Friday, 24 October 2025

የትውልድ ነቀርሳ - የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ክፍል - ፮

 Please read in PDF

3.    ክርስቶስ የመዳን ራስ እንደ ኾነ የሚታመነውን የክርስትና ዋና እምነት ጨርሰው ይክዳሉ፦ በአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አስተምኅሮ መሠረት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ “ዮጊ” ወይም “የዕውቀት ብርሃን ያገኘ የበራለት ሰው ብቻ” ነው። ይህም ብቻ ሳይኾን፣ ርሱን ፍጹም አምላክ ነው ብሎ ማመንና ማምለክ፣ መጥፎና ሰዎችን ‘እውነተኛ ኃይላቸውን’ ከማወቅ ለማራቅ የታለመ የውሸት ትምህርት ነው ብለው ያምናሉ፤ ያስተምራሉም።

ከዚህም ባሻገር የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ከክርስትና የሚቀበለው መርጦ ሲኾን፣ የክርስቶስን ፍጹም አምላክነት ባለ መቀበል ደግሞ ግንባር ቀደም ነው። ከፊል የክርስትና ትምህርትን ቢቀበልም እንኳ ከክርስትና ትምህርት ጋር፣ ጥንቆላን፣ ሂንዱይዝምን፣ ብዝኀ አምላክነትን፣ ቡድሂዝምን፣ አስትሮሎጂንና የኡፎሎጂ አስተምኅሮዎችና ልምምዶችንም ጭምር በአብሮነት ደባልቆ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ግን፤ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።” (ማቴ. 16፥24)፣ አለ፣ ምክንያቱም፣ “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።” (ማቴ. 11፥27) እንዲሁም፣ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ. 14፥6)፣ በሌላ ስፍራም፣ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3፥36) ብሎአል።

ክርስቶስ የሕይወታችን ራስ ወይም መገኛ ነው፤ (ሐ.ሥ. 3፥15)፤ መዳን ከርሱ በቀር በሰማይም ኾነ በምድር በሌላ በማንም የለም፤ (ሐ.ሥ. 4፥12)፤ ደሙን በማፍሰሱ ምክንያትም፣ “በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አጊኝተናል፤ ርሱም የበደላችን ስርየት” (ኤፌ. 1፥7) ነው። “ደም ሳይፈስ ስርየት የለም”ና (ዕብ. 9፥22)። ስለዚህ ጌታችን ክርስቶስ ደሙን ሰጥቶአል፤ ዐዲሱ ኪዳን ተመርቆ በተከፈተበትና (ዕብ. 9፥15፡ 18) የኀጢአታችን ማስተስረያ ይኾን ዘንድ በፈሰሰው ንጹሕ ደሙ (ቈላ. 1፥19) አማካይነት ታጥበን (ራእ. 1፥5) በመንጻት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ኾኖልናል። ክብር ይግባው መድኃኒታችን! እንዲያውም፣ ያለ ክርስቶስ የዚህን ዓለም የትኛውንም ነገር ተስፋ የሚያደርጉ፣ ከሰው ኹሉ ይልቅ ድኾችና ምስኪኖች ናቸው፤ (1ቆሮ. 15፥19)።

ስለዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አስተማሪ ብቻ ያይደለ፣ ፍጹሙ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉበት ዋነኛ ዓላማም፣ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እናምንና፣ አምነንም በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ”፤ ነው፤ (ዮሐ. 20፥31)። ያለ ኢየሱስ የቱም ሕይወት፣ ጨለማ፤ የቱም ሞት፣ ትንሣኤ አልባ፣ የቱም ክብር፣ በውርደት የታጨቀ ከንቱ ነው፤ መድኃኒታችን፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የኾነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ብሎ አጽንቶ ተናግሮአል፤ (ዮሐ. 11፥25-26)።

ስለዚህም እኛ የሥላሴ ፍጡራን የኾንን፣ ክርስቶስን በማመን ደግሞ በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ኾንን እንጂ እንደ ኢየሱስ የኾንን የእግዚአብሔር ልጆች አይደለንም። እኛ ፍጡር ነን፤ ክርስቶስ ግን ምንም እንኳ ሥጋ በመልበስ የተገለጠ ቢኾን የፍጥረተ ዓለሙ ፈጣሪና አስገኚና አሳላፊ ጌታና አምላክ ነው። ነገም፤ ተነገ ወዲያም እኛ ፍጡራንና የእግዚአብሔር ፍጹም አምልኮ የምናቀርብ የተመረጥን ሕዝቡ ነን፤ አምላክ አልነበርም፤ አንኾንም፤ አይደለንም፤ ወደፊትም ጨርሶ አንኾንም!

ቤዝወታችን፣ መዳናችንና ጽድቃችን ከእግዚአብሔር ብቻ እንደ ኾነም እናምናለን። ያለ ክርስቶስ ሰው የኀጢአቱን ቤዛና ሥርየት ሊያገኝ አይችልም፤ ያለ ክርስቶስ መካከለኝነትም ሊታረቅና ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ጨርሶ አይችልም። ሰው በኃጢአቱ ምክንያት የሚገባውን ቅጣት በመውሰድና በራሱ ብቻ ድኖ፤ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ አይችልም፤ (2ቆሮ. 5፥21፤ 1ጢሞ. 2፥5)፤ ከዚህ ትምርት ውጭ ያሉት በግልጥ ቃል የክርስቶስ መስቀል ጠላቶችና የማያምኑ ናቸው፤ (ፊል. 3፥18)።

ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።” (1ቆሮ. 16፥22)

ይቀጥላል …

3 comments:

  1. ኦርቶዶክስ ነኝ ይህን ትምህርት እቃወማለሁ

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ተሰፋ መንግስተ ሰማያትን ያውስልን

    ReplyDelete
  3. የአገልግሎት ዘመኖን ይባርክ መድሃኒዓለም

    ReplyDelete