሳሌ፦ ባዮሎጂ አካል አለው እንዴ? ... እርሷ[ነፍስ] በመንፈስና በሥጋ መካከል ሆና ላሸነፈው ላሳመነው ... እርሷን ራሱ በዕውቀት ነው የምታሳምነው፡፡ ... በተጨባጭ ነገር ካመነች ስሜት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ...
     ... ስለዚህ ሰው የራሱ ፈቃድ፣ የራሱ እውቀት፣ የራሱ ስሜት ያለው ማንም ጣልቃ የማይገባበት ለወደደው ነገር ራሱን የሚያስገዛ ማንነት ባለቤት ሆኖ ተፈጠረ፡፡ ስለዚህ ሰው ማን ነው? ከተባለ መንፈስ ነው ነፍስ አለው በሥጋ ውስጥ ያድራል ነው መልሱ፡፡ ሰው ሥጋ ነው፤ ነፍስ ነው አትልም፤ ሰው ማን ነው? ከተባለ ሰው መንፈስ ነው፤ …” 

Tuesday, 10 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (ክፍል 3)

2.   በጋሻው ደሳለኝ ተቀባሁበት ያለው “የኢየሱስ ቅባት”?!
    መጽሐፍ ቅዱስ ስለቅባት ወይም መቀባት ግልጥና ምንም የማያሻማ ትምህርት አለው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ነቢያት፣ ካህናትና ነገሥታት እንዲሁም ዕቃዎች ለአገልግሎት ስለመለየታቸውና ስለመሾማቸው በዘይት ይቀቡ ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር ሥራ የተለዩት የብሉይ ኪዳን የመገናኛው ድንኳንና ዕቃው ተቀብተው ነበር፤ (ዘጸ.30፥22-29)፡፡
    “ … ይህንን በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በግልጥ ሰፍሮ እንመለከተዋለን፡፡ እኒህም ካህናት፣ ነገሥታትና ነቢያት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙት በቅዱስ ቅባት ከተቀቡ በኋላ ነበር፡፡  ለምሳሌም፦ ሙሴና ወንድሙ አሮን (ዘጸ.40፥13 ፤ ዘሌ.4፥3 ፤ 8፥1 -9፥1-8 ፤ መዝ.98(99)፥6)፣ አብያታር(1ሳሙ.30፥7 ፤ 1ዜና.15፥11፤ 27፥34)፣ … ካህናት፤ ሙሴ (ዘዳግ.18፥15 ፤ ሐዋ.7፥37)፣ ናታን(2ሳሙ.7፥2)፣ ሳሙኤል (1ሳሙ.7፥15-17) … ነቢያት፤ ዳዊት(1ሳሙ.16፥13 ፤ 26፥11 ፤ 2ሳሙ.5፥3፤ ሐዋ.13፥22)፣ ሰሎሞን( 1ነገ.1) እኒህና ሌሎችን ብናነሣ ካህናት፣ ነቢያትና ነገሥታት የሆኑትና ሕዝቡን በግልጥ ያገለግሉ የነበሩት በአደባባይ በቅዱሱ ቅባት ተቀብተው ነበር፡፡ ይኸውም ለተለዩለትና ለተሾሙበት ሥራ በቅዱሱ እግዚአብሔር መለየታቸውንና ለሥራቸው ብቁዐን አድራጊው በዘይቱ የተመሰለው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መኾኑን በምሳሌነት ያሳያል፤ …” [1]
    በዚህ ዘመን የሚነሡ የሐሰት መምህራን “ተቀባሁ ወይም ተቀብቻለሁ” የሚለውን ሃሳብ ይዘው የሚነሱት፣ ስለመቀባት የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን “በሥልጣናዊ ቃልነት” የራሳቸውን ሃሳብ በማስገባት ሊጠቀሙባቸው በማሰብ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከእግዚአብሔር ተምረናል ብለው የሚናገሩትን ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንቀበላቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በእንከንና በሕጸጽ የተከበበውን ትምህርታቸውን “ትክክል አይደለም” ብለን ብንሞግት፣ “የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤” (መዝ.107፥14-15) የሚለውን በመጥቀስ እንዳፈለጋቸው ቢያጠፉና ቢያስቱ ምንም እንዳንናገራቸው፤ “በመቅሰፍታቸው ሊገስጹን” ስለሚፈልጉ ነው፡፡

Wednesday, 4 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (ክፍል 2)

