Tuesday, 4 November 2025

ቃሉን የሚያነብብ ብፁዕ ነው!

 Please read in PDF

ቅዱስ ቃሉን ማንበብ መንፈሳዊና ታላቅ አምልኮ ነው፤ አቡቀለምሲሱ ቅዱስ ዮሐንስ፣ “[ቅዱስ ቃሉን] የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” (ራእ. 1፥3) ይለናል። ሐዳሲው ቅዱስ ዕዝራ፣ “... ወንዶችና ሴቶች የሚያስተውሉም ሲሰሙ፥ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ ለመስማት ያደምጥ ነበር።” (ነህ. 8፥3) እንዲል፣ ቃሉን ከእኩለ ቀን በላይ ማንበብ እጅግ ታላቅ አምልኮ ነው።

እነ ነህምያና ዕዝራ በምርኰ ምድር ሳሉ ቅዱስ ቃሉን ዕለት፤ ዕለት ያነብቡ ነበር (ነህ. 8፥18)፤ ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርት በምኩራብ ሲገኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብን ያዘወትሩ ነበር፣ (ሉቃ. 4፥16፤ ሐ.ሥ. 13፥15)፤ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ድምፁን አሰምቶ ቅዱስ ቃሉን ሲያነብብ ሳለ፣ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን የሚያነብበውን ያስተውል ዘንድ ላከለት (ሐ.ሥ. 8፥28-30)። ኢትዮጵያዊው በጉዞው ኹሉ ቃሉን ሲያነብብ መገኘቱ፣ ቃሉን መውደዱን ያሳያል። ቃሉን መውደዳችን፣ ቃሉን በማንበብ ውስጥ ካለ መራብና መጠማት ይመነጫል፤ (መዝ. 119፥47)። ያላነበበ ጥማት፣ ራብና አምልኮ የለውም፤ መራብ፣ መጠማት፣ መናፈቅንና አብዝቶ መፈለግን አይችልም። ኢየሱስ በአባቱ ቤት በመቅደሩ ሳለ፣  “... በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄም ሲያቀርብላቸው ነበር።" (ሉቃ. 2፥46) ለምን? ካልን በትክክል ቃሉን የመፈለግንና የመናፈቅን እውነታም ሊያስተምረን።

ቃሉን ለማንበብና ለማሰላሰል እጅግ መትጋት ያስፈልጋል፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አዲሱን ትውልድ ስለ ቃሉ ሲመክር እንዲህ አለ፤ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግ. 6፥6-7) ሲል፣ ቃሉን ዘወትር ለማንበብና ለማሰላሰል ብርቱ ትጋት የሚያስፈልግ መዘንጋት አይገባም። እንዲህ ባለው ባንፈልገው ራብና ጥሙ እየከሰመ ሊሄድና ከመመንመን አልፎ ጨርሶ ሊጠፋ ይችላልና አብዝቶ መፈለግ፤ አብዝቶ መፈለግ ያሻል።

ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ። … እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ ሥርዓትህንም አሰላስላሁ።” (መዝ. 119፥15፡ 45-46) እንዲል፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ፍጹም የተሞላ ሰው፣ በቅዱስ ቃሉ ደስተኛና ቃሉን በማሰላሰልም ተድላን የሚያበዛ ነው።

ዘወትር ቃሉን ማንበብ ወደ ትጋት ይመራናል፤ ይህ ትጋት ደግሞ ቃሉን ቃሉን ወደ ማሰላሰል ይወስደናል፤ ቃሉን በማሰላሰል ኹለንተናው የተሞላ ደግሞ ከቃሉ ኃይል የተነሣ መታዘዝና ቃሉን “እሺ” ብሎ ወደ መተግበር መሄዱ አይቀሬ ነው። ቃሉን በመታዘዝ ውስጥ ፍጹም በረከትና የዘላለም ሐሴት አለ።

ብርሐነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁን ቅዱስ ጢሞቴዎስን ሲመክር እንዲህ አለው፣ “… እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ። … ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር።” (1ጢሞ. 4፥13፡ 15)። ቃሉን በትክክልና በጥንቃቄ ማንበብ እጅግ ታላቅ ብጽዕና ነው፤ ትጋቱ ብዙ ቢያደክምም፣ ነገር ግን ዘወትር ማድረግና ለማደጋችን ልንተጋ ይገባናል። ቅዱስ ቃሉን በትጋት አንብቡ፤ ደግሞም እስኪወርሳችሁ አሰላስሉ፤ ታዘዙትና ተደላደሉ፤ ተድላም ይብዛላችሁ፤ ይን በማድረጋችሁ አንዳች አትጸጸቱም!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

 

4 comments:

  1. እናንተን በቤቱ አፅንቶ ለአገልግሎት ያበቃ ጌታ እኛንም በአገልግሎታችሁ ተጠቅመን 30 60 100 ያማረ ፍሬ እንድናፈራ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን

    ReplyDelete
  2. ➕💒⛪ቃል ህይወት ያሠማልን ዳያቆን

    ReplyDelete
  3. Kale hiyiwet. Yasemalen❤❤❤💚💛❤️🤲🤲🤲

    ReplyDelete
  4. እድሜና ጤና ይስጥኽ ❤

    ReplyDelete