Thursday, 18 November 2021

“ወደ ኦርቶዶክስ አልተመለሱም፤ በዚህ መንገድም አይመለሱም!”

 Please read in PDF

ወደ ኦርቶዶክስ ተመልሰናል ባዮችና የኦርቶዶክስ “ቀናተኛው ማኅበረ ቅዱሳን”

የቀናተኞቹ ውይይት ዕጣሬ

በባለፈው ወር ”ወደ ኦርቶዶክስ ተመልሰናል“ ያሉ ወገኖች ብዙ ነጋሪት አስጐስመዋል፤ ከበሮ አስመትተዋል፤ እንቢልታ አስነፍተዋል። ነገር ግን ያስነፉትን እንቢልታ፤ ያስመቱትን ከበሮ፤ ያስጐሰሙትን ነጋሪት ያህል፣ ተቀባይነትን ሳይኾን “ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ ‘ኦርቶዶክሳዊ’ ቀናተኛን” በሚገባ አስቀሰቀሰባቸው እንጂ አልጠቀማቸውም። “ተመላሾቹ”፣ እንዲመለሱ መንገድ ያደላደለላቸው ሰው፣ “የማኅበራዊ ሚዲያ አቅም እንዲጠቀሙ በብዙ እንደ መከራቸው ይታመናል፤” ግን ውጤቱን አለመመዘናቸውና በተቀደደ ቦይ መፍሰሳቸው ሊመጣ ያለውን ናዳ አለማስተዋላቸው ወለል አድርጎ ያሳያል።





በቅርብ ርቀት፣ በ“ተመላሾቹ” ላይ፣ ኦርቶዶክሳውያን ቀናተኞች በሚገባ ተደራጅተው በተቃውሞ ተነሥተውባቸዋል። በግልጥ ቃልም፣ አገሩን የከዳ አንድ ወታደር፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ፈጽሞ እንደማይመለስ፣ እንዲሁ እኒህም ቤተ ክርስቲያንን ሲክዱ ጸጋውና ክህነቱንም ጭምር አብረው ክደዋል፤ ስለዚህም ኹሉም ነገራቸው አብሮ ተሽሮአል፤ ስለ መጡ ብቻ ከመድረክ ወደ መድረክ የሚሸጋገሩበት መንገድ የለም፤ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተመለሱ ሊያስቡ ይገባል እንጂ። ከመድረክ ወደ መድረክ ማሰባቸው በራሱ የጤና አይደለም።” በማለት ሲናገሩ ሰምተናል። በተጨማሪም፣ “መመለሳቸው የኹላችንም ደስታ ነው! … መመለሳቸውንም የእውነት ያድርግልን፤ ከመመለሳቸውም በፊት ግን በሽተኞች መኾናቸውን ማመን ይገባቸዋል።”

ስለሚመለሱ ሰዎች ምን ማድረግ ይገባናል? ለሚለው፣ ያረጋል አበጋዝ አምስት ነጥቦችን ያስቀምጣል፤ እኒህም፦

·        ከኑፋቄ እንዲመለሱ እንጸልያለን፤ ስለ መመለሳቸውም ደስታችንን እንገልጽላቸዋለን፤

·        ኦርቶዶክሳዊ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይገባል፤ የትምህርት ችግር ስላለባቸው፤ መንፈስም፣ ትምህርቱም እንዲለቃቸው በተደጋጋሚና በደንብ የተያዘ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል።

·        ኖላዊ ክትትል ያስፈልጋቸዋል፤ ጥንቃቄ ክትትል ያስፈልጋል፤ መጥተው ቤተ ክርስቲያንን ሊበጠብጡ ስለሚችሉ ብርቱ ክትትል ያስፈልጋል።

·        የሠሩትን ስህተት በሠሩበት መንገድ ፍጹም ሊያወግዙና ሊያስተባብሉ ይገባቸዋል። መጽሐፍ ጽፎ ያስተማረው፣ መጽሐፍ ጽፎ ማውገዝ አለበት፣ የዘመረ በዝማሬ የቀደመ ሥራውን እየዘረዘረ ማውገዝ አለበት።  መጨረስ ያለበትን ኹሉ መጨረስ ያለበት ደግሞ ከንስሐ አባቱ ጋር ነው፤ በአደባባይ ከበደለ ወይም ከኑፋቄ የሚመለስ ደግሞ ንስሐው በሕዝብ ፊት በጉባኤ መኾን አለበት። ይህን ካላደረጉ ምዕመናንን በኑፋቄ ማበላሸታቸው አይቀርም።

·        በእነርሱ ኑፋቄ ማስተማር ምክንያት የተነሣ፣ የጠፉ ሰዎች ካሉ እነርሱን መመለስ ይገባቸዋል። የታወቁትን ያህል ሊመልሱ እጅግ ሊተጉና ሊጥሩ ይገባል።

ግለ አስተያየቴ!

ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ መንገድ ለዝቦ መቅረቡ፣ በመንጋ ራሳቸውን በሲኖዶስ ቦታ አስገብተው፣ ከማውገዝና ከማጣጣል በፊት እንዲህ በጥቂቱ ልበ ሰፊ መኾናቸው በራሱ ይበልየሚያሰኝ ነው። በርግጥም የ“ተመላሾቹን” ስልና አደገኛ መንገድ ማስተዋላቸው፣ “እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ” የሚለውን ተረት በሚገባ ያስታውሳል። በማናቸውም መንገድ፣ ክርስቶስን ንቆና መካከለኝነቱን ነቅፎ የሚመለስና ወደኋላ የሚያፈገፍግ ሰው፣ ከዚህ የተሻለ አቀባበል እንደማይጠብቀው እናምናለን። ማኅበረ ቅዱሳን የቀደመ ጠባዩን እንዲህ በግልጥ ማውጣቱ ትክክል ነው፤ ከጥንትም እንዲሁ ክርስቶስንና የክርስቶስ የኾኑትን በማሳደድ የታወቀ ነውና። እናም እንኳንም እንዲህ ተገለጠ፤ ለትክክለኛ ወንጌል አማኞች የሥራ ጊዜያቸው አኹን ነውና!



ወደ ኦርቶዶክስ “መመለስ”፣ ከኦርቶዶክስ እንደ መውጣት አይቀልም!

በአጭሩ በዚህ ዘመን፣ የቅዱሳንን ወይም የፍጡራንን መካከለኝነት ትቶና ነቅፎ፣ የክርስቶስን የብቻ መካከለኝነት መቀበል በራሱ ብርቱ ሰማዕትነት ነው። “ወደ ኦርቶዶክስ እንመለስ” ያሉት አካላት፣ ያላስተዋሉት አንድ እውነት፣ የቅዱሳን መካከለኝነት በገነነበት፣ የክርስቶስን የብቻ መካከለኝነት አጠይመው ለመስበክ እንደሚችሉ መጃጃላቸው ነው። ማኅበረ ቅዱሳን በግልጥ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባቸው አስቀምጦአል። በመጽሐፍ የካደ፣ በመጽሐፍ ክህደቱን ሊገልጥ ይገባል፤ እና የክርስቶስን የብቻ መካከለኝነት የሰበኩና የዘመሩ ኹላ፣ ሌላ መካከለኛና ሌላ መታረቂያ ይሰብኩናል ወይም ዓይናቸውን በጨው አጥበው ይመጣሉ ማለት ነው።

በእርግጥ በውይይቱ ላይ እንደ ተነሣው፣ ይህንም የማድረግ ዕድል የሚያገኙት፣ እጃቸውን ይዞ፤ አንገታቸውን አንቆ ካላወረዱአቸው ብቻ ነው። ቀናተኛው ማኅበረ ቅዱሳን ይህንም ማድረግ እንደሚችል ደም ሥሩ እየተገታተረ ተናግሮአልና።



“ከወጡት ይልቅ ያልወጡት ይበልጣሉ!”

በውይይት መድረኩ ላይ፣ ይህን የተናገረችው “ዘማሪት” መሠረት ናት፤ ይህ ድንቅ ምስክርነት ነው። ይህን ማመናቸው በራሱ፣ ታላቅ የወንጌል ሥራ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እየተሠራ ለመኾኑ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ወንጌል የሰው ሥራ ሳይኾን፣ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፤ ተሐድሶ እኛ የምንሠራው ወይም እኛ እንዲመጣ የምንሻው ሥራ ሳይኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ራሱ እንደ ወደደ የሚሠራውና የሚተገብረው ነው። የነፍስ መዳን ጉዳይ ከዘላለም የእግዚአብሔር እንጂ፣ የሰው ሥራ ኾኖ አያውቅም። እኛ በመንግሥቱ እርሻ ውስጥ ያለን፣ አገልጋዮች ነን፤ ስለ መከሩ መብዛትና ስለ ነፍሳት መጨመር ግድ የሚለው፣ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ እኛ ደግሞ ባለሟሎቹ ነን። ተመለስን ባዮቹ ግን ከኹለቱም ወገን አለመኾናቸው ሌላ ተረት ያስታውሰኛል፤ “የፈለጉትን ቢያጡ ያጡትን ይቀላውጡ” እንዳይኾንባቸው ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይህን ብርቱ የተግሳጽ ቃል ግን መናገር ይገባናል!

“በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።  ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፦ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።”  (2ጴጥ. 2፥20-22)

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)

የማኅበረ ቅዱሳንን ሙሉውን ውይይት በዚህ ተመልከቱ -  ቀናተኛው ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ኦርቶዶክስ ተመለስን ላሉት ያደረገው ጥብቅ ውይይት! - YouTube

2 comments:

  1. አቢኒ ሰላካፈልከን በብዙ ተባረክ። መንፈስ ቅዱስ አሁንም
    ሊመጡት ባሉት ቀኖችና ዘመናት አቅም እና ኀይል ይሁንህ

    ReplyDelete