በክፍል አንድ ላይ ለተሰጡ አስተያየቶች “ሚጥጥዬ መደምደሚያ”
    የተሰጡት አስተያየቶች ሁለት መልክ ያላቸው ናቸው[ሦስተኛውን የስድብ ክፍል መጥቀስ ባልሻም]፤ አንደኛው ቀድሞ በግል መምከርና ማናገር ይገባ ነበር እና አንተ ራሱ ማን ኾነህ ነው እርሱን “የምትኰንነው?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ለአስተያየቶቹ መልስ መስጠትን ባላምንበትም፣ በአብዛኛው በዙርያዬ ያሉ ሰዎች ያዘነቡትን ስድብና[በተለይ በኢሜይል] አስተያየት ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እጅግ ስለወረደብኝ፣ የትምህርቱን ኢ ክርስቶሳዊነት ለሚረዱት የማጥራት ሥራ ለመሥራት፣ ትምህርቱን አምነው ለተከተሉት ደግሞ በክርስቶስ ትምህርት ላይ ለሚመጣው የትኛውም ሰውም ኾነ ማኅበር ጭካኔዬን ለማሳየት ነው፡፡ አንድ ነገር ማስታወስ እወዳለሁ፤ አሁን እየተቃወሙ ካሉ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት ግብረ ሰዶማውያን አገልጋዮች በግልጥ ተደርሶባቸው እንዲመለሱ ብዙ ተመክረው አልመለስ ሲሉ፣ ከአደባባይ ነውራቸው አልመለስ ብለው ልባቸውን ሲያደነድኑና እውነታውን ለማድበስበስ ሲጥሩ በአደባባይ ሰዎች እንዲጠነቀቋቸው ስጽፍ የተቃወሙኝ መኾናቸውን አሁንም ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
    በጋሻውን በተመለከተ በተደጋጋሚ ማውራቴንና በዚህ ትምህርት ማመን አለማመኑን ስለመጠየቄ፣ እርሱም ስለመናገሩ ያልጻፍኩት፣ ብዙም አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነው፤ አስፈላጊና ሁሉ ማወቁ የግድ ተገቢ ነው ከተባለ ግን እንዴትና ምን ብዬ እንዳወራሁት፤ እርሱም በዚህ ትምህርት ዙርያ ያለውን አቋሙን ምን ብሎ እንደነገረኝና ይህን የሐሰት ትምህርትም ሊለውጠውም እንደማይፈቅድ የመለሰልኝን በዚህ ጽሁፍ ማብቂያ ላይ ለመግለጥ ቃል እገባለሁ፡፡

Monday, 2 October 2017

በጋሻው ደሳለኝ ና አዲሱ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” ትምህርቱ (ክፍል 1)

ግቢያ
     በዚህ ዘመን በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታወቁትን(ማቴ.7፥23) በሕዝብ ዘንድ የገነኑትንና የታወቁትን አገልጋዮች “ተሳስታችኋል ተመለሱ” ማለት፣ ራስን በስለት ላይ የማቆም ያህል ሕመሙ ጽኑና እጅግ አደገኛ ነው፡፡ አደገኛነቱም ከሁለት ነገር አንጻር ነው፤
1.     ደጋፊዎቻቸው ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ ተቃውሟቸው ተራ ተቃውሞ ሳይሆን፣ ልክ እንደቅዱሳን ሰማዕታት ስለመምህሮቻቸው በነፍስ ተወራርደው እስከመግደልና ስም ለማጥፋት የሐሠት ታሪክን ፈብርከው ከማኅበረሰቡ እስከማግለል ሊያደርስ በሚችል ጽኑ ቁጣ ውስጥ ስለሚገቡና፤
2.    ሕዝብ[አማንያንም ጭምር] ደግሞ እንዲህ ያለውን ነገር በቅንነትና በልበ ሰፊነት ከእግዚአብሔር ቃልና ከስህተት መምህራን ጠባይ አንጻር ከመመዘን ይልቅ፣ እንዲህ ያሉ መምህራንን የሚቃወሙትን አካላት ቀንተው ወይም ከጥላቻ አንጻር ... አንዳንዴም ሲከፋ የራስን ቅቡልነት በሕዝቡ ለማስረጽ የሚደረግ ደባ ነው በማለት፣ ተግሳጽና ተቃውሞውን በትክክል ለሕዝቡና ለእግዚአብሔር ከመቅናት አንጻር እንደተደረገ አድርጎ መውሰድ ፈጽሞ አልተለመደም፡፡