Tuesday, 27 August 2013

የእግዚአብሔር መላዕክት ደስታ

       ባዕለጠጋውና ምንም ያልጎደለበት ትልቁ እግዚአብሔር መልኩን  የሚመስል (የጸጋ እውቀት ያለውና ህያው ሆኖ እስትንፋሱን የተካፈለ) እንደምሳሌውም (ገዢነትና ስልጣንን ሁሉ ከሰማይ በታች ያለውና በራሱም ነጻ ፈቃድ መወሰን የሚቻለውን) ክቡር ፍጡር ሰውን ፈጠረ፡፡ እንዲሰግድለት፣ እንዲገዛለት፣ ባርያ ሆኖ እንዲያገለግለው፣ እንዲያመልከው አልፈጠረውም  … እርሱን መስሎ የእርሱ የሆነውን እስትንፋሰ መለኮቱን እንዲካፈለው ፈጠረው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የእርሱ የሆነውን እንዲወርስና እንዲካፈል ፈጠረው፡፡ ባሕርይው ቅዱስ የሆነ ጌታ አመስጋኝ ባይኖር የተመሰገነ ምስጉን የተቀደሰ ቅዱስ ነው፡፡ አመስጋኝ ባይኖር እግዚአብሔር ምስጉን ነው፡፡

        ከሌሎች የፍጥረት ቀን ይልቅ ሰው በተፈጠረበት ቀን የሆነውን ቅዱስ ሙሴ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ "እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ"(ዘፍ.1÷31) ብሎ ጻፈው፡፡ በእርግጥ ሰው እጅግ መልካም ስለነበረም ነው በኃጢአት በወደቀ ጊዜ ይኸው ጌታ በቤዛነት ሊያነሳው ኪዳን በስሙ የገባለት፡፡

