Wednesday, 1 December 2021

ስህተትን ማን ያስተውላታል? (መዝ. 19፥12)

Please read in PDF

ኀጢአት አማኞች እንዳያስተውሉት ስለሚፈልግ፣ በጽድቅ መዝገብ ውስጥ ራሱን መደበቅ ይወዳል። አብዛኛኞቹ አማኞች ግን የተገለጠ ኀጢአትን አይተው ሲሸሹ፣ ራሱን ሊገልጥ የማይወደውንና ስውሩን ኀጢአትን ግን ሲዘፈቁበት አልያም “ኀጢአት አይደለም” ብለው ሲሞግቱ እንሰማቸዋለን። ከዚህ የተነሣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተሐድሶ እንዲመጣ የሚሹ አካላት፣ ዘወትር ሊያመለክቱ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ፣ ራሱን ሸሻጊውን፣ “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ባለ ነገር በነውር ሊይዝ” (ኤፌ. 5፥27) ከሚተጋው ኀጢአት መጠበቅና ማስጠንቀቅ፤ ዘወትር አማኞች እንዳይረሱ ማሳሰብ ነው።

ይህን የተረዳው መዝሙረኛው፣ እንዲህ በማለት ይጸልያል፤ “ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ።” (መዝ. 19፥12)፤ የእውነተኛ አማኝ ምጡ፣ በእግዚአብሔር ፊት እንከን አልባ ኾኖ መመላለስ ነው፤ የመዝሙረኛው ምጥ እንዴት ያለ ታላቅ ምጥ ነው!? መዝሙረኛው በዚህ ክፍል፣ የሰውን ልጅ ፍጹም ኀጢአተኝነት፣ ውሱንነት፣ ከዚህም የተነሣ ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ተወዳጁ፤ ከማርና ከማር ወለላም ይልቅ ጣፋጩ፣ ቅዱሱና ፍጹሙ የእግዚአብሔር ቃል የሰውን ኹለንተና ልብና ኩላሊቱን፣ ዐሳብና ምልልሱን ኹሉ ከሕፃንነት ጀምሮ እንደሚመረምር፤ እንደሚፈትን፤ እንደሚያበጥር ይናገራል።

“የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤” እንዲል፣ እንዲህ ባለ ታላቁና ቅዱሱ ጌታ ፊት የሚቆመው መዝሙረኛ፣ በፍጹም ፍርሃት ውስጥ ኾኖ ነው። በእርግጥም እውነተኛ አማኝ፣ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው በፍጹም ፍርሃት ነው። ምክንያቱም እርሱ ያልደረሰበት ወይም የማያውቀው ኀጢአትና በደል እንዳለ በማስተዋል ነውና። መዝሙረኛው ለዚህ ነው እንዲህ እያለ የሚጸልየው፤ “ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ።”።

መዝሙረኛው ስውር በደሉ አሳስቦት፤ አስጨንቆት አዳኝ አምላኩን “አንጻኝ” ብሎ ይማጸናል፤ መዝሙረኛው እንኳን በአደባባይና በተገለጠ ነውር ይቅርና፣ በአንዳች ስውር በደል አምላኩን መበደል አይሻም፤ መሻቱና ተማጽኖው አምላኩን ሳይበድል በፊቱ በንጽዕናና እንከን አልባ ኾኖ መኖር ነው። እናም አምላኩ መንጻትን እንዲሰጠው፣ ይቅር እንዲለው ፍጹም በትህትናና እንደ ባሪያ ራሱን በመቊጠር ያቀርባል።

የጻድቅ ጥሙና ረሃቡ፣ “እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ መውደድ ነው” (ዘዳግ. 6፥5)፤ ጻድቅ ደፋርና ትዕቢተኛ አይደለም፤ ይልቁን ልክ እንደ ኢዮብ፣ “ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ … እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር።” (ኢዮ. 1፥5)፤ እንዲል፣ ሳያውቅ ለሚሠራው በደል በእግዚአብሔር ፊት በፍጹም ፍርሃትና ትህትና ቆሞ መንጻትና ይቅርታን ይለማመናል፤ (ዘሌ. 5፥2-4)።

ሰው ዘወትርና ሳያቋርጥ በእግዚአብሔር ካልተደገፈ በቀር፣ ዝንባሌውና ዐሳቡ ኹሉ ጠማማና እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ነው፤ በብዙ መንገዱም ሳያውቅ አምላኩን ሊያሳዝን፣ ሊበድልና ሊስት ይችላል፤ እናም ዘወትር ወደ አምላኩ ሊጸልይ፣ “አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።” በማለት አምላኩን ሊለማመጥ ይገባዋል።

ዛሬ ላይ በስውር የዘረኝነት፣ የጥላቻና የበቀል ስሜት ያልተያዘ፤ በነውርና በዕድፈት ያልቆሸሸ፣ በስውር ኀጢአትና በደል ያልተያዘ ማን ይኾን? ይህ ጸሎትስ አያስፈልገኝም የሚል ጻድቅ ከቶውኑ ይኖር ይኾንን?

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

 

 

2 comments:

  1. tru mkr new tebarek

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር በብዙ ይባርክህ መንፈስቅዱስ በዘመንህ ሁሉ አቅምና ጉልበት ኃይልም ይሁንህ።

    ReplyDelete