Thursday, 16 September 2021

“ኑ! ወደ ኦርቶዶክስ[ዊነት] እንመለስ!” (የመጨረሻ ክፍል)

 

ካለፈው የቀጠለ …

ዛሬ ኦርቶዶክስ ማን ነው?

“ተዋሕዶ ሳይኾን ስሙ ሃይማኖቱ

ኦርቶዶክስም ሳይኾን ባህሉና ትምህርቱ

ሰርቆና ቀምቶ የሰው ስም በከንቱ

ሰው ኹሉ አለስሙ ምነው መጠራቱ”[1]


“መሃይምናኑ ራሳቸው ስለ ሃይማኖት ያላቸው ዕውቀት ዝቅተኛ መኾኑን መዝነው ስፍራውን ይለቅቁላቸው ዘንድ ተገቢ በሚኾንበት ፈንታ፣ ሊቃውንቱን በመናፍቃን ስም ቀብተው ‘አብዝኆ መጻሕፍት ያዘነግዕ ልበ።’ የሚል የአረማዊውን የፊስጦስን ቃል እየጠቀሱ (የሐዋ. ፳፮፥፳፬) ወዲያውኑ እንደ ተለመደው በሠለስቱ ምእት ሊቃውንት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሊፈርዱባቸው እንዳይቸኵሉና በዚሁ አስገራሚ አኳኋን የቤተ ክርስቲያንዋ መሻሻል ዕድል እንዳይሰበር አሥጊ መኾኑን ብቻ ለማሳሰብ ነው።”[2] እንደ ተባለ፣ ዛሬ ኦርቶዶክሳዊነትን የጨበጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የማያከብሩ፣ በኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት የጸኑትን የሚነቅፉና የሚያዋርዱ ናቸው።

በተቃራኒው የፍጡራንንና የግዕዛንን መካከለኝነት የሚሰብኩ፣ የክርስቶስን አምላክነት ብቻ እንጂ ሰውነቱን የተዉ ወይ ጨርሶ የዘነጉ፤ ለአምላክ ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን አምልኮታዊ ሥርዓት ለማናቸውም ፍጡራንና ግዕዛን የሚያቀርቡ … ኾነው ሳለ፣ በዚህ ተግባራቸው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ሌላውን መናፍቅና ሐራ ጥቃ ማለታቸው እጅግ የሚያሳፍር ተግባር ነው። አዎን፤ ዛሬ ላይ ኦርቶዶክሳውያን ነን የሚሉት፣ እንደ ቅዱስ ቃሉ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ያልኾኑት እንደ ኾኑ እሙን ነው።

ትምክህተ ኦርቶዶክስ!

ትክክለኛው ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሲኾን፣ በተቋም ደረጃ ራሱን ኦርቶዶክስ ብሎ የሚጠራው ተቋማዊው ኦርቶዶክስ[ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ግሪክ ተዋሕዶ፣ ራሺያ ኦርቶዶክስና ሌሎችም] ግን መሠረታቸውን የጣሉት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ባሉ አያሌ ሰዋዊ ተረቶችና እጅግ ዘግናኝ እንግዳና ልዩ አስተምኅሮዎች ላይ ነው። ይህም ኾኖ ግን፣ ስህተታቸውን ተቀብለው ለማስተካከል ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ፣ በከንቱ ግብዝነት በመታበይ በዚያው ስህተት መጽናት የፈለጉ ይመስላል። እንዲያውም በአገራችን ያለው ተቋማዊው ኦርቶዶክስ፣ ክርስትናን ከዓለም አገራት በግንባር ቀደምትነት የተቀበልን ነን በሚል ትምክህት ብቻ ሲኖር እንጂ፣ እልፍ ብሎ ፍጥጥ፤ ግጥጥ ብለው የሚታዩ ስህተቶችን ለማስተካከል የሚሠራ ሥራ አይስተዋልም።

በእርግጥ አንዳንድ በውስጥ ያሉቱ አባቶች፣ “ከብዙ አንጻር ሲታይ ኦርቶዶክሳዊው በኢትዮጵያ ያለው ክርስትናው በአገር ባህል ውስጥ የበቀለ እንጂ፣ በትክክል እንደ ክርስትናው ጠባይ የተተከለና የበቀለ የማይመስል መኾኑን ገልጠው ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።[3]