       ጠላት ሰይጣን እስከመጨረሻ ለመጣል ሙሉ ኃይሉን የተጠቀመ ቢሆንም ጌታ ግን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ከህሊናና ከመረዳት የላቀውን በልዩ የማዳን ጥበቡ ተገለጠ፡፡ ከጠላትም ተግዳሮት የሚበልጥ ምህረትና ኪዳን መጣ፡፡ ሞት ረዥሙን የዘላለም መንገድ በዕድሜ የገደበና ያጠረ ቢመስለውም ክርስቶስ ሁለተኛው አዳም ሆኖ የመጀመርያውን አዳምና እኛን ወደታየልንና ወደመልካችን የመለኮቱ ባሕርይ ተካፋይነት መለሰን፡፡
      ሰይጣን ያለንን የነጠቀ ሲመስለው እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የጠለቀ ፍቅር ከቶውን አላስተዋለውም ነበር፡፡ ትልቁ ጌታ እግዚአብሔር አዳምንም እኛንም በምንም ሁኔታ ብንሆን በማይዝል ክንዱ ይዞናል፣ በማይፈታ ፈትል ቋጥሮናል፡፡ ሰይጣን አዳምና ልጆቹ እንደወጡ የሚቀሩ፣ የእርሱ የዘላለም ባርያና ገረድ ሆነው ተገዝተው የሚቀሩለት መስሎት ነበር፡፡ የእርሱ ገንዘብ ስላልነበሩም ምንም አላዘነላቸውም፡፡ ስላልፈጠራቸውም ሞትን ነበር የደገሰላቸው፡፡ ጌታ ግን አሻግሮ አየላቸው የጸናውንም ክንዱን ሰደደላቸው፡፡
     ጌታ የባርያውን፣ እመቤት የገረዷን፣ አለቃ የምንዝሩን፣ መምህር የተማሪውን ልብስ በሚጠየፍባት በዚህች የሥጋና የመናናቅ ምድር ላይ ትልቁ ጌታ ኢየሱስ የተናቀውን የተዋረደውን የአዳምን፣ የእኔን የአንተን፣ የአንቺንየሁላችንን ይህን ሥጋ ይዋሐዳል ብሎ ሰይጣን ከቶውንም አላሰበም፡፡ ከፍታ በከፍታ የሚበልጥ መሰለው፡፡ ለሰይጣን ከፍታ በፍጹም ዝቅታ እንደሚረታ ማን በነገረው? አዎ! ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ አለልክ ዝቅ ብሎ ከክብርም ከደመናትም ሁሉ በላይ እጅጉን ከፍ ከፍ አለ፡፡ ረዥሙ ሰማያዊ ፈትል ክርስቶስ በአባቱ ዘንድ እያለ ወደእኛ መጣ፡፡ ስንቶቻችን እንሆን ለቤት ሰራተኞቻችን ክብርን የምንሰጥ? ዝቅ ብለን እንደጌታ ማገልገልስ የሚሆንልን ስንቶቻችን ነን? የባርያውን ልብስ(ሥጋ) የለበሰ ክርስቶስ እንዴት የተወደደ ውድ ጌታ ነው?
     የበዙ አዕላፍ በጎች ያሉት እውነተኛ እረኛ ለአንዱ በግ ነፍሱን ሊያኖር አድራሻውን አድራሻ አድርጎ ተገለጠ፡፡ ብዙ ክስና ነቀፌታ ያለበትን ምስኪን የተራቆተን የሰውን መንፈስና ነፍስ አይቶ ፍጹሙን ራራ፡፡አንዱን ኃጢአተኛ ፍለጋ መጣ፡፡ መላዕክቱ አይተው የምስጋናን ጅረት አፈሰሱ፡፡ ፍጹም የሆነን ደስታንም በሰማይ አደረጉ፡፡ አንድ ኃጢአተኛ ተመልሷልና በምድርም በሆነው ነገር ሁሉ በሰማይ አሰምተው ተናገሩ፡፡ የተራቆተው በጸጋው ዙፋን ፊት የክርስቶስን ጽድቅ ሲለብስ፣ የተራበው የህይወት ቃሉን ተመግቦ ሲቦርቅ፣ የተጠማው በማመኑ ከሆዱ የምንጭ ውኃ ሲፈልቅ፣ ኃጢአተኛው ስለማመኑና ስለመውደዱ እንዲሁ ምህረትን አጊኝቶ በመልካም ሲመለስበሰው መዳን መላዕክቱ እልልታቸውን እንደብዙ ውኃ አሰሙ፡፡
     ሰው በማይጥል እጅ ስለተያዘ፣ በማይደክም ትከሻ ስለታዘለ፣ በምቹ ዙፋንም ስለተቀመጠ፣ በእረፍት ውኃና በለምለም መስክ ስላረፈ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ወራሽ ሆኖ ሰማያዊውን ክብር ስለተቀዳጀ  … ኃጢአተኛእኔ ኃጢአተኛና ደካማ፣ አንተ ኃጢአተኛና ደካማ፣ አንቺእኛኃጢአተኞችና ደካሞች ጠላቶችም የምንሆን በእምነት በሚሆን ንስሐ በልጁ ሞት ታርቀን ሕይወቱንም አጊኝተን (ሮሜ.5÷6-10)ወደቀደመ ክብራችን  ስንገባ መላዕክቱ ለዘላለም እስከዘላለም አሰምተው ሳያርፉ አመሰገኑ፡፡
       "እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል"; (ሉቃ.15÷10)
    አዎ! እኔ ኃጢአተኛው በልጁ ሞት ዛሬ ምሕረቱን ለብሻለሁና ከሳሼ ሆይ ደስ አይበልህ፡፡ አመንዝራው ወንድሜ፣ ሌባዋ እህቴ፣ ገንዘብን አፍቃሪው አባቴ፣ የምታሚውም እናቴእኔ ከዚህ ሁሉ ነገር በጌታዬ ጉልበት ዛሬ ወጥቼ እነሆ በእቅፉ አለሁ፡፡በእኔም መመለስ መላዕክቱ ሁሉ ተደስተዋል፡፡ እናንተም ተመለሱና በእቅፉ እረፉ፡፡ ለደስታው ግብዣ የታረደው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁላችን የሚበቃ ነውና፡፡ መላዕክቱ ሆይ!  እነሆ ኃጢአተኛው ወደአባቴ ቤት በንስሐ ተመልሻለሁና ደስ ይበላችሁ፡፡

        ጌታዬ ሆይቀኝህ ስላቀፈችኝ ነፍሴ በዘመኔ ሁሉ ትባርክሐለች፡፡ አሜን፡፡                                  

2 comments:

  1. what anice beautiful spritual idea.God bless you. Brother God be with you.amen.......

    ReplyDelete
  2. This is our salvation,he is the only one sacrifices himself to the world.not only for me,it is a blessing.God bless you bra.by way nice to see you again.thanks.

    ReplyDelete