የንስሐ ጥሪ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ለክርስቶስ ወንጌል ራሳቸውን እንደ ለዩ በአንደበታቸው ከተናገሩ፣ “ቤተ ክርስቲያንም ከመሠረቱ”፣ ሕዝብ ሰብስበው ማገልገል ከጀመሩ … በኋላ፣ በተቋም ወደ ተደራጀውና የክርስቶስን እውነተኛ ወንጌልና መካከለኛነት ወደ ነቀፈው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንመለሳለን የሚሉ አገልጋዮች መብዛታቸውን እያስተዋልን ነው። ወደ ኋላ የሚመለሱባቸው ምክንያቶች እጅግ አያሌዎች ናቸው።

ምክንያቶቹ ምንም ይኹኑ ምን ግን፣ ወደ ተቋማዊው ኦርቶዶክስ መመለስ እንፈልጋለን ማለት፣ የማርያምን መካከለኝነትን ከኢየሱስ ለይቼ አስተምራለሁ ማለት አይደለም። ወደ ኦርቶዶክስ ለመመለስ የሚያስቡና የሚመለሱ ሰዎች፣ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ነገር የኢየሱስን በቂነትና መካከለኝነት መንቀፍ ነው። በተቋም ደረጃ የተደራጀው ኦርቶዶክስ ይህን በተደጋጋሚ በአያሌ አማኞችና አገልጋዮች ሲፈጽም፣ በሲኖዶስም ደረጃ ሲያወግዝና ሲያስወግዝ፣ የክርስቶስን መካከለኝነትን ያስተማሩትን በአደባባይ ሲሳደቡ፣ ሲደበድቡ፣ አልፎ ተርፎም ንብረቱን ሲዘርፉና የአካል ጉዳት ሲያደርሱ ታይቶአል።

እናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ወደ ወንጌላዊው የክርስቶስ ትምህርትና ሕይወት የመጣን ብዙዎችን ጌታችን ኢየሱስ እንዳስተማረን፣ ሰይጣን እምነታችንን ሊያጠፋ እያበጠረን መኾኑን አንዘንጋ (ሉቃ. 22፥31)፤ እናም በክርስቶስ ባለማፈር ጸንቶ መቆም ሲገባን፣ እርሱን በሚያሳፍር፣ አገልግሎታችንን በሚያስነውር፣ የተከተሉንን በሚያዋርድና ክፉ ምሳሌነትን በሚያንጸባርቅ ብሎም በሽምግልና ዘመን የምንጸጸትበትን ውሳኔ በመወሰን ለክርስቶስ ወንጌል መሰደብ ምክንያት እንዳንኾን እንጠንቀቅ!

መውጫ!

ኦርቶዶክሳዊ እውነት መጽሐፍ ቅዱስን፣ የክርስቶስን ሕይወትና ትምህርት አድርጎ ሲሰበክና ሲነገር ብቻ ነው፤ የእውነተኞቹ እውነት ክርስቶስ፣ እምነታቸውም ራሱ ክርስቶስ ነው! ርቱዕነትም(እውነተኛነትም) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረት መያዝ እንጂ፣ በተቋሙ ኦርቶዶክስ ስም መጠራትም አይደለም! ከዚህ የወጣው የሰው ትምህርትና ወግ ነው! እንግዲህ ሰዎች ወዳደራጁትና መጽሐፍ ቅዱስን ሰፍተው ወዳለበሱት ኦርቶዳክሳዊነት ሳይኾን፣ ለክርስቶስ ትምህርትና ሕይወት፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ወደ ተሸነፈና ወደ ታዘዘ አማናዊ ኦርቶዶክሳዊነት ኑ እንመለስ! ትኵረታችን፣ ጥማታችን፣ መሻታችን፣ ረሃባችን፣ መቃጥናችን፣ ስስታችን … መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ በመንፈሳዊ ኅብረት በመሰባሰብ መጸለይ፣ አንዳችን ሌላችንን በመቀባበል በእውነተኛ የክርስቶስ አጋፔያዊ ፍቅር እንታዘዝ፤ ትውልድ ሆይ፤ ኑ! ወደ አማናዊው ኦርቶዶክስ እንመለስ፤ ደግሞም የሐዋርያት ሥራ ላይ ወዳለችው ወይም ሐያ ዘጠነኛውን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን በሕይወታችን ለመጻፍ እንነሣ!

ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ! አሜን!

ተፈጸመ



[1] ገጽ 19

[2] መሠረት ስብሃትለአብ (አለቃ)፤ ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ፤ 1951 ዓ.ም፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 15

[3] ተሾመ ዘሪሁን (መልአከ ታቦር)፤ ዝክረ ነገር፤ 2009 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ማተሚያ ቤት ያልተጠቀሰ፤ ገጽ 74

2 comments:

  1. GOD bless you for sharing Abiny. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come.

    ReplyDelete
  2. Yes. Hearing God. Period! No noise. GBU

    ReplyDelete